Tuesday, August 21, 2018

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ሰላሳ

ከክፍል ሃያ ዘጠኝ የቀጠለ
የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤ ክፍል ስድስት
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
       ባለፉው ክፍል 29 ጸሁፋችን ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ያስተላለፉትን ውግዘትና ማስረጃዎቹን፤እንዲሁም ውግዘቱን ላለመቀበል የሚቀርቡ ምክንያቶችን  አስነብበናችሁ ቀጣዩን ክፍል "ከእኛ ምን ይጠበቃል" በሚለው ሃሳብ እንመለሳለን ብለን እንደነበር ይታወሳል፡፡ይህ የቤት ሥራችን እንደተጠበቀ ሆኖ ለዛሬው ከአባታችን ከአለቃ አያሌው በስማቸው ከተከፈተው ድረ-ገጽ www.aleqayalewtamiru.info ላይ ያገኘነውን ለአስራ አንደኛ ዓመት መታሰቢያቸው የቀረበውን ጽሁፍ ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡
ሰምተን ለመጠቀም ያብቃን፡፡

ይህ  ጽሑፍ የክቡር አባታችን የአለቃ አያሌው ታምሩን ዕረፍት 11ኛ ዓመት በማሰብ የቀረበ ነው።
 ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ጉባዔ ዋና ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት በመጀመሪያው       የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትረያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ሰያሚነትና  በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እውቅና ነው፡፡
 የዕለት ተዕለት ተግባርን በተመለከተ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ ተጠሪነትና የሥራ ኃላፊነት በተመለከተ ሚያዝያ 2ዐ ቀን 1959 ዓም የወጣው ነጋሪት ጋዜጣ ትእዛዝ ቁጥር 48 ንዑስ ቁጥር 4 ላይ በወጣው አዋጅና በ1984 ዓም ተሻሽሎ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረትነት ተጠሪነታቸው የቅዱስ ሲኖዶስ የነበረ ሲሆን  የተሰጣቸውን ኃላፊነት በከፍተኛ ደረጃ ሲወጡ ኖረዋል፡፡
       ከሃምሳ እስከ ስልሳ ዓመታት በሚቆጠረው የአገልግሎት ዘመናቸው  ሃይማኖትን፣ ቋንቋን፣ ባሕልን፣ የለያዩ የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፎችን አስመልክቶ ግምባር ቀደም ተጠያቂ የነበሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን፣ ኢትዮጵያን፣ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያውያንን አስመልክቶ የዓለማዊውም ሆነ የመንፈሳዊው ክፍል ባለሥልጣናት ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫናና ቅጣት ሳይፈሩ ስለማንኛውም ዓይነት አወዛጋቢ ጉዳይ የሚያምኑበትን በግልጽ፣ በድፈረትና በልበ ሙሉነት በማስተማር፣ በመምከር፣ በመገሰጽ በእሳቸው ደረጃ ከደረሰ ምሁርና የሃይማኖት አባት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል፡፡
 ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገለገል ላይ በቆዩባቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ በውጪ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጪ ይሰነዘሩ የነበሩ ፈተናዎችን ሁሉ ጠንክረው በመጋፈጥና በመመከት የኖሩ ለመሆናቸው የቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ የሚያውቀው ነው፡፡ ከውጪው ፈተና በተጨማሪ በራሷ ጳጳሳትና አገልጋዮች በኩል መሰንዘር የጀመውን አደጋ በመጋፈጥ ረገድም ግመባራቸውን ሳያጥፉ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡
