Sunday, July 31, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል አስራ አንድ

ክፍል አስር የቀጠለ

የተወደዳችሁ አንባብያን!

አሁንም እንደተለመደው "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ እነሆ ብለናል፡፡
ሙሉ ዘገባው የ"ወልድ ዋሕድ" ክፍል ሃያ ስድስት ነው፡፡
     ለዛሬው “ጌታሁን ደምፀ” የተባሉት የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ መምህር ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጻፉትንና፤July 29 2016 በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበኑንን ትምህርት በጣም ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው ለእናንተ ለተዋህዶ ልጆች ማካፈል ስለፈለግን፤ ጽሁፉ ለንባብ እንዲመች ከማስተካከል በስተቀር በሃሳቡ ላይ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡ይህ ጽሁፍ አጭር ግን ትልቅ ትምህርት ሰጪ በመሆኑና በተለይም በነሐሴ አንድ ቀን የእመቤታችንን የእርገቷን መታሰቢያ ጾም ለመጀመር በተዘጋጀንበት ወቅት የተላለፈ መልእክት በመሆኑ ከወዲሁ እራሳችንን እንድናዘጋጅ የሚያበረታታ ነው፡፡ጾሙን በተገቢው መንገድ ጾመን ከእመቤታችን በረከት እንድናገኝ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

Thursday, July 7, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል አስር

ክፍል ዘጠኝ የቀጠለ
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች”

የተወደዳችሁ አንባብያን!

‹‹ን ዝም አልልም ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን›› በሚል በአራት ንዑሳን አርእስት ከፋፍለን ባቀረብነው አጭር ምላሽ፤የተሐድሶዎች የእምነት መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ከገለባ ቀሎ የተገኘ፤ከንቱ የማጭበርበሪያ ሰነድ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ እናምናለን፡፡በዚህ አጋጣሚ በነዚሁ አስመሳዮች (የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች) ከንቱ ስብከት ተወናብዳችሁ በየዋህነት እነሱን የምትከተሉ ሁሉ፤እባካችሁ የእግዚአብሔር ቃል መንፈስን ሁሉ መርምሩ እንጂ ዝም ብላችሁ አትመኑ ስለሚል ቆም ብላችሁ እንድታስቡና ወደ እውነተኛይቱ የተዋሕዶ ሃይማኖት እንድተመለሱ አጥብቀን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
አሁንም እንደተለመደው "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ እነሆ ብለናል፡፡
ሙሉ ዘገባው የ"ወልድ ዋሕድ" ነው፡፡

     ለዛሬው የምናቀርብላችሁ የ "ቅብአት" እምነትን በተመለከተ “መልካሙ በየነ” የተባሉ የተዋሕዶ ልጅ፤ ከእነዚሁ የ "ቅብአት"እምነት ተከታዮች ከሆኑት በአንዱ ለተዘጋጀ "ወልደ አብ" ለተባለው የክህደት መጸሐፍ የሰጡትን፤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡንን፤ በአስር ክፍሎች የተዘጋጀ ምላሽ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡
ውድ አንባብያን! ምንም ጽሁፉ ረዘም ያለ ቢሆንም፤ ዓላማው እውነቱን ከሐሰት ለመለየትና ሁሉም እራሱን ከስህተት ትምህርት ለመጠበቅ እንዲችል ለማድረግ ስለሆነ፤መምህሩ ለመጻፍ ያልደከሙትን እኛ ለማንበብ መድከም ስለሌለብን፤ በትዕግስትና በጥንቃቄ አንብበን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ በማለት እያሳሰብን ወደ ቀጣዩ ትምህርታዊ ምላሽ እንመራችኋለን፡፡

መልካም ንባብ!

