Sunday, July 31, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል አስራ አንድ

ክፍል አስር የቀጠለ

የተወደዳችሁ አንባብያን!

አሁንም እንደተለመደው "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ እነሆ ብለናል፡፡
ሙሉ ዘገባው የ"ወልድ ዋሕድ" ክፍል ሃያ ስድስት ነው፡፡
     ለዛሬው “ጌታሁን ደምፀ” የተባሉት የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ መምህር ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጻፉትንና፤July 29 2016 በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበኑንን ትምህርት በጣም ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው ለእናንተ ለተዋህዶ ልጆች ማካፈል ስለፈለግን፤ ጽሁፉ ለንባብ እንዲመች ከማስተካከል በስተቀር በሃሳቡ ላይ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡ይህ ጽሁፍ አጭር ግን ትልቅ ትምህርት ሰጪ በመሆኑና በተለይም በነሐሴ አንድ ቀን የእመቤታችንን የእርገቷን መታሰቢያ ጾም ለመጀመር በተዘጋጀንበት ወቅት የተላለፈ መልእክት በመሆኑ ከወዲሁ እራሳችንን እንድናዘጋጅ የሚያበረታታ ነው፡፡ጾሙን በተገቢው መንገድ ጾመን ከእመቤታችን በረከት እንድናገኝ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡


ከዚህ በታች ያለው ጽሁፍ የመምህር ጌታሁን ደምፀ ነው፡፡

መልካም ንባብ!

     በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ቅዱሳን አበውና መላው ሕዝበ ክርስቲያን ከሚጸልዩአቸውና አምልኮታቸውን ከሚፈጽሙባቸው የጸሎት መጻሕፍት ውስጥ ቀዳሚና ተወዳጅ የሆኑት ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ናቸው። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ያሉ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር እንዲታረቁ በረከተ ሥጋና በረከተ ነፍስን እንዲያገኙ ምክንያት የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ናትና። ስለሆነም እርሷን ሳይማፀን ክብር ያገኘ በፈጣሪው ዘንድ ባለሟልነትን የተቀበለ ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ጻድቅ፣ ሰማዕት እንዲሁም ምእመን የለም። ይህንን አባ ጽጌ ድንግል በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ አልቦ ጸሎት ወአልቦ ትንባሌ እንበሌኪ ማርያም ዘየዐርግ ሉዐሌ እመቤቴ! ያለአንቺ እውቅና ያለአንቺ ምልጃ ወደ እግዚአብሔር የሚያርግ ልመናና ጸሎት ዕጣንና ቁርባን የለም በማለት ያለ እመቤታችን የሚያርግ ጸሎት አለመኖሩን ተናግሯል፤ በዚሁ መሠረት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ሳይጸልዩ ሰአሊ ለነ ቅድስት ሳይሉ አይውሉም አያድሩም።
     እመቤታችንም በፍቅሯ ለሚቃጠሉና በቃል ኪዳኗ ለሚታመኑ ሁሉ ምሕረትና ይቅርታ ጸጋና በረከት ለማጎናጸፍ ዘወትር የተዘጋጀች ናት። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል ብላ እንደተናገረችው ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት ብፅዕት እያሉ ሲያመሰግንዋት ኖረዋል ወደ ፊትም ይኖራሉ።ይኸውም እመቤታችን ብፅዕት የመባልዋን ምክንያት ቀጥላ ተናግራለች እስመ ገብረ ሊተ ኃይለ ዐቢያተ በእኔ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቷልና ትውልድ ሁሉ ብፅዕት እያሉ ያመሰግኑኛል ስትል ከነምክንያቱ ነግራናለች። ደግሞም እርሷ ባትነግረንም በእርሷ ምክንያት ያገኘነው ድኅነትና የተቀበልነው በረከት ምስክር ነው፤ ስለዚህ ፍጥረት ሁሉ እናታችን ቢላት ትበዛበት ይሆናል እንጂ አታንስበትም የፍጥረት ሁሉ ጌታ እግዚአብሔር እናት አድርጓታልና። ምንም እንኳን ከኃጢአት ባንነጻም በንስሐ እየታገዝን ከእርሷ በነሣው ደም የከፈተልን የሕይወት በር እንዳይዘጋብን ስለእናቱ ብሎ ይቅር እንዲለን ለእርሱ በእናትነት እርሷ ስለምትቀርበው ቅድስት ሆይ ለምኝልን እያልን እንድናመሰግናትና እንድንማፀናት ክርስቲያናዊ ግዴታ አለብን። ምክንያቱም ከድንግል ማርያም በቀር ማንኛውም ፍጥረት ያለተጓዳኝ ተፈጥሮ የኖረ የለም።ለመልአኩ መልአክ አምሳያ፣ ለጻድቁ ጻድቅ አምሳያ፣ ለሰማዕቱ ሰማዕት አምሳያ፣ ለነቢዩ ነቢይ አምሳያ፣ ለሐዋርያው ሐዋርያ አምሳያ የክብርና የቅድስና ባልደረባ አላቸው፤ እመቤታችን ግን ልክ ምትክ አቻ አምሳያ የሌላት፤ የክብርም ሆነ የቅድስና ባልደረባ የማይገኝላት ብቸኛ ፍጥረት መሆኗ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። ድንግልናዋም ሆነ ቅድስናዋ ከመነገር በላይ ነው።እንዲህ ያለች እናት ስለሆነች በኢትዮጵያ ምድር የወላዲተ አምላክ የከበረ ስም የማይጠራበት ክፍለ ሀገር ቀርቶ ቀበሌ የለም፤ ዛሬ በስሟ የታነጹ ገዳማትና አድባራት በጋና ክረምት መዓልትና ሌሊት ማኅሌተ እግዚአብሔር፣ ቅዳሴና መዝሙር ሳይጓደልባቸው እንደ ብሔረ መላእክት የምስጋና ቦታ ሆነው ይኖራሉ፤ ስለ እመቤታችን ስለ ድንግል ማርያም የተደረገው ድንቅ ምሥጢር ሁሉ ቢጻፍ ሰማይና ምድር እንደ ብራና፤ ባሕርና ውቅያኖስ እንደ ቀለም፤ መላእክትና የሰው ልጆች እንደ ጸሐፍት ሆነው ቢጻፍ ባልበቃ ነበር።
