Thursday, July 7, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል አስር

ክፍል ዘጠኝ የቀጠለ
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች”

የተወደዳችሁ አንባብያን!

‹‹ን ዝም አልልም ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን›› በሚል በአራት ንዑሳን አርእስት ከፋፍለን ባቀረብነው አጭር ምላሽ፤የተሐድሶዎች የእምነት መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ከገለባ ቀሎ የተገኘ፤ከንቱ የማጭበርበሪያ ሰነድ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ እናምናለን፡፡በዚህ አጋጣሚ በነዚሁ አስመሳዮች (የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች) ከንቱ ስብከት ተወናብዳችሁ በየዋህነት እነሱን የምትከተሉ ሁሉ፤እባካችሁ የእግዚአብሔር ቃል መንፈስን ሁሉ መርምሩ እንጂ ዝም ብላችሁ አትመኑ ስለሚል ቆም ብላችሁ እንድታስቡና ወደ እውነተኛይቱ የተዋሕዶ ሃይማኖት እንድተመለሱ አጥብቀን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
አሁንም እንደተለመደው "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ እነሆ ብለናል፡፡
ሙሉ ዘገባው የ"ወልድ ዋሕድ" ነው፡፡

     ለዛሬው የምናቀርብላችሁ የ "ቅብአት" እምነትን በተመለከተ “መልካሙ በየነ” የተባሉ የተዋሕዶ ልጅ፤ ከእነዚሁ የ "ቅብአት"እምነት ተከታዮች ከሆኑት በአንዱ ለተዘጋጀ "ወልደ አብ" ለተባለው የክህደት መጸሐፍ የሰጡትን፤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡንን፤ በአስር ክፍሎች የተዘጋጀ ምላሽ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡
ውድ አንባብያን! ምንም ጽሁፉ ረዘም ያለ ቢሆንም፤ ዓላማው እውነቱን ከሐሰት ለመለየትና ሁሉም እራሱን ከስህተት ትምህርት ለመጠበቅ እንዲችል ለማድረግ ስለሆነ፤መምህሩ ለመጻፍ ያልደከሙትን እኛ ለማንበብ መድከም ስለሌለብን፤ በትዕግስትና በጥንቃቄ አንብበን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ በማለት እያሳሰብን ወደ ቀጣዩ ትምህርታዊ ምላሽ እንመራችኋለን፡፡

መልካም ንባብ!

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 1
© መልካሙ በየነ
ሰኔ 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ለሁሉ እንዲዳረስ በመጀመሪያ አንብቡት ስትጨርሱ ደግሞ
===SHARE===LIKE===COMMENT ማድረግ አትዘንጉ፡፡
እንኳን ለጾመ ሐዋርያት በሰላም እና በፍቅር አደረሳችሁ
አደረሰን!
     ዛሬ ዛሬ ማንነታቸውን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ትምህርታቸውንም ከኩሽና ቤት ወደ አደባባይ አውጥተውታል፡፡ በግልጽ ማስተማር መከራከር ጀምረዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን መሳደብ መንቀፍ ጀምረዋል፡፡ መናፍቃኑ! እነዚህን ልዩ የሚያደርጋቸው በቤተክርስቲያናችን ጥላ ሥር ተጠልለው ከበላነው በልተው ከጠጣነው ጠጥተው እኛ በሠራነው ሥርዓት ተሠርተው ለእኛ በተሾመልን ጳጳስ ደቁነው ቀስሰው ጰጵሰው የሚገኙ መሆናቸው  ነው፡፡ በብዛት ሰፍረው የሚገኙት ደግሞ በጎጃም ጥቂት አካባቢዎች ውስጥ ነው፡፡ከዚህ በፊት አስተምህሯቸው በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ተከታዮቹም የእናት እና የአባቴ እምነት ነው ብለው ክርር ከማለት ባለፈ ምሥጢራትን አያውቁም ነበር፡፡ የየዋሃኑም መከራከሪያ ሆኖ የቆየው የጌታችን የልደት በዓል ቀን በ28 እና በ29 ይከበራል ወይስ ደግሞ በ29 ብቻ ይከበራል የሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ስለነበር ለብዙዎቹ ልዩነት ያለን በ4 ዓመት አንድ ቀን ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለአጽዋማት የሚያውቁት ደግሞ በጾመ ነቢያት እና በጾመ ሐዋርያት መግቢያ ላይ ብቻ ያለ ልዩነት አድርገው ይቆጥሩት ስለነበር በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚፈጠር የአጿጿም ችግር ይመስላቸው ነበር፡፡
     ዛሬ ግን ሊደበቅ የማይችል በምንም በማንም ሊሸፈንና ሊከለል የማይችል አደባባይ ላይ የወጣ ምንፍቅና ቅ--ብ---አ---ት፡፡ዛሬ ላይ በልደት በዓልና በአጽዋማት መግቢያ ላይ የምንከራከርብት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ አድርጉ ፈጽሙ በተባልንበት ቀን የምናደርጋቸው በተከለከልንባቸው ቀናት ደግሞ የምንቆጠብባቸው የምንታቀብባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ እንድናደርግ ወይም እንዳናደርግ ቤተክርስቲያናችን ስልጣንና ኃላፊነት የሰጠችው አካል አለ እርሱም ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ልደትን በታህሳስ 28 ማክበራችን አያጣላንም ምክንያቱም እንኳን ምሥጢር እያለው ይቅርና መስከረም 1 ወይም ጥቅምት 30 ወይም ደግሞ ሰኔ 24 ወይም ሚያዝያ 7 ወይም ደስ ያላችሁን ቀን መርጣችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ ብንባል ኖሮም እናደርገው ነበር እናከብረውም ነበር፡፡ ጌታችን በየዓመቱ የሚወለድ ሆኖ ነው እንዴ እያከበርነው ያለነው? አይደለም፡፡ የአጽዋማት መግቢያም እንዲሁ ነው፡፡ የነቢያት ጾም በህዳር 15 የሐዋርያት ጾም ደግሞ ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በነጋታው ሰኞ እንድንጀምር ሥርዓት ተሠራልን በዚያ ሥርዓት እንመራለን እንተዳደራለን፡፡ አለቀ፡፡ ይህ ምንም አያከራክርም ምክንያቱም ቀኖና ስለሆነ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቀደሙ አባቶቻችን እና ከመጽሐፎቻቸው ጋር በማይጣላ መልኩ አድርገው በወሰኑልን ውሳኔ የምንፈጽመው ነው፡፡ እነዚህ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች የሚጠቅሱት ነገር አለ “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ወደ ኋላ ከተመለሰ ጥምቀት ግዝረት ለምን አንድ ቀን ወደኋላ አይመለሱም” የሚል ነው፡፡ የእነርሱ ደጋፊ የሆኑት ጳጳስም “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ቀንሶ በታህሳስ 28 ይከበር የምትሉ እናንተ ልደታችሁን ስታከብሩ አንድ ቀን ቀንሳችሁ ነውን? ታህሳስ 29 የተወለደ ሰው በዘመነ ዮሐንስ ልደቱን ታህሳስ 28 ያከብራልን?” ብለዋል፡፡ መልካም ነው! እኔ ግን ግርም ድንቅ የሚለኝ ነገር አለ፡፡ አሰቀድሜ እንደተናገርኩት ይህ የቀኖና ጉዳይ ነው ይህን መፍታት የሚችል ራሱን የቻለ አካል አለው፡፡ አይደለም ታህሳስ 28 ከ365ቱ ቀናት መካከል አንዱን ቀን መርጠው የጌታችን ልደት በዚህ ቀን ይከበር ብለው ካሉን ግዴታችን ነውና እናከብረዋለን፡፡ምክንያቱም የጌታችን ስቅለት፤ ትንሣኤ እና ዕርገት በጥንተ ስቅለት፣ በጥንተ ትንሣኤ እና በጥንተ ዕርገት እያከበርናቸው ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የ2008 ዓ.ምን ስቅለት፣ትንሣኤና ዕርገት ቀን አስቡት፡፡ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ነው እኛ ግን ስቅለቱን ሚያዝያ 21 ትንሣኤውን ሚያዝያ 23 እንዲሁም ዕርገቱን ሰኔ 2 ቀን አከበርን ለምን? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ታዲያ በአንድ የልደት ቀን አከባበር ላይ ከምንነታረክ ለምን እነዚህንስ አንከራከርባቸውም፡፡ ስለዚህ በልደት በዓል አከባበርና በአጽዋማት መግቢያ ላይ ምንም መከራከሪያ ልናነሣ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም እኛ ታዛዦች እንጅ አዛዦች አይደለንምና አድርጉ በተባልነው ቀን ማድረግ ብቻ ነው ሥራችን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለቅብአት ምንፍቅና የመደበቂያ ካባዎች እንጅ መሠረታዊ ነጥቦች አይደሉም፡፡ህዝበ ክርስቲያኑም ማስተዋል የሚገባው ይህንን ጉዳይ ነው፡፡ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት አስተምህሮ ላይ ወይም ዶግማ ላይ ነው፡፡ ዶግማን ማሻሻል የሚችል አካል የለም፡፡ ምክንያቱም ስታምን የምትቆይበት ካላመንክ ደግሞ ተለይተህ የምትወጣበት መሠረተ እምነት ነውና፡፡ ለሲኖዶስ ቀኖናን የማሻሻልም የመለወጥም የመቀየርም ስልጣን አለው ለዶግማ ግን ማንም ቅንጣት ታህል የማሻሻል የመለወጥ የመቀየር ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡
     ስለዚህ መሠረታዊ ነጥቦቻችን መከራከሪያዎቻችን መሆን ያለባቸው አስተምህሮ ላይ ነው፡፡አስተምህሯቸውን ደግሞ በራሳቸው ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እናገኘዋለን፡፡ ያ አስተምህሮ በእውነት እኛ የተዋሕዶ አማኞች የምንከተለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው ስለሚሆን ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ እንደ መከራከሪያ አድርጋችሁ ጊዜ እንዳታጠፉ እጠይቃለሁ፡፡ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆችም ሳትቸኩሉ በማስተዋል ለስድብ ሳትፈጥኑ ራሳችሁን በመመርመር ስህተቶቻችንን እየተማማርን እንድንቀጥል አሳስባችኋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል…
 “የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 2
ሰኔ 14/2008 ዓ.ም