Tuesday, June 28, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ዘጠኝ

ክፍል ስምንት የቀጠለ
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
"ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ! ክፉውን ነገር ተጸየፉት…"በሚለው አምላካዊ ቃል መሰረት፤ዝግጅቶቹ የእኛ ባይሆኑም፤ የዓላማ አንድነት እስካለን ድረስ፤በተለያዩ የተዋህዶ ልጆች የሚተላለፉትን፤የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ትምህርትና ወቅታዊ መልእክቶች፤ስናካፋላችሁ እንደነበር ታስታውሳላቸሁ፡፡
ለዛሬ "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን
"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!
በሚል ርዕስ ሦስተኛውንና አራተኛውን ክፍል እንድትመለከቱት እንጋብዛለን፡፡
መልካም ንባብ፡፡

Monday, June 13, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ስምንት

ክፍል ሰባት የቀጠለ
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
"ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ! ክፉውን ነገር ተጸየፉት…"በሚለው አምላካዊ ቃል መሰረት፤ዝግጅቶቹ የእኛ ባይሆኑም፤ የዓላማ አንድነት እስካለን ድረስ፤በተለያዩ የተዋህዶ ልጆች የሚተላለፉትን፤የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ትምህርትና ወቅታዊ መልእክቶች፤ስናካፋላችሁ እንደነበር ታስታውሳላቸሁ፡፡
ለዛሬ "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን
"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!
በሚል ርዕስ በሁለት ክፍል የቀረበውን ዘገባ እንድትመለከቱት እንጋብዛለን፡፡
መልካም ንባብ፡፡
ሙሉ ዘገባው "የወልድ ዋሕድ" ብሎግ ነው፡፡
"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!"
የተከበራችሁ የቅድስቲቱ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ልጆች!
ከዚህ በመቀጠል  ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››
በሚል ርዕስ ጥቂት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡
መልካም ንባብ!
     "ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ" እንዲሉ ከሃያ ሁለቱ ስነ ፍጥረት መካከል ቅዱሳን መላእክትና የስው ልጆች የተፈጠሩበት ዋነኛው ምክንያት ልዑል እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለዘላለምም ሕያዋን ሆነው እንዲኖሩ ነው፡፡በስነ ፍጥረት የመጀመሪያው ቀን ከተፈጠሩት ከመቶው ነገደ መላእክት መካከል በዚያን ጊዜ አለቃቸው የነበረው ሳጥናኤል ፈጣሪያቸሁ እኔ ነኝ ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡በዚያን ቅጽበት አንዱ ነገድ  አዎ! ፈጣሪያችን አንተ ነህ ብለው ሲቀበሉት ቀሪዎቹ ዘጠና ዘጠኙ ነገድ ለተወሰነ ጊዜ ቢታወኩም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ገብርኤል አረጋጊነት የፈጠራቸው አምላክ በብርሃን እስኪገለጥላቸው ድረስ ጸንተው ተገኝተዋል፡፡በመሆኑም ልዑል እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ /ለዘለዓለም/ ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እያሉ የሚያመሰግኑበት ጸጋ የተላበሱ ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ ሳጥናኤል ከነጭፍሮቹ በማስካድና በማሳሳት ሥራቸው እንደጸኑ ናቸው፡፡ የሰው ልጅንም ሁኔታ ስንመለከት ይህ ቀረሽ የማትባል ገነትን ያህል ቦታ እንዲያጣና ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያህል ጌታ እንዲለይ /በባሕርይው እንዲጎሰቁል/ ያደረገው ይኸው ጠላት ሳጥናኤል የጠነሰሰው ክፉ ምክር ነው፡፡
     ስለማይነገረው ስጦታው ስሙ ይመስገንና፤ይህንን የጠላታችንን ክፉ ምክር ለማፍረስ ሰውን ወዳጅ የሆነው ልዑል እግዚአብሔር እራሱ ሰው ሆኖ የኃጢአታችንን ዕዳ ባይከፍልልን ኖሮ ለዘላለም በገሃነመ እሳት በሳጥናኤል እጅ ስንቀጠቀጥና ስንቃጠል በኖርን ነበር! አሁንም በፍጥረታት ሁሉ አንደበት ስሙ ይክበር ከፍ ከፍም ይበልና! ጌታችን አምላካችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ጠላታችንን ሳጥናኤልን (ሰይጣንን፣ዲያብሎስን) በመስቀል ቀጥቅጦ ድል ካደረገው በኋላ፤ እኛም ክርስቲያኖች ፈጣሪያችን በሰጠን መሳሪያ፤ ማለትም በሃይማኖትና በመስቀሉ ኃይል ተጋድሏችንን እንድንፈጽም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሰጥቶናል፡፡ይህ ስጦታው ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን አምነው፤ሰይጣንን ክደው የሚኖሩት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡ስለሆነም እግዚአብሔርን ለማወቅ ህጉንም ለመጠበቅ ያልወደዱት ሁሉ በክህደትና በጥርጥር ማዕበል እየዋኙ፤ሌሎችንም ሲያስክዱና ሲያጠራጥሩ ይኖራሉ፡፡