       በተለይም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛ ፓትረያርክ በአባ ጳውሎስ ዘመን የገጠማት ፈተና ግን በዓይነቱና በክብደቱ ለየት ያለ ሆኖ ይታያል፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት እስከ አበው ሊቃውንት፣ ከአበው ሊቃውንት እስከ ቅርብ ዘመን የደረሰውን እምነቷን ጠብቀው ለማስጠበቅ፣ አክብረው ለማስከበር፣ ምእመናንንም በቀደመችው የጸናች እምነት ለመጠበቅ ምለው በተሾሙ በራሷ ጳጳሳት የተሰነዘረ ውስጣዊ ፈተና ሲሆን ከብዙዎቹ ውስጥ አንዱና ዋነኛው የፓትረያርክነት ሹመት ተቀብለው ዓመት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ወደሮም በመጓዝ ለ16ዐዐ ዓመታት ተጠብቆ የኖረውንና በሁለቱ አብያተ ክርስቲያን መካከል የነበረ ግዝት መጣሳቸው ነው፡፡
        ይኽንን አስመልክቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና ጠብቆ በማስጠበቅ ረገድ ኃላፊነት ከነበረባቸው ከሊቃውንቱ ጉባዔ ዋና ሰብሳቢ ከአባታችን ከአለቃ አያሌው ታምሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ በተጽዕኖ በማፈን በጉዟቸው የፈጸሙትን መሠረታዊ የሆነ የቀኖና ጥሰት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ጉዳዩ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ሳያሳውቁ ተከታታይነት ያላቸውን ድርድሮችና ስምምነቶችን ፈጽመዋል፡፡
       ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በነበራቸው ጥንቃቄና በመንፈሳዊ መርህ የመጓዝ ስብእና የተነሳ ጉዳዩን ገና ከጅምሩ በንቃት ሲከታተሉ የነበሩት አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ከፓትረያርኩ ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስና እያንዳንዱ አባላት እንዲወያዩበት ለማድረግ ብዙ ትግል ቢያደርጉም ትልቁ ቁምነገር እንደ ቀልድ ታይቶ ታለፈ፡፡ በሂደቱ ውስጥ በአባታችን ላይ ብዙ መከራና ግፍ የተፈጸመባቸው ሲሆን ለስድሳ ዓመታት በቅንነትና በሙሉ ልብ ካገለገሏት ቤተ ክርስቲያን የጡረታ መብታቸውን ሳይቀር ተገፈው ከሥራ እንዲገለሉ ተደርጓል፡፡
        የተፈጸመውን የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ አባታችን ያቀረቡትን የሃይማኖት ጥያቄ ማቅረባቸው በፓትረያርኩና በወቅቱ የቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በአባ ገሪማ ላይ እንደተሰነዘረ ድፍረት ተቆጥሮ "ከፓፓው በላይ ክርስቲያን ነኝ" እንዳለው ሰው ሆነሀል ከሚል ዘለፋ ጀምሮ በርካታ ፌዝና ስድብ የተቀበሉ ሲሆን ያልተደረገና ያልሆነ ነገር እንደተናገሩ ተደርጐ በኮሚቴም አንደተጠና ተደርጐ ለጉዳዩ ሀሰተኛ ገጽታ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ ነገርግን በጊዜው በፓረያርኩ የተፈጸመው ቀኖናዊ ጥሰት እንዲሸፋፈንና እንዲደባበቅ ቢደረግም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የራሷ የቫቲካን ሬዲዮ አማካይነት እውነቱ ፍንትው ብሎ ወጥቷል፡፡ ይኸውም የተገለጠው ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትረያርክ አባ ማትያስ በ2016 ዓ.ም. ቫቲካንን መጐብኘታቸውን ተከትሎ የቫቲካን ሬዲዮ ባስደመጠው አንድ ዜና ላይ ነው፡፡ ዜናው ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ሲተረጐም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
"የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሃይማኖት ውይይት የሚያደርገው አለምዓቀፋዊ ኮሚሽን አካል ነች፡፡ይህ ኮሚሽን በየዓመቱ የሚሰበሰብ ሲሆን ዓመታዊው ስብሰባ በሮም ወይም ሰባቱ አባል የኦርዬንታል አብያተ ክርስቲያናት በወከሉት አገር ይካሄዳል፡፡
       በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንና በሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መካከል የተፈጠረው ግንኙነት የተጠናከረው በፊተኛው ፓትረያርክ በአባ ጳውሎስ ዘመን ሲሆን እሳቸውም በ1993 ዓ.ም. ከፓፓ ጳውሎስ 2ኛና በ2ዐዐ9 ዓ.ም. ከፓፓ ቤኒዲክት ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ከአባ ቤኒዲክት ጋር በተገናኙበት ዓመት የአፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ልዩ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ኢኩሙኒካል እንግዳ በመሆን ንግግር አድርገዋል፡፡