      በክፍል 1 የቅብአት ምንፍቅና የተደበቀባቸውን ሁለት ጉዳዮች አንሥተን ተመልክተናል፡፡ የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበርና የአጽዋማት መግቢያ ላይ በሰፊው ለማየት ሞክረናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና በመሆናቸው የቀደሙ አባቶቻችን በሰሩልን በቀየሱልን በሄዱበት በተመሩበት መንገድ ብቻ መጓዝ እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ ይህንን ማንሣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ልዩነታችንን የቀኖና ብቻ በማስመሰል ህዝበ ክርስቲያኑን በማታለል ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቀኖና ጉዳይ ላይ በቤተክርስቲያናችን የሥልጣን እርከን የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የቀደሙ አባቶቻችን ባቆዩን መልኩ እንድንቀጥል በወሰነልን መንገድ እንሄዳለን፡፡ በመሆኑም ቀድሞ በነበረው ሥርዓት ወደፊትም እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡
     በዚህ ክፍል የምንመለከተው መጻሕፍትን አብነት አድርገን እንከራከራለን በሚሉት የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ዙሪያ ነው፡፡ መጻሕፍትን እንደፈለግነው መተርጎም አንችልም፡፡ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” የሐዋ 8÷31 ማለት ያስፈልገናል፡፡ ጃንደረባው ፊደል ያልተማረ ሆኖ አይደለም ተምሯል የሚያነበው የመጽሐፍ ምሥጢር ግን ፊደላትን ከማወቅ በላይ ነውና ይህንን ቃል ተናገረ፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን እንዴት እንደሚተረጎም ሳንረዳ ምክንያተ ጽሕፈቱን ሳናውቅ የመጻሕፍት ቃላትን እንዲህ ማለት ነው ብለን መተርጎም አንችልም፡፡ የቅብአት እምነት አራማጆች ሙሉ ጊዜያቸውን ያቃጠሉት ጉባኤ ቤት በመማር አልያም ሊቃውንቱን በመጠየቅ ወይም ትርጓሜውን በማመስጠር አይደለም ፕሮቴስታንቶች ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ለማለት “አማለደ”፤ “ለመነ” ፣“አስታረቀ” ወዘተ የሚሉትን ቃላት ፍለጋ እንደደከሙ ሁሉ የቅብአት እምነት አራማጆችም “ቅብአት”፣ “ተቀባ”፤ “ቀባ”፣ “ቀባው”፣“አስቀባው” ወዘተ እና የመሳሰሉትን ከ “ቀ” እና ከ “በ” ፊደላት የተጣመሩ ቃላትን ፍለጋ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የቃሉን ትርጉም ሳይመለከቱ “እዚህ ቦታ ላይ ቀባው ይላል” ፣ “እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቀባው ይላል” ወዘተ እያሉ ራሳቸውን እያታለሉ የሚገኙት፡፡ የሚጠቅሱት ጥቅስ ደግሞ ከ“አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝ መዝገበ ቃላት” ወይም ደግሞ ከ “ገብረ መድኅን እንዳለውን የኑፋቄ መጽሐፍ ወልደ አብ” ብቻ ነው፡፡ አንድምታቸው “ወልደ አብ” ማብራሪያቸው ደግሞ “መዝገበ ቃላት” ነው፡፡ በእውነት እንደ ሰው ማሰብ ከቻልን ለመሠረተ እምነት የአንድ ሰው መጽሐፍ ያውም የቋንቋ ማስተማሪያ መዝገበ ቃላት ሊጠቀስ እንዴት ይችላል? እሱንም እሽ እንቀበላችሁ ጥቀሱት፡፡ “ወልደ አብ” እንዴት ማስረጃ ሆኖ ይጠቀሳል? ምክንያቱም “ወልደ አብ” የታተመው ትናንትና ነውና፡፡ ስንት ቀደምት መጻሕፍት እያሉ የትናንትናውን የ “ገብረመድኅን እንዳለው” ን ተረት እንደማጣቀሻ መጠቀም ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል? በእርግጥ ሌሎችም የሚጠቃቅሷቸው መጻሕፍት አሉ ያውም የብራና ናቸው አሉ፡፡ ህዝቡን ለመሸወድ “የብራና መጽሐፍ ገጽ እዚህ ላይ እንዲህ ይላል” ይላሉ፡፡ ሕዝቡ የሚረዳው አንድ ነገር አለ እሱም ምንድን ነው “የብራና መጽሐፍ ማለት ቀደምት መጽሐፍ ነው” የሚል ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ ስለሚያውቁ ነው እንግዲህ በድክመታችን ገብተው የራሳቸውን ምንፍቅና ለመዝራት የብራና መጽሐፍ ወዘተ የሚሉት፡፡
     ወገኖቼ በዚህ እንዳትሸወዱ የብራና መጻሕፍት የሚጻፉት ከፍየል ቆዳ ነው ዛሬ ድረስ ፍየሎች አሉ ቆዳቸውም አለ፡፡ ስለዚህ ዛሬም መጻፍ እንችላለንና ይህ ቀደምትነትን ያሳያል ብላችሁ እንዳትሸወዱ፡፡እነርሱ የሚጠቅሷቸው መጻሕፍት ቀደምት ላለመሆናቸው ማስረጃው “ደብረ ወርቅ ማርያም” እና “ቆጋ ኪዳነ ምሕረት”ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ብራና ላይ የተጻፈውን ሁሉ ወረቀት ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ወረቀት ላይ ያለውንም ሁሉ እንዲሁ ብራና ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቁምነገሩ የብራና የወረቀት መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም “ድንግል ማርያም አታማልድም” ብሎ ብራና ላይ መጻፍ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ብራና ላይ ስለተጻፈ ብለን የዓለም እናትን ወላዲተ አምላክ እመ ብርሃንን የጭንቅ ቀን ደራሽ እናታችንን አታማልድም ብለን አንናገርም፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውንስ በብራና ጽፈው ቀደምት ነው እያሉ ስላለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ አለን? ስለዚህ ብራና ኑፋቄን አይቀበልም ብለን ስለማናምን እውነተኛ መጻሕፍት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ አሁን እንደ መግቢያ ይህን የምጽፍላችሁ ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንገባ እነዚህን ጉዳዮች ልብ እንድታደርጉ ስለምፈልግ ነው፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን የኑፋቄ መጽሐፋቸውን እስከዛው ድረስ እያነበባችሁ እንድትቆዩኝ አሁንም አሳስባችኋለሁ፡፡ የቅብአት እምነት ተከራካሪ ወገኖችም በትህትና ያለመሰዳደብ እውነቱ ላይ ብቻ አተኩረን እንድንነጋገር አሳስባችኋለሁ፡፡
ይቀጥላል…
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 3
ሰኔ 15/2008 ዓ.ም
     ባለፉት 2 ክፍሎች በቅብአት ምንፍቅና የተጠመዱ ሰዎች ህዝበ ክርስቲያኑን ለማታለል የተደበቁባቸውን ሶስት ካባዎች ተመልክተናል፡፡ የመጀመሪያው የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጾመ ነቢያትና የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ቀናትን ነው፡፡ በመጨረሻ የተመለከትነው የመደበቂያ ካባ ደግሞ “ቀባ” እና ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ቃላትን ነው፡፡ ከዚህ ጋርም በተያያዘ ከመጻሕፍት ላይ እነዚህን ቃላት በመፈለግ እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል” ማለታቸውን እንዲሁም ጥንታዊ እምነት ቅብአት ነው ለማለት “በብራና መጻሕፍት ላይ እንዲህ ተጽፏል” እያሉ ህዝቡን ለማደናገር መሞከራቸውን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው “ቅብአት” የሚል ቃል በመጻሕፍቶቻችን ውስጥ ይገኛልን? የቃሉ ትርጉምስ እነርሱ እንደሚሉት ነውን? የሚለውን ነው፡፡በአሥራው መጻሕፍቶቻችን እንዲሁም በአዋልድ መጻሕፍቶቻችን የ”ቅብአት” ነገር ብዙ ጊዜ ተጽፏል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች በመጻሕፍተ ሊቃውንትም እንዲሁ በተለያዩ ሊቃውንት ጽሑፎች ላይ “ቅብአትን” ያነሣሉ፡፡
     ይህ ቅብአት ምንድን ነው? ስትሉ ግን እምነት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ቃላት እንደቃላቸው በቀጥታ አይፈቱም አይተረጎሙም፡፡ “ቅብአት” ን በተለያየ መልኩ ሊቃውንቱ መተርጉማኑ ይፈቱታል ይተረጉሙታል፡፡ “ቀባ” ብለው አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ፤ “ቀባ” ብለው አነገሠ ሾመ ሥልጣን ሰጠ፣ “ቀባ” ብለው አዋሐደ እያሉ ይተረጉሙታል ይፈቱታል፡፡ የቅብአት እምነት ተከታዮች ደግሞ “ቅብአት” የሚለውን ቃል ወስደው “አብ ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቅብአትነት አከበረው” ብለው ይተረጉሙታል ውድቀቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ወገኖቼ ግልጽ ይሁንላችሁ በደንብ ተረዱት፡፡ ወደሌላ ምሥጢር ሰደደኝ እንጅ ለዚህ ሁሉ እምነት መፈልፈል ምክንያቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ነው፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም ቢሆንም ቅሉ ቅብአት ከሳጥናኤል ቀጥሎ የሚመጣ ክህደት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሳጥናኤል እኔ ፈጣሪ ነኝ አለ፡፡በመቀጠል በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ምክንያት ከተሰናከሉት(ክህደት ካፈለቁት) ወገኖች ግንባር ቀደም የሚሆኑት “ቅብአቶች” ናቸው፡፡ እስላሞች በዕለተ ስቅለት ጊዜ የተሰቀለው ነቢይ ነው በማለታቸው አምላክነቱን በመካዳቸው እስላም እንደተባሉ ሕማማተ መስቀል ያስነብበናል፡፡ ፕሮቴስታንቶችም የተሰቀለው በደሙ ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ብለው በማመናቸውን ክህደትን ጀምረዋል፡፡ ጸጋዎችም በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና አምላክ ሆነ ብለው በማመን ክህደታቸውን ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ የካዱ ናቸው ቅብአቶች ግን ሲወለድ ጀምረው ክህደት ጀምረዋል፡፡ ምን ይላሉ “ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ” ወልደአብ ገጽ 216 ቅብአቱ ምን እንዳደረገው ሲገልጹ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብለው ክደዋል ወልደ አብ ገጽ 233፡፡