     እንግዲህ የሐሰተኞችን የእውነተኞች ልዩነት ከዚያን ጊዜ /ከዓለመ መላእክት/ ጀምሮ እስከ ዛሬ አለ፤ ወደፊትም እስከ ምጽአት ድረስ ይኖራል፡፡የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች በሆኑትና የሳጥናኤል የግብር ልጆች በሆኑ ሰዎችም መካከልም ፈጽሞ ሊታረቅ የማይችል፤ የብርሃንና የጨለማ ያህል የሰፋ ልዩነት አለ፡፡ጠላት ዲያቢሎስም በዘመነ ብሉይ የአዳምን ልጆች በግድ ሲገዛቸው የኖረ ሲሆን፤ በዘመነ አዲስ ደግሞ ሰውን የሚገዛው እንደየ ሰው ዝንባሌ የተለያየ የማስመሰያ /የማታለያ/ ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስኪመስል ድረስ እራሱን ይለውጣል እንደተባለው፡፡
     የክርስትና መገለጫዎች ከሆኑት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው፤ ማንኛውም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በልቡ ያመነውን እውነተኛ እምነት በአማንያንም ሆነ በኢአማንያን ፊት ሳያፍርና ሳይፈራ መመሰከር እንዳለበት ጌታችን እራሱ  ‹‹ሰው በልቡ አምኖ በአፉ መስክሮ ይድናል፡፡››ሲል ተናገሯል፡፡በፍጻሜ ዘመን የተነሱት ሐሰተኞች መምህራን "የወንጌል" ሳይሆን "የወንጀል" ትምህርት ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡
     ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔርም "ሕጌንና ትእዛዜን ብትጠብቁ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤በመጨረሻም የዘላለምን ሕይወት ትወርሳላችሁ፤ ህጌን ባትጠብቁ ሰይፍ ይበላቸኋል፡፡" አለ አንጂ ማንንም ፍጡር አሰገድዶ እንዲያመልከው አላደረግም፡፡የጸጋው ግምጃ ቤት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከፈጣሪዋ በተቀበለችው ትእዛዝ መሰረት እምነቷንና ሥርዓቷን አምነው ለተቀበሉት ብቻ አስፈላጊውን አገልግሎት ትሰጣለች፡፡
     አንዳንዶቹ ዘባቾች ግን የኦርቶዶሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትን እየተቃወሙ፤ነገር ግን የዋሁን ምዕመን በለመደውና በሚወደው ነገር መስለው ለማሳሰትና ወደ ራሳቸው የጥፋት ዓላማ ለማስገባት ሲሉ የማያመኑበትን ሥርዓት ለይሰሙላ ብቻ ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ሆኖም ያዋጣናል ብለው የሄዱበት የማሳሳቻ መንገድ ሁሉ እንደፈለጉት ስላልሆነላቸውና ተስፋ ስለቆረጡ፤"እንግዲህ ምን ታመጣላችሁ"? ያሉ ይመስላል፤አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምደው እምነታችን ይህ ነው ብለው የእምነት መገለጫቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ይሁን እንጂ እንደማንኛውም የእምነት ድርጅት የራሳቸውን ቢሮና የአምልኮ ስፍራ ለይተው የወደዱትን ማድረግ ሲችሉ፤ዋናው አላማቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው እንክርዳድ ትምህርታቸውን በየዋሃኑ ምዕመናን ላይ መዝራት ስለሆነ ከላይ እስከ ታች ባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ክፍሎች ውስጥ ተሰግስገው ይገኛሉ፡፡እነዚህም ክፍሎች እራሳቸውን "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ" ብለው የሰየሙ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ናቸው፡፡ 
     ሰለ እኩይ ሥራቸው ለማስታወስ ያህል ይህንን ካልን፤ከዚህ በመቀጠል"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ" እና "አባ ሰላማ" በተባሉት  ድረ-ገጾቻቸው ላይ "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" ብለው ያወጡትን ባለ 43 ገጽ መገለጫቸውን፤የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ተገቢውን ምላሽ እስከሚሰጡ ድረስ፤ ለይሰሙም ቢሆን እናምንበታለን ብለው የሚፎክሩበትን 66ቱን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ምስክር በማድረግ የእምነት መገለጫቸው ይዘቱ ምን እንደሚመስል ከብዙው በጥቂቱ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
ለሁላችንም ጥበቡንና ማስተዋሉን ይስጠን፡፡
ለዛሬው እዚህ ላይ ይቆየን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንቀጥላለን፡፡