     በአጠቃላይ ክርስቶስና ሥራዎቹ ያለእርሷ ሕይወት የማይነገር መሆኑ ለክርስቲያኖች ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም በበሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ለተነሡ ቅዱሳን አበውና ቅዱሳት አንስት የታሪክና የድኅነት መሠረታቸው እመቤታችን ናትና። በአልቃሻው ዓለም የደስታ መፍሰሻ፣ በጨለማው ዓለም የብርሃን መፍሰሻ፣ ሙት በሆነው ዓለም የሕይወት መፍሰሻ፣ በኃጢአተኛው ዓለም የጽድቅ መፍሰሻ አድርጓታልና፤ ስለዚህ በየዘመኑ የተነሡ ቅዱሳን የእመቤቴ ምስጋና በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግቤው እንደ ውኃ ጠጥቼው እንደ ልብስ ተጎናጽፌው እያሉ ተመኝተዋል ምኞታቸውም ተፈጽሞላቸው ስለ እመቤታችን ዘምረዋል፣ ተቀኝተዋል፣ ጽፈዋል፣ አመሥጥረዋል፣ ተርጉመዋል ከእነዚህም ውስጥ ቅዱስ ኤፍሬምና ቅዱስ ሕርያቆስ ይገኙበታል። ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤታችን ምስጋና ይበዛለት ዘንድ አጥብቆ ይማፀን ነበርና መንፈስ ቅዱስ የተመኘውን መልካም ምኞት ፈጽሞለት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ስለ እመቤታችን ብቻ አሥራ አራት ሺህ ድርሰት ደርሷል። ዛሬ የእመቤታችን ምስጋና በዝቷል ለሚሉ መናፍቃን ትልቅ ትምህርት ነው ምክንያቱም ቅዱሳን ምስጋናዋን አልጠግብ እያሉ ሁልጊዜም አዲስ እየሆነባቸው በምስጋናዋ ባሕር ሲዋኙ ያልታደሉ መናፍቃን ግን በዛባት እያሉ ለመናገር የሚያጸይፍ ለመስማት የሚቀፍ ነገር ይናገራሉ ልቡና ይስጣቸው። ቅዱስ ኤፍሬም ግን ያንን ሁሉ ድርሰት ጽፎ በመጨረሻ የእመቤታችን ምስጋና የላይና የታች ከንፈር ባለው በዚህ በሥጋ አንደበት ተነግሮ በሥጋ እጅ ተጽፎ እንደ ማያልቅ በድርሰቱ ላይ አስፍሮታል።
     ቅዱስ ኤፍሬም ከደረሳቸው ድርስቶቹ አንዱ ውዳሴ ማርያም ነው። ውዳሴ ማርያም ምሥጢሩ የረቀቀ የጸሎቱ ኃይል የመጠቀ የጸሎቶች ሁሉ እምብርት ነው፤ ምክንያቱም ስሙ ውዳሴ ማርያም ይባል እንጂ ከጸሎቱ ባሻገር የምሥጢሩ ይዘት በአብዛኛው ስለ ምሥጢረ ሥጋዌና ስለ ምሥጢረ ሥላሴ አጉልቶ የሚያስረዳ ረቂቅና ምጡቅ የሆነ የጸሎትና የትምህርት መጽሐፍ ነው። ሶርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም በርቱዕ አንደበቱ ወንጌልን ሰብኳል፤ አምልኮተ እግዚአብሔርን አስፋፍቷል፤በቅዱሳት እጆቹ በርካታ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጽፏል፤ በእግሮቹ እየተዘዋወረ ምእመናን እያሳመነ አጥምቋል፤ ባጠቃላይ በመላው ሕዋሳቱ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ ታላቅ ሊቅ ነው።ቅዱስ ኤፍሬም በጾምና በጸሎት፣ በምናኔና በትኅርምት፣በወንጌል አገልግሎት እየተጋደለ ከኖረ በኋላ ሐምሌ አሥራ አምስት ቀን ከዚህ ዓለም በክብር ዐርፏል።በመቀጠልም አባ ሕርያቆስም ተምኔቱ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም በመሆኑ የእመቤታችን ምስጋና ይበዛለት ዘንድ አብዝቶ ይጸልይ ነበርና መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ከቅዳሴዎች መካከል በምስጢሩና በጸሎቱ ተወዳዳሪ የሌለውን ቅዳሴ ማርያምን ደርሷል። አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም አምስቱን አዕማደ ምሥጢር በሚገባ በምሳሌ እያስረዳ ለጆሮ የሚጥም ለአንደበት የሚጣፍጥ የማይጠገብ የማያልቅ የመለኮት ስንቅ፤ ያልተገራ የመናፍቃንን አንደበት የሚዘጋ የምዕመናንን ልቡና የሚያጸና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና በረከት የተሞላ ድርሰት አብርክቶልናል።የብሕንሳው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ሕርያቆስ ብዙ ድርሳን ደርሷል ብዙ ተግሣጽ ጽፏል እንደ ቅዱስ ኤፍሬም በጾምና በጸሎት በምናኔና በትኅርምት በወንጌል አገልግሎት እየተጋደለ ከኖረ በኋላ ጥቅምት ሁለት ቀን ከዚህ ዓለም በክብር ዐርፏል።
     ስለሆነም ውዳሴ ማርያምንና ቅዳሴ ማርያምን የጸለዩ አባቶች ከፍ ያለ ክብርና ከፈጣሪያቸው ዘንድ ባለሟልነትን ተቀብለውበታል። እኛም በጸሎቱ ተጠቅመን ከሰይጣን ሥራ ከሥጋ ፈተና ተጠብቀንበት በአምላካችን ዘንድ ክብር እንድናገኝ ያድርገን፤ ለቅዱስ ኤፍሬምና ለቅዱስ ሕርያቆስ የገለጠች እመቤት ለእኛም ጥበቡን ማስተዋሉን ትግለጥልን፤ ከነዚህ ቅዱሳን በረከት ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን።

ለመምህር ጌታሁን ደምፀ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

ይቆየን፡፡

ለቀጣዩ በሌላ ርዕስ በሰላም ያገናኘን፡፡


No comments:

Post a Comment