     ስለዚህ የቅብአት ክህደት የሚጀምረው ገና ከማኅጸነ ማርያም ሲወጣ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ በእውነት ልብ በሉ ወገኖቸ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር አይደለምን? ዮሐንስ ወንጌላዊ ለመናፍቃን መዶሻ በሆነው መለኮትን በረቀቀ መልኩ በገለጸበት ወንጌሉ ምእራፍ 1 ቁጥር 1 ላይ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ስለዚህ ቃል ራሱ የባሕርይ አምላክ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለ አምላክ ነው፡፡ ቃል ራሱ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ከአምላክነት ዝቅ አድርገውት “ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለው በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለው ክህደታቸውን በዚህ ጀምረዋል፡፡ ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና “ቀባ” የሚለው ቃል ትርጉሙ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ በተለምዶ የምናውቀውን መቅባት የሚያስረዳ ብቻ አይደለም፡፡ ነገሥታትን አነገሠ ሲል ቀባ ይላል፡፡ሥጋን አከበረ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ተዋሐደ ሲል ቀባ ይላል፡፡ሥጋን ከፍ ከፍ አደረገ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ አደረገ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ የየራሱ የትርጉም ቦታና ጊዜ አለው፡፡
     ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽዮን” ፣“መማለድ” የሚሉ ቃላትን ብዙ ቦታ እናገኛቸዋለን፡፡ ጽዮን አንዳንድ ቦታ ከተማ አንዳንድ ቦታ ተራራ አንዳንድ ቦታ ድንግል ማርያም አንዳንድ ቦታ ታቦት ሆኖ ይተረጎማል እንጅ “ጽዮን” የሚለውን ቃል በሙሉ ለተራራ ብቻ አልያም ለከተማ ብቻ አልያም ለድንግል ማርያም ብቻ አልያም ለታቦት ብቻ ተሰጥቶ አይተረጎምም አይፈታምም፡፡ “መማለድ” የሚለው ቃልም እንዲሁ ተመሣሣይ አፈታት አለው፡፡ ነገር ግን አፈታቱ አተረጓጎሙ አንድ ብቻ ነው ካልን ሮሜ 8÷34 ን ወስደን ወልድ ይማልድልናል፤ ሮሜ 8÷26 ን ወስደን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል ኤር 7÷25 ን ይዘን ደግሞ እግዚአብሔር ይማልዳል ልንል ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ አምላካችን ማን ሊሆን ነው? ስለዚህ በተመሳሳይ መልኩ ከ“ቅብአት” ጋራ ተያይዞ የተገለጹት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላትም በሙሉ የየራሳቸው የአተረጓጎም ስልት አላቸው የሚተረጎሙትም በተለያየ ቦታ የተለያየ ፍችን ወስደው ነው፡፡ ዳዊትና ሳኦል ተቀቡ ሲል መቸም የባሕርይ አምላክ ሆኑ ተብሎ አይፈታም፡፡ በሀገራችንም እንደ ላሊበላ እንደ ቴዎድሮስ እንደ ምኒልክ እንደ ኃይለ ሥላሴ ያሉ ነገሥታት ተቀብተዋል ስንል የባሕርይ አምላክ ሆነዋል ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛም እንዲሁ በ40 በ80 ቀናችን ተቀብተናል ማለት ልጅነትን አግኝተናል ማለት እንጅ የባሕርይ አምላክ ሆነናል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አፈታቱና አተረጓጎሙ ይለያያል፡፡ ሊቃውንቱ “ቀባ” የሚለውን ቃል “ሥጋን አከበረ ሥጋን ከፍከፍ አደረገ ሥጋን ተዋሐደ” ብለው አርቅቀው አመስጥረው አብራርተው አስረድተው ይተረጉሙታል፡፡ ስለዚህ “ቀባ” ማለት ቅብአትን አፍስሶ ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ማስተካከል ማለት አይደለም፡፡ወደ ክህደት መጽሐፋቸው ልገባ ስለሆነ እንደተለመደው “ወልደ አብ” ን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል...
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 4
ሰኔ 16/2008 ዓ.ም
     ባለፉት ክፍሎች የቅብአት ክህደት ለዓለም ሁሉ ተገልጦ ሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጥ ክህደታቸውን እንዳይረዳ በሥውር ክህደታቸውን ለማስፋፋት ያመቻቸው ዘንድ ክህደታቸውን የደበቁባቸውን ካባዎች ተመልክተናል፡፡ በእነዚያ ተከታታይ ክፍሎች ላይም የ “ቅብአት” ምንፍቅና ቅልጥ ያደረጋቸው እህቶችና ወንድሞች ከተጻፈው ጽሑፍ ጋር የማይገናኙ የተለያዩ አስተያየቶችን በስድብ አጅበው ሰጥተዋል፡፡ እኛ ግን ግልጹን እንንገራችሁ ስለተዋሕዶ ዝም አንልም፡፡ ገና ብዙ እንላለን ገና ምኑን አይታችሁት፡፡ እናንተም ስደቡን እኛም እንሰደባለን! በዚህ ክፍል የምናየው በ “ቅብአት” የከበረው ማን ነው? የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ባለፉት ክፍሎችም እንደተመለከትነው “ቀባ” የሚለው ቃል አንድ ዓይነት ፍቺ የለውም፡፡ “ቀባ” አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ የሚለውን እንውሰድና እንመልከት፡፡ በ “ቅብአት” እምነት ውስጥ “ቀባ” የሚለው ቃል ከዚህ የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም፡፡ “ቀባ” ብሎ አከበረ ከፍከፍ አደረገ የሚል ብቻ ነው ትርጉማቸው፡፡ እሽ እናንተ በተሰፋችሁበት ልክ እንሰፋ እና እንነጋገር፡፡ “ቀባ” ማለት አከበረ ከፍከፍ አደረገ ማለት ብቻ ነው ብለን እንከተላችሁ፡፡ ማን ነው የተቀባው? ማለትም ማነው ከፍ ከፍ ያለው? ማነው የከበረው? የሚለውን ጥያቄ ግን እንድትመልሱልን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄየን ግን ተውኩት የጥያቄውን መልስ “ወልደ አብ” ከተሰኘው የምንፍቅና መጽሐፋችሁ ገጽ 233 ላይ አገኘሁት፡፡ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብላችሁ የከበረው ከፍ ከፍ ያለው ወልድ (ቃል) እንደሆነ በክህደት በተሞላ ጽሑፋችሁ ጽፋችሁልናል፡፡ ቆዩ እንጅ ትንሽ ግን አይዘገንናችሁም? “ወልድ” ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል ነውን መወለድ ያስፈለገው? “ወልድ” በመጀመሪያ እግዚአብሔር አልነበረምን? በእውነት ኅሊና ላለው ሰው መክበርን ከፍ ከፍ ማለትን መስተካከልን ለመለኮት ቀጽሎ ይናገራልን? እንደፈለጋችሁት ማተም የሚችል ሰው ስላገኛችሁ ብቻ ይሆንን እንዲህ ያለውን ክህደት ለትውልዱ ያስቀመጣችሁት? ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ በፈሰሰው ደሙ በተወጋው ጎኑ ይቅር ይበላችሁ፡፡
     በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ያውም በአንዲት ገዳማችን ስም እንዲህ ያለውን ምንፍቅና ለመጻፍ ያስደፈራችሁ አይዟችሁ ባይ በማግኘታችሁ ሳይሆን አልቀረም፡፡ የሆነው ሆነና “ወልድ” በቅብአት ከበረ ከፍ ከፍ አለ ስትሉ እንዴት አታፍሩም? መቼም ይህንን በመጽሐፋችሁ ያሰፈራችሁትን አትክዱም፡፡ በዚህ ብቻ አያልቅም ወገኖቼ የከበረው ወልድ እንደሆነ ቁልጭ እያደረጉ ነው የጻፉት፡፡ መስማት ካልከበዳችሁ ስሙት ያሉትን “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ወልደ አብ ገጽ 127፡፡ “ወልድ” እዚህ ላይ ፍጡር ሆኗል ማለት ነው ምንም ክርክር የሌለው ነጥብ ነው፡፡እንግዲህ “ወልድ” ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ አምላክ ለመሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል “ቅብአተ መንፈስ ቅዱስ” አስፈለገው ክህደት ማለት ይቺ ነች እንግዲህ፡፡ አያችሁ ወገኖቻችን ሚጠት የሚባለው ክህደት ይኼ ነው እንግዲህ፡፡ ሚጠት ማለት መመለስ ማለት ነው፡፡ ወልድ አስቀድሞ አምላክ ነበረ ከድንግል ማርያም ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ተፈጠረ (ሰው ሆነ) ከዚያም በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ እና አምላክ ሆነ ወደ ቀደመው አምላክነቱ ተመለሰ ይሉናል፡፡ የቅብአት ክህደት እንግዲህ በዚህ ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት እንደ በትረ ሙሴ ማለት ነው፡፡ የሙሴ በትር በእጁ ሲይዛት በትር ሲጥላት እባብ ሲያነሣት ተመልሳ እንደቀድሞው በትር ሆናለች በዚያ ምሣሌ ቅብአቶችም አምላክን እንደዛ አደረጉት፡፡ ቅብአቱ ረባው ጠቀመው ማለታቸውም ቅሉ ከአምላክ ጋራ (ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ) ጋራ አስተካከለው ማለታቸው ነው፡፡ ሎቱ ስብሐት!በዚህ ይቀጥሉና አርዮስን ጥሩ ዘመዳቸው ያደርጉታል፡፡ በእርግጥ እንዲህ አድርገህ ብትክድ ኖሮ እኮ እኛን ትመስለን ነበር ነው ለማለት የፈለጉት፡፡ ትንሽ የዝምድና መራራቅ ሊኖር ይችል ይሆናል በሰማይ ቤት ግን ለዘለዓለም መዛመዳቸው አይቀርምና ያው ዘመዳሞች ናቸው እንበል፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 ይላሉ፡፡ አርዮስ እናንተን ሳያገኝ በመሞቱ ሳይሰማው አይቀርም ምክንያቱም ክህደቱን በሌላ ክህደት ታስተካክሉለት ነበርና፡፡ እኔን የገረመኝ ነገር እንዲህ እንደፈለጋችሁ ስትፈነጩ ዝም የተባላችሁበት ነገር ነው፡፡ ምን ዓይነት አዚም እንደለቀቃችሁብንም አይገባኝም፡፡ ጠቅለል ሲል መክበር ከፍ ከፍ ማለት የሚስማማው “ቃል” ሳይሆን ሥጋ ነው፡፡ ሥጋን የሚያከብረው ደግሞ ራሱ እከብር አይል ክቡር የሆነው “ቃል” ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል እግዚአብሔር ነውና! ዮሐ 1÷1 ለዛሬ በዚሁ ልቋጨው እንደተለመደው መጽሐፉን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል፡፡