ክፍል ሁለት
"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል ሁለት)
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
     ሁላችንም የተዋህዶ ልጆች እንደምናውቀውና እኛም ይህንን የመወያያ መድረክ(ወልድ ዋሕድን)ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ለማስገንዘብ እንደሞከርነው፤ እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ›› ብለው የሚጠሩት መናፍቃን፤ኑፋቄያቸው ከተለያዩ የፕሮቴስታንት የእምነት ድርጅቶች የተውጣጣ መሆኑ እየታወቀ፤ ልክ ጠላታችን ሰይጣን ሰውን ለማሳሳት የብርሃን መልአክ መስሎ እንደሚታይ ሁሉ፤እነሱም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ለመምሰል የማያምኑበትን የተለያየ ሥርዓት ሲፈጸሙ ይታያሉ፡፡(በእምነት ለሚቀበሉት የሚያድን እሳት፤ሳያምኑበት ለሚቀበሉት የሚባላ እሳት የሆነውን ቅዱስ ቁርባንን በድፍረት እስከ መቀበል ድረስ!)
አሁን ወደ ጥንት ነገራችን ተመልሰን፤ ስለ "ተሐድሶ የእምነት መግለጫ" ቀጣዩን  ክፍል  እንዳስሳለን፡፡(ክፍል ሁለት)
     ቀደም ብለን በተደጋጋሚ እንደገለጽነው፤ የዚህ መልእክታችን ዋና ዓላማ እነዚህ ተኩላዎች የለበሱትን የበግ ለምድ ገፎ ተኩላነታቸውን ለማሳየት ያህል እንጂ እነርሱ ሥራ ፈትተው ሌላውን ሥራ ለማስፈታት ለጻፉት እርስ በርሱ ለሚጣረስ "መግለጫቸው"ለእያንዳንዱ አንቀጽ መልስ ለመስጠት ባለመሆኑ አለፍ አለፍ እያልን የተወሰኑትን ብቻ እንመለታለን፡፡

አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር እውነትን እንድናስተውል አእምሯችንን ያብራልን፡፡