       በጥር ወር 2ዐ12 ዓ.ም. በሌሎች አብያተ ክርስቲያናትና በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል ሃይማኖታዊ ውይይትን የሚያሳልጠው የጋራ ኮሚሽን ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በአባ ጳውሎስ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን እሳቸውም በዚያ ዓመት መጨረሻ ላይ በድንገት  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡" ይህ ዜና በቫቲካን ሬዲዮ የተደመጠው የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትረያርክ አባ ማትያስ ቫቲካንን የጐበኙበትን ቆይታ በሚመለከት ዘገባ ላይ የሮይተርስ የዜና መኪል ፊሊኘ ሀቼን ያቀረበው ነው፡፡
       በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት ከሮይተርስ የዜና ወኪል በተጨማሪ "ኤዥያን ኒውስ" በተሰኘ መጠሪያ የሚታወቀው የዜና ምንጭም በ 02/29/2016 ባቀረበው ዜና ላይ ከዚህ በታች የሠፈረውን አቅርቦ ነበር፡፡
 "በክርስቲያኖች መካከል በተለይም ደግሞ በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል መፈጠር ያለበት ህብረት እጅግ በጣም አፋጣኝና  አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ፖፕ ፍራንሲስ  በጥብቅ አሳሰቡ፡፡ ፓፓው ይህንን የተናገሩት ዛሬ ጠዋት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትረያርክ የሆኑትን አባ ማትያስን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡
ብጹዕነታቸው እንደተናገሩት፤ ¨…ከ2ዐዐ4 ዓም ጀምሮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በመካከላቸው  የተጠናከረ ሕብረት አንዲኖር የሚያስችላቸውን ምክክር ለማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይኽ ውይይት የሚካሄደው በዓለምአቀፋዊው የጋራ ኮሚሽን አማካይነት ነው፡፡ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሄደውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም የውይይት ተሳታፎ ስናወሳ ደስታ ይሰማናል፡፡ ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ከመረመራቸው መሠረታዊ ሃሳቦች መካከል በቤተ ክርስቲያን አንድነትና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው አንድነት ጋር አንድ መሆኑን አምኗል፡፡ በዚህ መሠረት የኮሚሽኑ አባላት አንድ እምነትን፣አንድ ጥምቀትን፣ አዳኝ ጌታ የሆነ አንድ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ረገድ ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌላቸው ተገንዝበዋል፡፡ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አካል በሚያደርገን በጥምቀት ጸጋ የተባበርን ሲሆን የበለጸገ ገዳማዊ ህይወትን በመከተል፣ ሥርዓተ ቅዳሴና እንዲሁም በሌሎች የጋራ ጉዳዮች የተነሳ በመካከላችን ህብረት አለ፡፡ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ የሆንን ወንድሞችና እህቶች ከመሆናችን በተጨማሪ ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያዋህዱን ጉዳዮች በልጠው ይታያሉ፡፡  ¨
       የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚገድባትን የብዙ ሺ ዘመናት ግዝት ጥሳ ሁለቱን ሃይማኖቶች በሚለዩአቸው መሠረታዊ የሃይማኖት ምሥጢሮች ላይ በርካታ ድርድርና ስምምነት ስታደረግ ጉዳዩ የቤተክርስቲያኒቱ ባለቤቶችና ባለመብቶች ለሆኑ ምእመናን ሳይገለጥ የተፈጸመ ከመሆኑ ባሻገር ቅድስቲቱን ቤተ ክርስቲያናችንን ከጠላቷ ከሊዮን ጫማ ሥራ የጣለ አልፎ ተርፎም ከፍተኛ የሃይማግት ነውጥና  ክህደት የተፈጸመበት ድርጊት ነው፡፡
ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ጥያቄ ከማንሳት አልፈው ቃለ ውግዘት እስከማሳለፍ ያደረሳቸው ጉዳይም ይኸው ሲሆን ምንም እንኳ በጊዜው ትኩረት ባይሰጠውም ዛሬ ላይ ግን በግልጽ አደባባይ የወጣ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡
አሁን ያለንበት ወቅት አገራችን ከነበረችበት የችግር አረንቋ ለማውጣት ሁሉን አቀፍ ርብርብ የሚደረግበት መሆኑን በተለያየ አቅጣጫ ከሚደረገው ርብርብ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
       በትክክለኛው የቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት ተመርጠው ቤተክርስቲያናችንን ሲያገለግሉ የነበረሩትና በወታደራዊው መንግሥት ዘመን በግፍ ከተገደሉት ሁለተኛው ፓትረያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከሥልጣን አንዲወርዱ ከተደረገ ግዜ ጀምሮ የተደረጉ የፓትረያርክነት ሹመቶች ከቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና ውጪ መሆናቸው እየታወቀ ጉዳዩን በድፍረት ተጋፍጠው መፍትሔ ማምጣት ይጠበቅባቸው የነበሩ ሁሉ ዝም ባሉበት ሰዓት ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ጉዳዩ ላይ ግምባር ቀደም ትግል አድርገዋል፡፡
       በተለይ የአራተኛውን ፓትረያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን ስደት ተከትሎ ቤተክርስቲያኒቱን ለሁለት ሲኖዶሶች የከፈለው ድርጊት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከሥልጣን ለማውረድ ከተደረገው የቀኖና ጥሰት ቀጥሎ የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ አቋም ያናወጠ ድርጊት ከመሆኑ ባሻገር በአንድ እረኛ ሊመራ ይገባው የነበረው መንጋ በየአቅጣጫው እንዲቅበዘበዝ መንገድ የከፈተ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥም ከፍተኛ ጥፋት የፈጠረ ድርጊት ነው፡፡
በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተፈጠረውን ዕርቅና አንድነት ተከትሎ በቅርቡ ከውጪ ከመጡት ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ እንደተናገሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ ለሁለት ተከፍሎ በነበረባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት የተፈጸመው መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ ዋጋ አልባ አንደነበረ በግልጽ የተናገሩት ሃቅ ሲሆን በአጠቃላይ ላለፉት አርባ አራት ዓመታትም ቤተከርስቲያን በከፍተኛ ችግር ላይ እንደነበረች በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡
       ከሁለተኛው ቅዱስ ፓትረያርክ ሕልፈት ወዲህ የተፈጸሙ የሃይማኖትና የቀኖና መዛነፍና ጥሰቶችን በዝርዝር ነቅሰው በማውጣት እንዲመከርባቸውና እውተኛ እርምትና ንስሐ አንዲወሰድባቸው በማሰብ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ጥቅምት 17 ቀን 1987 ዓም ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡት አቤቱታ ዛሬም ተግባራዊ መልስ የሚሻ ሲሆን እርሳቸው በአቤቱታቸው ላይ ካካተቷቸው የከፉ ሌሎች አሳዛኝ ድርጊቶችም በቤተ ክርስቲያን ስም መፈጸማቸው ሳይገታ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

እነዚህ አስከፊና አሳዛኝ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ባሉበት ሁኔታ የሚከናወኑ የታይታ ሥራዎች ሁሉ በእውነተኛ መመለስና ንስሐ እስካልተስተካከሉ ድረስ በቤተክርስቲያን፣ በአገርና በህዝብ ላይ እየደረሰ የለውን መከራ ማብቂያ እንደማይኖረው ግንዛቤ ተወስዶ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ በ1987 ዓም ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡት አቤቱታና በ1988 ዓም ያስተላለፉት ቃለ ግዝት ትኩረት ተሰጥቷቸው እርምት እንዲወሰድ ቤተ ክርስቲያንን በሚመራ በመንፈስ ቅዱስ ዳኝነት እንማጸናለን፡፡

No comments:

Post a Comment