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 5
ሰኔ 20/2008 ዓ.ም
      በክፍል 4 ትምህርታችን መክበር የሚስማማው ሥጋ እንጅ መለኮት እንዳይደለ ተመልክተናል፡፡ በዚህ የማይስማሙት የቅብአት ምንፍቅና ተከታዮች ግን አሁንም ስድባቸውን ቀጥለዋል፡፡ እውነቱን የሚገልጥባቸውን አይፈልጉም እኛ ግን እውነታውን እንናገራለን ምሥጢረ ተዋሕዶንም እንመሰክራለን፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 የሚለውን ጽሑፋቸውን እና “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና” ወልደ አብ ገጽ 127 የሚለውን ክህደት አሁንም ድረስ ይከራከሩበታል፡፡ “በሥጋው ፍጡር ካላልነውማ በመለኮቱ ታመመ በመለኮቱ ሞተ ትላላችሁ ማለት ነዋ!” ብለው ያልተጻፈውን ያነብባሉ፡፡ እኛስ አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንዲህ እንላለን “ሰው ስለሆነ ተፈጠረ ሰው በመሆኑም ዓለምን ለማዳን ታመመ ቢባልም እርሱስ የአብ አንድ ልጁ ነው ፍጡርም አይባልም” ሃ.አበ ዘቄርሎስ ምእራፍ 76 ክፍል 35 ቁጥር 2 ስለዚህም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ እንለዋለን እንጅ እኛስ ከተዋሐደ በኋላ ሥጋንና መለኮትን ከፋፍለን በሥጋው ፍጡር ነው አንለውም፡፡ መታመሙ መሞቱ በሥጋው ነው ስንል በመለኮቱ ታመመ በመለኮቱ ሞተ ማለታችን አይደለም፡፡ መለኮትን የተዋሐደ ሥጋ ሞተ እንላለን እንጅ፡፡መለኮት የተለየው ሥጋ አልተሰቀለም መለኮት የተለየው ሥጋ ወደ መቃብር አልወረደም መለኮት የተለየው ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን አላወጣም መለኮት የተዋሐደው ነው እንጅ፡፡ ቃለ ግዘት ምእራፍ 120 ክፍል 3 ቁጥር 1 ላይ “እሱ ሰውን ፈጠረ ከዚህም በኋላ በእሱ በፍጡሩ እግዚአብሔር ቃል አደረበት የሚል ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ይላል ሃይማኖተ አበው፡፡ ስለዚህም በዚህ ከላይ ባየናቸው ክህደቶቻቸው ለዘለዓለም የተወገዙ ናቸው፡፡
     እነርሱ ግን የተዋሕዶ ትርጉም አልገባቸው ማለቱን የተረዳሁት ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ የጻፉትን ድፍረት ስመለከት ነው፡፡ “ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይሉናል፡፡ ወገኖቼ አስቡት ይህንን ድፍረት ምሥጢረ ስላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን ያልተማረ ሰው ካልሆነ በቀር እንዲህ የሚለውን ክህደት ባልሞከረውም ነበር፡፡ “የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” የሚለውን እንውሰደው እንግዲህ፡፡ በመጀመሪያ ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት ማለት ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት ቦታ ነው ለመንፈስ ቅዱስ ያጣንለት? በመቀጠል የቃል ክብር ከመንፈስ ቅዱስ ክብር ይለያልን ብንላቸው ምን ይሉን ይሆን? እነርሱ እንደሚሉት ከሆነ የቃል ክብር ከመንፈስ ቅዱስ ክብር የተለየ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” ማለታቸው፡፡ ቃል ባለበት መንፈስ ቅዱስ የለም ማለት ክህደት ነው፡፡ ቃል ሥጋን የተዋሐደው ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ አይደለም፡፡ በቃል ሕልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በጊዜ ተዋሕዶም ሕልውናውን አላጣም፡፡ ስለዚህ የቃል ተዋሕዶ ከመንፈስ ቅዱስ ባለመለየት እንደሆነ እንናገራለን፡፡ተዋሕዶ የቃልን ክብር ወደ ሥጋ ማሳለፍ ብቻ አይደለም ተዋሕዶ ማለት “የቃልን ገንዘብ ለሥጋ የሥጋንም ገንዘብ ለቃል ማድረግ” ነው፡፡ ቀጥለው “ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይላሉ፡፡ ተዋሕዶ ሁለትነትን ለማጥፋት አንድነትን ለማጽናት ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ ሁለትነትን ለማጥፋትማ መዋሐድም ላያስፈልግ ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም በመቀላቀል በመደባለቅ ሁለትንትን አጥፍቶ አንድነትን አጽንቶ መኖር ይቻላልና፡፡ ምናልባት ጸሐፊው ዘመናዊውን ትምህርት ያልተማረ ይሆናል እንጅ ይኼ 1ኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጥ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ “አየር የምንለው ኦክስጅን፣ ናይትሮጅን፣ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ… የመሳሰሉት በባሕርይ የተለያዩ የሆኑ ጋዞች ተቀላቅለው የሚገኙበት ነው፡፡ እነዚህ ከሦስት በላይ የሆኑ ጋዞች አንድነትን አጽንተው አየር የሚል ስም የተሰጣቸው በመዋሐድ ሳይሆን በመቀላቀል ነው፡፡ ያልተዋሐዱ በመሆናቸውም የኦክስጅን ገንዘብ ለናይትሮጅን የናይትሮጅንም ገንዘብም ለካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሊሆን አይችልም፡፡ የአንዱን ገንዘብ ለሌላው ገንዘቡ ለማድረግ የግድ መዋሐድ ያስፈልጋቸዋል” ስለዚህ ተዋሕዶ ያስፈለገው ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ለማጽናት ብቻ አይደለም፡፡ ተዋሕዶ ያስፈለገው የሥጋን ገንዘብ ለቃል የቃልንም ገንዘብ ለሥጋ ለማድረግ ነው፡፡ ሥጋ ክብርን የሚያገኘውም ከቃል ጋር ሲዋሐድ ብቻ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ይህ የሥጋ ነው ይህ የመለኮት ነው በማለት ልንለያየው አንችልም፡፡
     ይህንንም ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ “ኦክስጅንና ሄድሮጅን ተዋሕደው ውኃን ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ከተዋሐዱ በኋላ ይህ ሃይድሮጅን ነው ይህ ደግሞ ኦክስጅን ነው ብለን መክፈል አንችልም፡፡ ምክንያቱም የሃይድሮጅን ገንዘቦች በሙሉ ለኦክስጅን የኦክጅንም ገንዘቦች በሙሉ ለሃይድሮጅን ሆነዋልና ” ይህ ለተማሩት ማስረጃ የሚሆን ቀላል ምሳሌ ነው፡፡በእርግጥ ምሳሌዎች ሁሉ የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ ያስረዳሉ ማለት አይደለም ትንሽ ፍንጭ ይሰጣሉ ለማለት ነው እንጅ፡፡እንግዲህ የመለኮት ከሥጋ ጋር መዋሐድ ሁለትነትን ብቻ ለማጥፋት እንዳልሆነ በዚህ ተረዱ፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ሁለትነትን ብቻ ለማጥፋት ቢሆን ኖሮ መቀላቀልም ይችል ነበርና ነገር ግን በመቀላቀል ጊዜ የአንዱ ገንዘብ ለሌላው አይሆንምና የሥጋን ገንዘብ ለቃል የቃልንም ገንዘብ ለሥጋ አድርጎ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ተዋሐደ፡፡ ይህንንም ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምእራፍ 78 ክፍል 48 ቁጥር 3 ላይ እንዲህ ይጽፍልናል “ካልተዋሐደስ እርስ በእርሱ በተካከለ ሥራ አንድ ሆኖ ባሕርዩ በመለኮት ላይ ተጨመረ እንዳልን ይቆጠራል፡፡ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ ወደ መሆን እንደተለወጠ ቃልም የሥጋን ባሕርይ ወደ መሆን እንደተለወጠ አይነገርም መለኮት ባሕርዩን ሊለቅ ሊለውጥ እንዳይቻል እንዲሁ ከፍጡራንም ወገን ማንኛውም የመለኮትን ባሕርይ ወደመሆን ሊለወጥ አይቻልም ሥጋ ፍጡር ግቡር ነውና” ይለናል፡፡ ስለዚህ ለሥጋ የጠቀመው የረባው እንዲከብር ያደረገው የቃል ከሥጋ ጋር መዋሐድ ነው፡፡ ሥጋ ከቃል ጋር በመዋሐዱ ነው ግዙፍ ሲሆን ረቂቅ አምላክ ሲሆን ሰው ምሉዕ ሲሆን ጠባብ መሆኑ እና መባሉ፡፡
ይቀጥላል…
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 6
ሰኔ 21/2008 ዓ.ም
     በክፍል 5 ተዋሕዶ የሚለው ቃል በቅብአት መናፍቃን አንደበትና በእኛ አንደበት የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጠው ተመልክተናል፡፡ በዚህም ክፍል እንዲሁ ከአባቶቻችን ምሳሌ አንዱን እንመለከታለን፡፡ በክፍል 5 ላይ የሰጠኋችሁ የተዋሕዶ ምሳሌ “የሃይድሮጅንና የኦክስጅን” ውህደትን ነበር፡፡ እሱ ምሳሌ ትንሽ ፍንጭ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው እንጅ አባቶቻችን ከቀድሞው ዘመን ጀምረው ቅብአትን የሚረቱበት ምሳሌ አላቸው፡፡ እኛም እንዲሁ እሱን እንነግራችኋለን፡፡ የቅብአት ምንፍቅና ያነሆለላቸው ጥቂት የሚባሉ በተለይም ደግሞ አሁን በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ደረጃ ላይ ያሉ ለጋ ወጣቶች ተዋሕዶን “ወርቅ ከብር ጋር ተቀላቅሎ ክብር እንደሚሆነው ሁሉ በተዋሕዶም ወቅት መለኮት ለሥጋ ክብር ሆነው ትላላችሁ” ብለው ነገርን ያጣምማሉ፡፡ እኛስ አባቶቻችንም እንዲህ ያለውን የክህደት ምሳሌ አላስተማሩንም አልጻፉልንምም አልመሰሉልንምም፡፡ እነዚህ የቅብአት በሽታ የተጠናወታቸው መናፍቃን ግን እኛ ያላልነውን ብለው እኛ ያልጻፍነውን አንብበው እንዲህ አሉ ብለው ይናገራሉ፡፡ ወርቅ ከብር ጋር ቢቀላቀል እንጅ እንዴት ሆኖ ሊዋሐድ ይቻለዋል? እኛ የምንለው ያለመጨመር፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመደባለቅ፣ ያለ ማደር፣ ያለ መጎራበት፣ ያለመለወጥ በፍጹም ተዋሕዶ አካለ ሥጋ ከአካለ ቃል ጋራ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኑ ነው፡፡ ወርቅና ብር ደግሞ በምንም ተአምር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሊሆኑ አይችሉም ምክንያቱም መዋሐድ ስለማይችሉ፡፡ ይህንን ደግሞ የኬሚስትሪ ባለሙያዎችን አማክሩ፡፡ አለቀ፡፡