የ"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" አጠቃላይ ይዘት፤

ሀ/ የእምነት መግለጫቸውን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለማስመሰል የተጠቀሙባቸው የማጭበርበሪያ ስልቶች፤
1/ በአሁኑ ዘመን ለቋንቋ ጥናትና ለምርምር ሥራ ካልሆነ በስተቀር ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውጪ የግዕዝ ቋንቋ የሚጠቀምበት እንደሌለ ማንም የማይክደው ሲሆን እነሱ ግን  ይህንን የግዕዝን ቋንቋ መጠቀማቸው አንዱ የዋሃንን የማደናገሪያ ስልት ነው፡፡
2/ "መክሥተ አርእስት" ብለው የጠቀሱት፦ጸሎተ ሃይማኖት፣አመክንዮ ዘሐዋርያት፣የተለያዩ ቅዱሳን አባቶች የሃይማኖት ውሳኔዎች፣የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት፣የቤ/ክ ታሪክ፣አዋልድ መጻሕፍት፣መጻሕፍተ ሊቃውንት፣ገድላት ድርሳናትና ተአምራት፣ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ነገረ ቅዱሳን፣ነገረ ማርያም፣…በማለት በአርእስትነት የተጠቀሙባቸው ቃላትና ክፍለ ትምህርቶች በሙሉ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ በስተቀር ተሐድሶን ጨምሮ በየትኛውም የእምነት ድርጅት የማይታመንባቸው መሆኑ እየታወቀ፤ እነሱ ግን ያው ዓላማቸው መስሎ ለማሳሳት ስለሆነ እነዚህን ቃላት ተጠቅመው ጽፈዋል፡፡ሆኖም በእያንዳንዱ ርእስ ሥር የሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ወደ ዝርዝሩ ስንገባ የምናየው ይሆናል፡፡
3/ ተሐድሶዎች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክንን እምነት፤ሥርዓትና ትውፊት እየተቃወሙ፤ነገር ግን "እናት ቤተ ክርስቲያናችን" እያሉ ስሟን ያለ አገባብ /ለማስመሰል/ እየጠቀሱ መጻፋቸው ነው፡፡
     እዚህ ላይ አንባቢ እንዲፈርድ፤ እነሱ በዚሁ የእምነት መግለጫቸውም ሆነ በየ ድረ-ገጾቻቸው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚሳደቡበትን አጸያፊ ቃላት መጥቀስ ይቻል ነበር፡፡እኛ ግን ለቤተ ክርስቲያናችን ክብር ስንል መጻፍ አንፈልግም፡፡ስድብን በተመለከተ በመጨረሻው ዘመን የሚነሱ አሳቾች በአውሬ በተመሰለው በዲያቢሎስ መንፈስ እየተመሩ እግዚአብሔርንና ማደሪያውን እንደሚሳደቡ በወንጌላዊው ዮሐንስ የተነገረውን ትንቢት በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 13 የተመዘገበውን ስንመለከት፤ተሐድሶዎቹ በገዛ እራሳቸው የዲያቢሎስ የግብር ልጆች መሆናቸውን መስክረዋል፡፡