     እኛ ግን ተዋሕዶን አባታችን ቄርሎስ በመሰለልን የጋለ ብረት እንመስለዋለን፡፡ ብረት የሚስማማው ባህርይ እሳት ከሚስማማው ባህርይ ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብረት እና እሳት ሁለት የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ደህና ብረት ሰሪ ያገኘው እንደሆነ ከእሳት አግብቶ ያግለዋል፡፡ ከዚያም የጋለውን ብረት አውጥቶ የፈለገውን ዓይነት ቅርጽ ሰጥቶ ይሰራዋል፡፡ እዚህ ላይ የምንመለከተው ቅድመ ግለት፤ ጊዜ ግለት እና ድኅረ ግለትን ነው፡፡ ቅድመ ግለት ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያትን እንመለከታለን፡፡ እሳት አንድ አካል ነው አንድ ባሕርይ ነው ብረትም እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ እሳትና ብረት የራሳቸው የሆነ አካልና ባሕርይ አላቸው፡፡ በጊዜ ግለት ግን እሳት የብረትን ብረትም የእሳትን ባሕርይ ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ለዚህም ነው እሳቱ የብረቱን ቅርጽ ብረቱም የእሳቱን መልክእ ይዞ መገኘቱ፡፡ በጊዜ ግለት ጥቁር የነበረው ብረት የእሳትን ቀይነት መልክእ ገንዘቡ አድርጎ ቀይ እንደሚሆን ሁሉ ጎንና ዳር የሌለው የማይጨበጠው ረቂቅ እሳትም ግዙፍ የሆነውን የብረት ቅርጽና ግዘፍነት ገንዘቡ አድርጎ የብረቱን ቅርጽ የብረቱን ግዘፍነት ይዞ ይገኛል፡፡ ትክክለኛው የተዋሕዶ ምሳሌ እንግዲህ ይህ ነው፡፡ ብረቱ የሥጋ እሳቱ የመለኮት ግለቱ የተዋሕዶ ምሳሌ ነው፡፡ በቅድመ ተዋሕዶ ሥጋ እና መለኮት የተለያዩ ባሕርያት የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ሥጋ የራሱ ገንዘብ የራሱ አካል አለው መለኮትም የራሱ ባሕርይ የራሱ አካል አለው፡፡ በጊዜ ተዋሕዶ ግን ሁለት አካላት አንድ አካል ሁለቱ ባሕርያት አንድ ባሕርይ ሆነዋል፡፡ መለኮት የሥጋን ግዘፍነት ጠባብነት ውስንነት ደካማነት ገንዘቡ እንዳደረገ ሁሉ ሥጋም የመለኮትን ረቂቅነት አምላክነት ፈጣሪነት ምሉዕነት ፈታሒነት ገንዘቡ አደረገ፡፡ ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ መለኮትም የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ ሌላ አካልን አይሹም፡፡ ቃል መለኮት ነው ይህ መለኮት የራሱ የተለየ አካል የተለየ ገጽ አለው ከሥጋ ጋርም የተዋሐደው በራሱ አካል ነው፡፡ ይህ ማለት እጅ ከሰውነት አካላት ሳይለይ ዕቃን እንዲያነሣ ቃልም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ የጠፋ በግ አዳምን ይፈልግ ዘንድ በማኅጸነ ማርያም በሥጋ ማርያም በፍጹም ተዋሕዶ ተገልጧል ማለት ነው እንጅ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነቱ ተለይቶ ተዋሕዷል ማለት አይደለም፡፡
     ስለዚህ በጊዜ ተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስን አይሻም ማለት ስለዚህ ነው፡፡ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በማኅጸነ ማርያም አድሯልና ቅብአቶች እንደሚሉት ለተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስን የሚሻ አይደለም፡፡ ከዚህ ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋና መለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ናቸው እንጅ ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት አይደሉም፡፡ ቅብአቶች እንደሚሉት ተዋሕዶ ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ለማምጣት ብቻ የተደረገ እንዳልሆነ በጋለው ብረት ምሳሌ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ብረት ከእሳት ጋር ሲዋሐድ የየግል ገንዘቦቻቸውን የጋራ ገንዘቦቻቸው አድርገው ነው፡፡ ለዚያም ነው የማይቀጠቀጠው እሳት ከብረት ጋራ ስለተዋሐደ በመዶሻ የሚቀጠቀጠው ሆኖም ግን መቀጥቀጡ በብረቱ እንጅ በእሳቱ ላይ አይደርስበትም፡፡ ቅብአቶች “ህማሙ ግርፋቱ በመለኮቱ ደርሶበታል ልትሉን ነውን” ይሉናል፡፡ እኛ ግን የሥጋው ሕማም ወደ መለኮቱ የሥጋው ረሃብ ወደ መለኮቱ የሥጋው ግርፋት ወደ መለኮቱ ያልፋል አንልም፡፡ የጋለን ብረት ቢቀጠቅጡት እሳት ላይ እንደማይደርስ ሁሉ የሥጋና የመለኮትም እንዲሁ ነውና፡፡ ፀሐይ ያረፈችበትን ግንድ ቢቀጠቅጡት ግንዱ ይቀጠቀጣል እንጅ ፀሐይ አትቀጠቀጥም እንደዚህም ሁሉ መለኮት የተዋሐደው ሥጋ በሥጋው ቢገረፍ ቢጠማ ቢራብ ቢቸነከር ቢቀበር በመለኮቱ አይደርሱበትም፡፡ ይህ ማለት ግን መለኮት የተለየው ሥጋ ተቀበረ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተገረፈ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተቀበረ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተራበ ተጠማ ማለት አይደለም፡፡ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሥጋ ከመለኮቱ ባለመለየት ታመመ ሞተ ተራበ ተጠማ ተሰቀለ እንላለን አንጅ፡፡
ይቀጥላል…
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 7
ሰኔ 22/2008 ዓ.ም
     በክፍል 6 የተዋሕዶን ምሳሌ በጋለ ብረት መስለን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ወልድ ከድንግል ማርያም ሥጋን ለመዋሐድ የመንፈስ ቅዱስን ቅባትነት እንደማይሻ ተረድተናል፡፡ምክንያታችንም እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ጥንትም ያለ ነው እንጅ፡፡ ጥንትነቱም መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወቱ የሆነው ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የሰው ኅሊና በማይደርስበት ረቂቅ ምሥጢር ነው አንጅ ዛሬ ሥጋን ሲዋሐድ አይደለምና ነው፡፡ ያ የቀድሞ የባሕርይ ሕይወቱ ለቅጽበት ታህል እንኳ የተለየበት ጊዜ ሰለሌለ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን የባሕርይ ሕይወቱ ያደርገው ዘንድ ወልድ አይሻም፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው በዚሁ ዙሪያ ነው፡፡ወልደ አብ ገጽ 212 ላይ ያለውን ክህደት መነሻ አድርገን እንጽፋለን፡፡ “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው፡፡ ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም፡፡ ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም ነፍስ ሕያው የሆነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” ይላል፡፡
     እስኪ ቃል በቃል እንመልከተው፡፡“በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”ሁላችን እንደምናውቀው በከዊን አብን “ልብ” ወልድን “ቃል” መንፈስ ቅዱስን “እስትንፋስ” እንላለን፡፡ የአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” ከመንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት (እስትንፋስነት)አይቀድምም አይከተልምም፡፡ በተመሳሳይ የወልድ “ቃልነት” ከአብ “ልብነት” እና ከመንፈስ ቅዱስ “እስትንፋስነት” አይይቀድምም አይከተልምም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም “ሕይወትነት” (እስትንፋስነት) ከአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው ማለት የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ማለት ነው፡፡ በቅብአት እምነት ውስጥ ግን “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ይላሉ፡፡እንግዲህ “ወልድ” ማለት ልጅ ማለት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ልጅነቱም ከአብ የባሕርይ ልጅነት ነው፡፡ ይህ “ወልድ” የሚለው ስም አብ “አብ” ከተባለበት መንፈስ ቅዱስም “መንፈስ ቅዱስ” ከተባለበት ስሙ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ “ወልድ” የሚለው ስም የተገባው የሆነ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ አይደለም፡፡ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜስ “አማኑኤል” “ኢየሱስ” ተባለ እንጅ ወልድ የተባለውስ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ “ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል” ከአብ በተወለደ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ “ወልድ” የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ያገኘው ዛሬ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ሳይሆን ጥንት ከአብ ተወልዶ “ወልድ” ተብሎ በተጠራበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ቢባል ክህደት ነው አንጅ እምነት አይባልም፡፡ ምክንያቱም “አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው ነውና” እንዳሉ የቀደሙ አባቶቻችን በሃይማተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምእ 101 ቁጥር10 ላይ፡፡