ለ/ የእምነት መግለጫቸውን ያዘጋጁበት ምክንያት፦

ማስረጃ፦ ከሰነዳቸው ገጽ 11 መግቢያ የተወሰደ፦"በልዩ ልዩ ምክንያቶች በማንነት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው የተሐድሶ አገልግሎት አንዱ ጉድለትም ይህ ነው የሚባልና ወጥ የሆነ ኹሉም በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ የሚቀበሉት የእምነት መግለጫ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ይህንን ክፍተት ለመሙላት በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ይህንን የእምነት መግለጫና በዚያ ላይ የተመሰረተውን አስተምህሮና ሌሎች ከእንቅስቃሴው ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የያዟቸውን አቋሞች ያካተተውን ሰነድ ማዘጋጀት አስፈልጓቸዋል፡፡"
የተዋህዶ ልጆች እዚህ ላይ ልብ በሉልኝ!
ከዚህ በላይ በተመለከትነው የእምነት መግለጫቸው እንደገለጹት፦
1/ እነሱ ለእራሳቸው የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጥተው አእምሯቸው /አስተሳሰባቸው/ የተቃወሰባቸው መሆኑን እየነገሩን ነው፡፡ ታዲያ "እራሷ ክርስትና ሳትነሳ ልታቋቁም ሄደች" የሚለው ተረት  አይስማማቸውም?
2/ እንደነሱ አባባል፤ በማንነት ቀውስ ውስጥ ከሚገኘው የተሐድሶ  እንቅስቃሴ ከብዙ ጉድለቶቹና ክፍተቶቹ አንዱ የእምነት መግለጫ ያልነበረው መሆኑ ሲሆን፤ይህም የተዋህዶን ሃይማኖት ከማጥፋት በስተቀር  እውነተኛና ጠቃሚ መንፈሳዊ ትምህርት ይዘውና አቅደው እንዳልተነሱ ያረጋግጣል፡፡ለመሆኑ በራሱ ጉደለትና ክፍተት ያለበት "እምነት" ይዘው ነው ስንዱዋን እመቤት  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚቹት? በእውነቱ እራስን አለማወቅ ትልቅ ድንቁርና ነው!
3/ ከአሁን በፊት "ተሐድሶ የሚባል የለም እነ እንትና የፈጠሩት ወሬ ነው" ሲሉ እንዳልነበር፤ዛሬ ማጣፊያው ሲያጥራቸው የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን በራሳቸው አንደበት መናገራቸው፤ ከጥንቱም የድርጅታቸው መሠረቱ ሐሰት/ውሸት/ መሆኑንና ዓላማቸውም ከግብር አባታቸው ከሐሰት አባት ከዲያቢሎስ የተወረሰ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡
4/  "ኹሉም በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ …"የሚለው አባባል በመካከላቸው የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ነገር ግን እንደ ወንጌሉ ቃል እርስ በእርሱ የተለያየ መንግስት አይጸናም፡፡ 

ሐ/ እነዚህ የውስጥ መናፍቃን /ተሐድሶዎች/ ከነባሮቹም ሆነ በየጊዜው ከሚፈበረኩት የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ጋር ተባባሪ ስለመሆናቸው፤

ማስረጃ፦ ከሰነዳቸው ገጽ 5/የተወሰደ፦ "……ቤተ ክርስቲያን ራሷን በእግዚአብሔር ቃል እንድትመረምርና ከዚህ ሁኔታ ውስጥ እንድትወጣ በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጭም ልዩ ልዩ ተሐድሷዊ ጥሪዎች ሲተላለፉ ኖረዋል፡፡አሁንም እየተላለፉ ይገኛሉ፡፡በታሪክ ከሚጠቀሱት መካከልም በዋናነት ከውስጥ በአባ እስጢፋኖስና በደቀ መዛሙርቱ የተላለፈውን የተሐድሶ ጥሪ፤ ከውጭ ደግሞ በኢየሱሳውያን ቀርቦ የነበረውን ትችት መጥቀስ ይቻላል፡፡…"

ማስገንዘቢያ፤አንባብያን እዚህ ላይ ልብ እንበል!

1/ ከውስጥ በአባ እስጢፋኖስና በደቀ መዛሙርቱ የተላለፈውን የተሐድሶ ጥሪ መቀበል ነበረባት፤ ስላሉት
መልስ፦በብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ  ካልዕ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጸሐፍ ገጽ 49 እንዲህ ይነበባል፦
 "የቤተ ክርስቲያናችን ስነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብን ያስፋፉት፣አምልኮ ጣኦትን ከምድረ ኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋት የታገሉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ናቸው፡፡ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የነገሡት በ1444-1468 ዓ.ም ነው፡፡ከዚህም ሌላ በዘመናቸው ዜና መዋዕላቸው እንደሚለው ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል ስግደት አይገባም የሚሉ መናፍቃን እንደ ተነሱ ይጽፋል፡፡ይኸው ዜና መዋዕል እንደሚለው እነዚህን መናፍቃን ንጉሡ ባሉበት ሊቃውንቱ ተከራክረው ረቷቸው፡፡……"
 2/ከውጭ ደግሞ በኢየሱሳውያን የቀረበውን ትችት መቀበል ነበረባት፤ ፤ ስላሉት
መልስ፦በብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ  ካልዕ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጸሐፍ ገጽ 57-59 እንዲህ ይነበባል፦
"ኢየሱሳውያን የሚባሉት ካቶሊኮች ተንኮል ውስጥ ውስጡን ሲሔድ ቆይቶ በይፋ የተከሰተው በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡/1607-1632/ ጴጥሮስ ፓኤዝ እንደ አንድርያ ኦቢያዶ ግትር ሳይሆን በጣም ፈሊጠኛ ነበር፡፡የሀገሪቱን የአምልኮት ማቅረቢያ ቋንቋ ግዕዝ ተምሮ ይሰብክ፤ ይቀድስ ነበር፡፡ወደ ንጉሡ እየቀረበ የሮማ ካቶሊክን እምነት ቢቀበሉ የፖርቱጋል መንግሥት የጦር መሣሪያ ያስታጥቅዎታል እያለ ይሰብካቸው ነበር፡፡…ዐፄ ሱስንዮስ በ1622 ዓ.ም በጴጥሮስ ፓኤዝ እጅ ከነቤተሰቦቻቸው በሮማ ካቶሊክ ሥርዓት ተጠምቀው ካቶሊክነታቸውን አስታወቁ፡፡ (የኢ/ቤ/ክ ታሪክ ገጽ 57)…ዐፄ ሱስንዮስ በነገሡ በ27ኛው ዓመት ታመው አንደበታቸው ተዘጋ፤…የገዳማቸው መነኮሳት….ሦስት ሱባኤ በጸሎት በምህላ ቆይተው ጸበል አጠመቋቸው በዚህ ጊዜ የተዘጋ አንደበታቸው ተፈታ…፡፡" (የኢ/ቤ/ክ ታሪክ ገጽ 59)
     እንግዲህ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መቀበል ነበረባት እያሉ እንደ አብነት የጠቀሷቸው ከላይ የተመለከትናቸውን "ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል ስግደት አይገባም" ይሉ የነበሩትን የውስጥ መናፍቃን ደቂቀ እስጢፋን/እስጢፋኖስን/፤ ከውጭ ደግሞ ኢየሱሳውያን የተባሉትን የካቶሊክ መልክተኞችን ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን አገርንም ጭምር ለማጥፋት የተሰለፉ ነበሩ፡፡እንግዲህ የዛሬዎቹ "ወንጌላውያን" ነን ባዮች /ተሐድሶዎች/ በጥቂቱ 500 አመታትን ያስቆጠረውን፤ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ኩራት፤ለመናፍቃን እፍረት፤የሆነውንና በዚያን ጊዜ ቅዱሳን አባቶች በቂ መልስ ሰጥተውና በእግዚአብሔር ቃል እረትተዋቸው የዘጉትን ታሪክ እያስታወሱ፤ አሁንም በድፍረት ይህንኑ የጥፋት መልእክት ተቀበሉ እያሉ የሚወተውቱት፤ እውነትም በማንነት ቀውስ ውስጥ ቢሆኑ አይደል እንዴ?
ሌላው ቢቀር!
1/ ዐፄ ሱስንዮስ በካቶሊክ ሥርዓት ሲጠመቁና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን ሲያውጁ አንደበታቸውን የዘጋውን፤
2/ ተጸጽተው ንስሃ ሲገቡ ደግሞ በአባቶች ጸሎትና በጸበል ተጠምቀው ወደ ቀደመ ጤንነታቸው የመለሳቸውን፤
3/ በዚህም የተዋህዶ ቤ/ክ በእግዚአብሔር ወልድ ደም የተመሰረተች በመሆኗ ያረጋገጠበትን፤
4/ በአጠቃላይ ከዚችው ከአንዲቱ ተዋህዶ በስተቀር ሌላው ሁሉ ከንቱ መሆኑ፤/በክርስትናው ዓለም ውጭ ያሉትን አይጨምርም/

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በድንቅ  ተአምራት የመሰከረውን እውነት መቀበል አለመቻላቸው፤ አይነ ህሊናቸው የታወረና "እምነት" ብለው የያዙትም መንገድ/ተሐድሶ/ ከእውነት የራቀ ለመሆኑ ሌላ ምስክር አያሰፈልገውም፡፡

ውድ አንባብያን! የተሐድሶ ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም ገና ብዙ አስቂኝ ነገር አለ፡፡!