    ስለዚህ ይህ ህልውና ቀድሞ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ ያለ በመሆኑ እና ወልድ ከዚህ ህልውናው የተለየበት ጊዜ ስለሌለ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ” ቢባል ክህደት ነው፡፡ “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” ማለትን ከማን እንደተማሩት አይታወቅም፡፡ አብ በመለኮቱ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ወለደው እንጅ ድህረ ዓለምም ዳግመኛ በሰውነቱ ከእናት አልወለደውም፡፡በሰውነቱስ ከአብ ዳግመኛ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ “ወልደ አብ” መባል “ወልደ ማርያም” ከመባል በበለጠበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅድመ ዓለም “ወልደ አብ” የተባለው ድኅረ ዓለም “ወልደ ማርያም” ቢባል እኩል ነው አንጅ አይበላለጥም፡፡ እንዲያውም ሊቃውንቱ ሲያመሰጥሩ “ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ” ይላሉ፡፡ ይህ ማለት “ወልደ አብ” መባሉ “ወልደ ማርያም” በመባሉ ታወቀ ተገለጠ ማለት ነው፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ምእ 53 ቁ 13 ላይ “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደሆነ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ እንዴት እንደሆነ አትጠይቀኝ፡፡ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” ይላል፡፡ ሊቁ “ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” አለ እንጅ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች እንደሚሉት “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” አላለም፡፡ “ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም ”ይኼኛው ከመጀመሪያ ሃሳባቸው ጋር ይጋጫል፡፡ ምክንያቱም ቅድም “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” ብለው ነበር አሁን ግን “ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ” ብለው ሃሳባቸውን ራሳቸው ያጣሉታል፡፡ በእርግጥ መጽሐፋቸው ሙሉውን እንደዚህ እርስ በእርሱ የተጣረሰ ሃሳብ የሰፈረበት ነውና አይገርመኝም፡፡ እሽ ይሁን ብለን ብንቀበለው እንኳ “ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም ” ስላሉ መንፈስ ቅዱስን “ወላዲ” ያሰኛልና አንቀበለውም፡፡ አብን “ወላዲ” ፣ ወልድን “ተወላዲ”፣ መንፈስ ቅዱስን “ሰራጺ” ብንል እንጅ መንፈስ ቅዱስን “ወላዲ” እንዳንል እነሆ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡ “ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል” አልን እንጅ መቼ “ወላዲ” ነው አልን ቢሉም ወላጅ የሚመስል ሕይወት የለም ብለን እንመልሳለን፡፡“ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም ነፍስ ሕያው የሆነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡
     እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ረቂቅ ልደት በእንስሳት እና በሰው ልጅ ልደት ልንመስለው እንዴት እንችላለን? ሰው ቢወለድ ከእናት እና ከአባቱ ዘር ነው እንጅ በድንግልና አይደለም፡፡ እንስሳትም ከእንስሳት ቢወለዱ እንዲሁ በተራክቦ ነው እንጅ በድንግልና አይደለም፡፡ የወልድስ ከድንግል ማርያም መወለድ በማክሰኞ ቀን ኅቱም ምድር ለታብቁል ባለው ቃል አብቅላ አፍርታ እንደተገኘች ያለ ነው፡፡ ሰው ከሰው የተለየ እንስሳን፤እንስሳም ከእንስሳ የተለየ ሰውን ይወልዱ ዘንድ ፈጣሪ ተአምሩን ከገለጸ ይወልዳሉ፡፡ ይህንንም በተለያዩ ዜናዎች እየሰማን እና እየተመለከትን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምሳሌ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው” ለሚለው ክህደት ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ “እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” ብለው ክህደታቸውን በአራት ነጥብ ይቆልፉታል፡፡በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ ካልተወለደ በቀዳማዊ ልደቱ አብ ወልድን የወለደው የባሕርይ ሕይወቱ ከሆነው መንፈስ ቅዱስ ሕያው ከሆነ በኋላ ነውን ቢሏቸው መልስ የላቸውም፡፡ይህ ክህደታቸው ሌላ ክህደትን ይፈጥርባቸዋል፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” የሚለውን ስንመለከት ወልድ ከአብ ለመወለድ በመንፈስ ቅዱስ ህያው መሆን አለበት ከተባለ የአብን ልብነትስ መቼ ገንዘቡ ሊያደርግ ነው ቢባሉ መልስ የላቸውም፡፡ ጠቅለል ሲል እኛ አባቶቻችን ያስተማሩንን ትምህርተ ተዋሕዶ እንማራለን እናስተምራለን እንጅ አሁን በመጣ እንግዳ ትምህርት አንታለልም አንነጠቅምም፡፡
ይቀጥላል…
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 8
ሰኔ 23/2008 ዓ.ም
      በክፍል 7 “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት” ክህደት እንደሆነ በሚገባ ተመልክተናል በዚህ ክፍልም የዚህን ተከታይ መጽሐፋቸው “ወልደ አብ” ላይ ያለውን መነሻ አድርገን እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ የመጽሐፉ ርእስ “ወልደ አብ” የተባለበትን ምሥጢር ግን ሁላችን ልንረዳው ይገባል፡፡ “ወልደ አብ” ብለው መሰየማቸው አብ በመለኮትና በሰውነት ሁለት ጊዜ ወልዶታል ብለው ስለሚያስቡ ነው “ወልደ ማርያም” ከሚለው ስሙ ይበልጣል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ለማንኛውም እምነታቸው የራሳቸው ስለሆነ ባይመለከተንም በአንድ ገዳማችን ስም ስለጻፉት ግን የእኛ አስተምህሮ እንዳልሆነ እንገልጽ ዘንድ እንገደዳለን፡፡ ስለዚህም ዝም አንልም!!!
     ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ ነኝ ዛሬ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” እያለ ክህደት እንደ ጉድ ይጎርፋል፡፡ ቃል በቃል እንመልከት፡፡
“ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” ሥጋ ከፈጣሪው የጸጋ ልጅነትም የለውም ነበር ማለታቸው አዳም ስለበደለ እና ጸጋ እግዚአብሔር ስለተገፈፈበት ነው፡፡ ሆኖም ግን እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ያለው መለኮት ሲዋሐደው የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነትንም አገኘ ብለው ይደመድማሉ፡፡ በጣም ጥሩ ነው አሁን ላይ መለኮት ሲዋሐደው ሥጋ አምላክ ሆነ ክቡር ሆነ የቃል ገንዘብ ገንዘቡ ሆነ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ቀጥለው ይህንን ይጣረሱታል፡፡ “ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ከላይ “የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” ብለው ነበር አሁን ደግሞ እንደገና ተመልሰው “በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ብለው የሚጋጭ ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ ለዚህ ሃሳባቸውም የሚደግፍ ማስረጃ ብለው ሰውን ለማደናገር ግዕዙን ብቻ ጠቅሰው አማርኛውን ሳያስቀምጡት አለፉ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ግእዝን እንደማይችል ስለሚያውቁ እንዲህ ይላልሳ እያሉ ያወናብዳሉ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ፍችውም “ሃብታም ሲሆን እናንተ በርሱ ድህነት ባለጠጋዎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ደሃ ሆነ” የሚል ነው፡፡ እነርሱ ግን ሙሉውን ሳይጠቅሱ ቆርጠውታል፡፡ ሆኖም ይህ ጥቅስ “ቃል በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ” ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ ስለዚህም ማስረጃነቱን ለማወናበድ ካልተጠቀሙበት በቀር ምንም ማረጃነት የለውም፡፡ ማስረጃ ሊሆን የማይችለውም ነድየ የሚለው የሚስማማው ለሥጋ ነው እንጅ ለመለኮት አይደለምና ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ የሥጋ ንድየት በቃል ባዕልነት ተወግዷል፡፡ ስለዚህ የዚህ ማስረጃነት ተቀባይነት የለውም፡፡ ቀጥለውም  “ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም” ይላሉ፡፡
     በክፍል 7  ዳግመኛ “ከአብ በማኅጸነ ማርያም ተወለደ” የሚለውን ክህደት ተመልክተናል ስለዚህ እዚህ ላይ አልደግመውም፡፡  በመቀጠልም “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ብለው ወልድን ከአብ ያሳንሳሉ፡፡ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በመግዛት አንድ ናቸው፡፡ ይህ ምሥጢረ ሥላሴ ነው፡፡ ይህ የመግዛት አንድነት ወልድ ሥጋን በለበሰ ጊዜ አልተቋረጠም፡፡ ስለዚህ ወልድ የመግዛት አንድነቱን ይዞ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ሥጋን ቢዋሐድ ሥጋ የመግዛት ሥልጣንን ከወልድ ያገኛል እንጅ ከአብ አያገኝም፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስ አሉና አብ ለወልድ የመግዛት ስልጣንን የሚሰጠው ወልድም የመግዛት ስልጣንን የሚቀበል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመግዛት አንድነቱ የተለየበት ጊዜ ስለሌለ፡፡ ምናልባት በግልጽ አልጻፈላቸው ይሆናል እንጅ ጸሐፊው “ገብረ መድኅን እንዳለው” ወልድ አምላክነቱን ለዓይን ጥቅሻ ታህል አጥቷል ብሎ ያምናል፡፡ ሎቱ ስብሐት!
አሁንም በግእዝ ጠቅሰው ለማወናበድ “ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰” ይላሉ ትርጉሙን እንመልከት፡- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፡- ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” የሚል ነው ቆርጠው ስላስቀሩት ነው እንጅ፡፡ እስኪ አስተውሉ ወገኖቼ! “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ለሚለው “ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ማስረጃ ሊሆን የሚችለው በምን ሂሳብ ነው፡፡ ወይስ ደግሞ ግእዝ ስለሆነ የተጠቀሰው ሁሉ ማስረጃ ይሆናል ማለት ነው፡፡ “ገብረ መድኅን እንዳለው” በእውነት የመጽሐፍ ሊቅ አይደለም ማለት ነው እንጅ እንዲህ ባላለም ነበር፡፡ ከመጻሕፍት ሊቃውንት የወሰዳቸው ቃላት “እንዲል” “አንድም” የሚሉትን ብቻ ነው እንጅ እውቀቱን ትምህርቱን አልወሰደም፡፡ በራሱ ደስ እንዳለው የሚጽፍ የልብ ወለድና የፈጠራ ጸሐፊ ነው፡፡ በመቀጠልም “መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው” ይላሉ፡፡ አብን ሰጭ ወልድን ተቀባይ ልናደርገው እንዴት እንደፍራለን፡፡ ወልድስ ለመግዛት አብን እያስፈቀደ ነው ልንል እንዴት እንደፍራለን፡፡ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ መቀበል ያስፈለገውስ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ሕይወቱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አልቆበት ነው ልንል ነውን? ወይስ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ሊያድስ ነው ልንል ይሆን? ለዚህም ማስረጃቸው ያው የተለመደው ግእዝ ብቻ ነው፡፡ “አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ትርጉሙም “እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል” የሚል ነው፡፡ አንድምታውን ስትመለከቱ “ከእግዚአብሔር አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ተወልዶ የመጣ እሱን እግዚአብሔርነቱን ያስተምራል፡፡ ሀብተ መንፈስን በልክ የሚሰጥ አይደለምና” ይላል ተመልከቱት ሁላችሁም፡፡ ሌላው የጠቀሱት “ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” የሚል ነው ትርሙም “ሁሉን ወራሽ ባደረገው” ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ሁለቱም ቦታዎች ላይ ያስቀመጧቸው ጥቅሶች “ወልድ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው” የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ ማስረጃ ተብለው የተቀመጡት ሁሉ ማስረጃነት የሌላቸው የመጽሐፉን ገጽ ብቻ ለመጨመር የተጻፉ እንደሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ይቀጥላል…
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 9
ሰኔ 25/2008 ዓ.ም
     በክፍል 8 “ወልደ አብ” በተሰኘው የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ገጽ 219 ላይ ያለውን የክህደት አስተምህሮ ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 182 ላይ ያለውን ክህደት መነሻ በማድረግ እንጽፋለን፡፡“መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው፡፡ በእንተዝ ይትበሃል ከመ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ቀብዓኒ በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ እንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ እን ሳዊሮስ ዘአንጾ ሃ አ ክ ፱ ቁ፲፯” ይላል ሙሉ ንባቡ፡፡ እንግዲህ እንደተለመደው ቃል በቃል ለማየት እንሞክር፡፡“መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው”
      በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ “መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ” የሚል ትምህርት የለም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ካሉት ምሥጢራት መካከል አንዱ “ሜሮን” ነው፡፡ በዚህ ሜሮን በሚባል ቅዱስ ቅብአት ላይ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል መንፈስ ቅዱስ ያከብረዋል እንላለን እንጅ “መንፈስ ቅዱስ ቅብአ ሜሮን ነው” ብለን አልተማርንም፡፡ በሐዋ ሥራ 2 ላይ እንደምንመለከተው መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ አደረባቸው እንላለን እንጅ “ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ሆኑ” አንልም ምክንያቱም የሚያድርባቸው በጸጋ ነውና፡፡ስለዚህ ይህ አስተምህሮ የእኛ አይደለምና በአንዲት ገዳማችን ስም እንዲህ ዓይነቱን ኑፋቄ ማውጣት ድፍረት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ለዚህም የጠቀሱት ማስረጃ ያው እንደተለመደው አንዱን ካንዱ ጋር በማቀላቀል የሚያስቀምጡት የተቆረጠ የመጽሐፍ ክፍልን ነው፡፡ “በእንተዝ ይትበሃል ከመ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ቀብዓኒ በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኃደረ ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ እንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ እን ሳዊሮስ ዘአንጾ ሃ አ ክ ፱ ቁ፲፯” ይላሉ፡፡
     የጠቀሱት የሃይማኖተ አበው ክፍል ምን እንደሚል በግእዝም በአማርኛም እንመልከተው እስኪ፡፡ በመጀመሪያ እነርሱ እዚህ ላይ ቁጥር 17 ያሉት የቁጥር 16ን የተወሰነ ክፍል እና የቁጥር 17ን የተወሰነ ክፍል ቆራርጠው ነው፡፡ እንዲህ ይላል ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ክፍል 9 ቁጥር 16 ግእዝ “ወሃሎ መንፈስ ቅዱስ ይጼልል መልዕልተ ማይ እምቅድመ ዝንቱ ግብር ዘተፈጸመ በእንቲአነ በጥበብ ወሥርዓት ዘከመ ወጠነ ዳግመ ልሂኮተነ ወበእንተ ዝንቱ ይደሉ ይትበሃል ከመ ውእቱ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ቀብዓኒ” አማርኛ ትርጉም “እኛን ማደስን እንደጀመረ በጥበብ በሥርዓት ስለእኛ ከተፈጸመው ከዚህ ሥራ (ከጥምቀት) አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ ይሰፍ ነበረ ስለዚህም የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ሕልው ነው ስለዚህ ነገር አዋሐደኝ ሲል በኢሳይያስ የተነገረለትን የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን እርሱ ገንዘቡ እንደአደረገ ሊነገር ይገባዋል” የሚል ነው፡፡ በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ ሥጋ ገንዘቡ አደረገ ሲል እንዲህ አለ እንጅ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ተቀብሎ አብ ከድንግል ማርያም በሥጋ ወለደው አላለንም፡፡ ቁጥር 17 ግእዝ “በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ ዘህላዌየ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ ዝንቱ ውእቱ መድኃኒትነ ዝንቱ ውእቱ ፈውሰነ ዝንቱ ውእቱ ሐዋጺነ” ይላል አማርኛ ትርጉሙም “ስለዚህ በባሕሬዬ ገንዘቤ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ብሎ አስተማረ ሰው ብሆን ነው እንጅ ያለዚያ ለምን ክርስቶስ ተባልኩ? የምንድንበት ይህ ነው፡፡የሚፈውሰን ይህ ነው የጎበኘን ይህ ነው” ይላል፡፡ እንግዲህ ሁላችሁ እንደምታዩት ቆራርጠው በጠቀሱት ጥቅስ መንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ የባሕርይ ሕይወት ሆነው የሚል ትርጉም አንድም ቦታ ተጽፎ አላገኘንም፡፡ “በባሕሬዬ ገንዘቤ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ብሎ አስተማረ” ይላል እንጅ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቤ ሆነ አላለንም፡፡ ሰው ስለሆነ ይህንን ተናገረ ክርስቶስ የተባለው ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ በኋላ ነው እና፡፡ ከተዋሕዶ በፊት ክርስቶስ አልተባለም ነበርና አሁን ግን ሲዋሐድ ክርስቶስ ተባለ፡፡ ስለዚህም ሰው በመሆኑ “በእኔ ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ለሥጋየ ገንዘቡ ሆነ” አለን እንጅ እነርሱ እንደሚሉት ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቤ ሆነ አላለንም፡፡ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ገንዘቡ አደረገ የሚሉት ግን በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ወዴት ሄዶ ነው ዛሬ በሥጋ ርስት ዳግመኛ ሕይወት የሚሆነው? እዚህ ጋር ማስተዋል ያስፈልገናል ዋናው የክህደታቸው ምንጭ ይህ ስለሆነ፡፡
     እኛ የምንለው መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ይህም ጥንት ከሌለው ዘመን ጀምሮ በሰው ህሊና በማይመረመር አምላካዊ ጥበብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወልድ ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ ይህ በወልድ ሕልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሥጋን የባሕርይ አምላክ አደረገው ነው፡፡ እነርሱ የሚሉት ደግሞ ወልድ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ሕይወቱ አደረገ ነው፡፡ እኛ የምንጠይቀው ያ በቃል ህልው ሆኖ ይኖር የነበረው መንፈስ ቅዱስ የት ሄዶ ነው ዳግመኛ አከበረው የሚባለው? ወይስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ያልቃል ልትሉን ነው? ወይስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ አርጅቶበት ማደስ ያስፈልገዋል ልትሉን ነው? እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንመራለን፡፡ ኢሳ 61÷1 ላይ ያለውን ቃል ሉቃ 4÷17 ላይ ይተረጉሙታል፡፡ ሳዊሮስም ሃይማኖተ አበው ላይ እሱን ይተረጉማል ሳዊሮስ ክ 9 ቁ 18 እንዲህ ይላል “ስለዚህ ነገር ከዚህ በኋላ ለድኆች የምሥራች እነግራቸው ዘንድ ያዘኑትን አረጋጋቸው ዘንድ ለተማረኩት ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ ዕውሮች ያዩ ዘንድ ስለዚህ ላከኝ አለ፡፡መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ ሆነ መባሉ ቃል ሰው ስለሆነ ነው ሰውማ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ህልው እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮት ገንዘቡ ነውና እንደምን ገንዘቡ ሆነ ይባላል አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው መሆኑን እንደተናገረ”፡፡ ሳዊሮስ እዚህ ክፍል ላይ የተረጎመው ኢሳ 61÷1 ላይ ያለውን ቃል ነው፡፡ እንግዲህ ሳዊሮስ በግልጽ እንዳስቀመጠልን መንፈስ ቅዱስ በወልድ ህልው ሆኖ ይኖራል ያ ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ለሥጋ ገንዘቡ ሆነ ማለት ነው እንጅ ዳግመኛ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚል ትምህርት አላስተማረም እንዲያውም እዚሁ ክፍል ቁጥር 19 ላይ ሳዊሮስ እንዲህ ይላል “በዚህም ግብር ተዋሕዶ ጠፍቶ ከነቢያት እንደ አንዱ አልሆነም መንፈስ ቅዱስ ያደረበት አይደለም” ይላል፡፡ ስለዚህ የት ቦታ ላይ ነው ወልድ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ተቀብሎ አብ ከማኅጸነ ማርያም ወለደው የሚለው ትምህርት ያለው፡፡ ሉቃ 4÷17 ላይም ወንጌላዊው ሉቃስ ‹‹ኢሳ 61÷1›› ያለውን ወስዶ አስቀምጦታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌሉ እንዲህ ይላል፡፡ “ዘይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ” መጽሐፉን ገልጾ ሳለ ማስተማር በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሐደኝ እግዚአብሔር አንድም ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተርጉሞታል መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ብሎ የባሕርይ ህይወቴ መንፈስ ቅዱስ በእኔ ህልው ነው ወዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ነዳያንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ስለዚህ እነሱ ለጻፉት ኑፋቄ ይህ ማስረጃ ተብሎ ሊጻፍ አይገባውም ነበር ነገር ግን ሰውን ወደ ጥርጥር ለመክተት ተጠቅመውበታል፡፡ “ቀባ” የሚለው ቃል በርካታ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ተመልክተናል እዚህ ላይ ቀብዓኒ ያለውን ያዋሐደኝ ብለው ነው የተረጎሙት፡፡ ስለዚህ ምናልባት ቅብአቶች የራሳቸው ሃይማኖተ አበው የራሳቸው የትርጓሜ መጻሕፍት ሊኖሯቸው ይችል ይሆናል እንጅ የእኛ መጻሕፍት ግን “መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው” ብለው አናገኛቸውም፡፡ ምክንያቱም ኑፋቄ ነውና! አባቶቻችንስ የማይመረመረውን መለኮት መርምሮ በማይደርሰው ኅሊናችን እንመረምር ዘንድ እንደማይገባ አስተማሩን እንጅ በድፍረት የመሰለንን ነገር ለመለኮት እንቀጽል ዘንድ አላስተማሩንም፡፡ ሃ አ ዘቴዎዶጦስ ም 53 ቁ 5 ላይ “ተመርምሮ የማይታወቅ ከሆነስ አለመመርመርን ማወቅ ይገባናል፡፡ ድንቅ ምንድን ነው? የባሕርዩ ሥራ ነው እንጅ ድንቅ እርሱ ከሆነ ድንቅ የሆነ እርሱም ሁልጊዜ ድንቅ በመባል የሚኖር ከሆነ እውቀትን ድንቅ ድንቅ ሥራ በሚሠራ ለፍጥረቱ ሁሉ ገዥ ለእርሱ ተው” ይላል፡፡ ስለዚህ የማይመረመረውን መለኮት እንመረምራለን እያሉ ክህደታቸውን ለሚተፉ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች መልእክታችን ቆም ብላችሁ አስቡ የሚል ነው!