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ እንቀጥላለን፡፡

እናንተም ከጾምና ከጸሎት ጋር በትዕግስት ጠብቁን፡፡

"ንቁ ! በሃይማኖት ቁሙ!"

የዘወትር መልእክታችን  ነው፡፡!







Saturday, June 11, 2016

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1

ክፍል ሰባት
ክፍል ስድስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
     ይህንን "እምነ ጽዮን" ብለን የሰየምነውን የመወያያ መድረክ ስንጀምር “ጆሮ ያለው መሰማትን ይስማ”  በሚል ርዕስ ፤በአራት ተከታታይ ክፍሎች፤ እንዲሁም "ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ"በሚለው ርዕስ በስድስት ተከታታይ ክፍሎች፤ ባቀረብነው ጽሁፍ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን በበላይነት የሚመሩት ክፍሎች እያደረሱ ያለውን ጥፋት በማሳየት ከእኛስ ምን ይጠበቃል በሚል ማጠቃለያ ሰፊ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡አንባብያን ሀሳቡን በጥሞና እንድትከታተሉት በማሰብና ዛሬ ለምንወያይበት ርዕስም አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው "ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ"በሚለው ርዕስ በክፍል አራት ያቀረብነው ጥሁፍ እንዳለ አምጥተነዋል፡፡

Sunday, March 6, 2016

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1 ክፍል ስድስት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

"ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" ሉቃስ 16፤13
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች!
እንደምን ሰነበታችሁ?
ን ዝም አልልም ” በሚለው ርዕስ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ክፍሎች በቅድስት ቤ/ክ ውስጥና በዙሪያዋ በማንኛውም ሁኔታ የሚከናወነው ንግድ የተወገዘ እንደሆነ የጌታችንን ወንጌል መሰረት አድርገን ብዙ ተማምረናል፡፡እንዲሁም በክፍል አራትና አምስት ደግሞ ይኸው አላስፈላጊ የቤተ ክርስቲያን የንግድ ሥራ እያስከተለ ያለውን ችግር በማስመልከት ‹‹ሐራ ዘተዋህዶ›› ከተባለው ድረ ገጽ ያገኘነውን ጽሁፍ ተመልክታችሁ ስለ ችግሩ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ "ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" በሚል ርዕስ እንማማራለን፡፡ 
መልካም ንባብ!

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1 ክፍል አምስት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
       
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
“ስን ዝም አልልም ” በሚለው ርዕስ በክፍል አራት‹‹ሐራ ዘተዋሕዶ›› ከተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡አሁንም የዚያኑ ጽሁፍ ተከታዩን ክፍል እድታነቡ እየጋበዝን፤የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ፤ይህንን የቤተ ክርስቲያን ችግር አውቀን፤ ከእኛ ምን ይጠበቃል? ብለን ወደ መፍትሄ የሚያደርሰንን መንገድ እንድንቀይስ እንጂ ችግሩን ብቻ እያወራን እንድንኖር አይደለም፡፡ስለሆነም ጉዳዩ ይመለከተኛል የምንል ሁላችን የእናታችን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋ፣ሥርዓቷና ትውፊቷ እንዲሁም ሀብትና ንብረቷ በአግባቡ ተጠብቆ ከአባቶቻችን በተረከብንበት ሁኔታ፤ እኛም ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ አለብን፡፡ስለዚህ ማንኛውም መንፈሳዊ ሥራ በእኛ ጥረት ብቻ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል፤በጾምና  በጸሎት ፈቃደ እግዚአብሔርን ከመማጸን ጋር አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ የምንነሳበት ጊዜው አሁን መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የመናፍቃን፤የሌቦችና የወንበዴዎቸ ዋሻ ከመሆን ይጠብቅልን፡፡
መልካም ንባብ!