ይቀጥላል…
“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 10
ሰኔ 26/2008 ዓ.ም
     በፌስ ቡክ ስጽፍ የመጀመሪያውን ረዥም ጽሑፍ የጻፍኩት በዚህ ርእስ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ጉዳዩ አሳሳቢ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ስለዚህ እናንተንም ላለማሰልቸት በዚህ ክፍል ይህን ርእስ ለመቋጨት እገደዳለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል በዋናነት የምንመለከተው እስካሁን ያየናቸውን ማጠቃለያ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ማጠቃለያዎችም ለእነርሱ የምንፍቅና ምንጭ በሆኑ ነጥቦች ላይ ነው፡፡
1. መጀመሪያ ክርስቶስ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ለምንፍቅናቸው ተጠቅመውበታል፡፡ ክርስቶስ ማለት በዐረቡ መሢሕ በግዕዙ ቅቡዕ በአማርኛው የከበረ ንጉሥ ማለት ነው፡፡ / ቃለ ጽድቁ ለአብ ገጽ 104/ እንግዲህ ቅብአቶች የተጠቀሙት ቅቡዕ የሚለውን ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ የሚለው ስም ከተዋሕዶ በኋላ ያወቅነው ስም ነው እንጅ ከተዋሕዶ በፊት በዚህ ስም ጠርተነው አናውቅም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ማለት የከበረ ንጉሥ ማለት ነው፡፡ ነገሥታት ሲነግሡ እንደሚቀቡ ሁሉ መለኮትም ተቀብቷል ማለት ግን አይደለም፡፡ ልብ ማለት እዚህ ላይ ነው እነዚህ የጸጋ ነገሥታት ናቸው እርሱ ግን የባሕርይ ንጉሥ ነው፡፡ ዳዊት በመዝሙር 73 ላይ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም” ይለዋል ስለዚህ ክርስቶስ የከበረ ንጉሥ ነው፡፡ ይህም ማለት ራሱን በራሱ ያከበረ ሿሚ ሻሪ የሌለው ንጉሥ ማለት ነው፡፡ ልዩነታችን እነርሱ ሌላ አክባሪ ያስፈልገዋል ነው የሚሉት እኛ ደግሞ ራሱን በራሱ ያከብራል ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ስንል በባሕርይው ህልው ሆኖ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ራሱን በራሱ ያከበረ ንጉሥ ማለታችን ነው፡፡ ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው እንዲል ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ም35 ክ1 ቁ2 ላይ።
2. ተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ ልዩነታቸው ምንድን ነው?በሚለው ጥያቄ ጊዜ የሚያቃጥሉ የቅብአት መናፍቃን በዝተዋል፡፡ ምናልባት “ቅብአት እና በቅብአት ከበረ” የሚሉትቃላት እንደሚለያዩ ስለሚያውቁ ተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ የሚለውም የሚለያይ መስሏቸው ይሆናል፡፡ ተዋሕዶ ማለት ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነበትና የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃልም ገንዘብ ለሥጋ የሆነበት ምሥጢር ነው፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ” ማለትም ህልው ሆኖ በሚኖረው በባሕርይ ህይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን አምላክ አደረገው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ በተዋሕዶ ከበረ የሚለው ትርጉሙ ጊዜ የሚወስድ አይደለም፡፡ እነርሱ ላይ ግን ልዩነት አለው እነርሱ የሚሉት “ተዋሕዶ” ሁለትንትን አጥፍቶ አንድነትን የሚያጸና እንጅ ሥጋን ማክበር አይችልም፡፡ ስለዚህ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ወልድ የባሕርይ ህይወቱ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ገንዘቡ ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ደግሞ ቅብአት ያስፈልጋል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት ስለዚህ ነው፡፡
3. ቀኖና እና ዶግማ ላይ ክርክር አለ፡፡ ዶግማ ማንም የማይሽረው ማንም የማያሻሽለው ማንም የማይለውጠው ማንም የማይቀንሰው ማንም የማይጨምረው ነው፡፡ ቀኖና ግን እንደሁኔታው የሚደረግ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ማንም ደስ እንዳለው ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡ በዓላት አከባበር ላይ አጽዋማት መግቢያና መውጫ ላይ አባቶቻችን አንድ ጊዜ ሥርዓት ሠርተውልናል በዚያ ሥርዓት መሠረት እንመራለን፡፡ ስለዚህ ገና በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ 28 በሌሎች ዘመናት ታህሳስ 29 እንዲከበር በወሰኑልን መሠረት እናከብራል፡፡ በክፍል1 ላማሳየት የሞከርኩት ቀኖናው መከራከሪያ መሆን የለበትም ዶግማው አስተምህሮው ላይ ነው ለማለት ነው እንጅ ወደፊት ታህሳስ 29 ብቻ ይከበራል ብለን እንደ ቅብአት እምነት አራማጆች ምሥጢሩ ሳይገባን አንደመድምም፡፡ ቀኖና ላይ አንድ ምሣሌ ልስጣችሁ ጥምቀት ላይ ወንዶች በተወለዱ በ40 ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ ይላል ነገር ግን ህጻኑ(ኗ) ሳይጠመቁ ለሞት የሚያበቃ በሽታ ቢይዛቸውስ? የግድ 40 እና 80 ቀን ይጠብቃልን? አይጠብቅም በሞግዚት ገብተው ይጠመቃሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥቱን ተመልከቱት፡፡ ሌላም ልጨምራችሁ የጌታችን ጥንተ ስቅለት መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ነው፡፡ በየዓመቱ ስትመለከቱ ግን ድሜጥሮስ በተገለጸለት ባሕረ ሃሳብ ተሰልቶ ስቅለት አርብን ትንሣኤ እሁድን ዕርገት ሐሙስን እንዳይለቅ ሆኖ ይከበራል እንጅ ሁልጊዜ መጋቢት 27 ስቅለትን መጋቢት 29 ትንሣኤውን አክብረን አናውቅም፡፡በየዓመቱ በተለያየ ቀን እናከብረዋለን ለምን ብትሉ ቀኖና ስለሆነ ነው መልሳችን፡፡
4. ቅብአት ማለት መንፈስ ቅዱስ ነው የሚሉት ፈሊጥ አለ፡፡በእውነት መንፈስ ቅዱስን የት ቦታ የትኛው ሊቅ ነው ቅብአት ነው ብሎ ያስተማረው የጻፈው? እኛ የምናውቀው ቅብአት ቀጥተኛ ትርጉሙ ክብር ማለት እንደሆነ ነው እንጅ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ አይደለም፡፡
5. አብ በሰውነቱ በማኅጸነ ማርያም ወልዶታል የሚለው ሦስተኛው የልደት ዓይነት በቤተክርስቲያናችን የትኛውም መጽሐፍ ላይ አልተጻፈም፡፡ እነርሱ የሚጠቅሱት መጽሐፍ አለ ያ መጽሐፍ ግን የራሳቸው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍትን አብነት ማድረግ ይገባናል፡፡ ጥንታዊ ለማስመሰልም የብራና እያሉ የሚጠቃቅሱት አለ፡፡ ይኼ ውሸት ነው ምክንያቱም ሰይጣን እንኳን ይህን ሌላም ያስደርጋልና አሁን የጻፏቸው የብራና መጽሐፍ እንዳለ እረዳለሁ፡፡ የእኛ መጻሕፍት ግን ሦስተኛውን ልደት አውግዘውታል። ኢትዮጵያዊው ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ላይ "ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር ፤ በሰማይ እናት በምድርም አባት የለውም" ይለናል። ሃይማኖተ አበውም ለምድራዊ ልደቱ አባት ለሰማያዊ ልደቱም እናት አትሹለት ይለናል። ስለዚህ በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አንልምና አብ በማኅጸነ ማርያም ወለደው የሚለውን የሰይጣን ትምህርት አንቀበልም።
6. “ማቅ” እና “ካራ” የሚሏቸው ፈሊጦች፡፡ ቅብአቶች ማኅበረ ቅዱሳንን “ማቅ” የተዋሕዶ አማኞችን “ካራ” እያሉ ካራ በሆነ አፋቸው ይሳደባሉ፡፡ እኔ ስጽፍ እስከ ክፍል 10 ድረስ ሁሉንም ማየት ትችላላችሁ አንድም ቦታ ላይ ስለ “ማኅበረ ቅዱሳን” አላነሣሁም፡፡ እነርሱ ግን ጥያቄ ሲጠየቁ እና ዋናው የክህደት መነሻቸው ሲነገር “ማቅ” ወይም “ካራ” ይላሉ ምን ለማለት እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ብዙዎች የተዋሕዶ ልጆች እንዲህ ወደ ስድብ ሲገቡ “አሙካ” ብለው ለቅብአቶች ይመልሱላቸዋል፡፡እነርሱም “አሙካ” ያልከው እኮ መንፈስ ቅዱስን ነው ምክንያቱም “ቅብአት” መንፈስ ቅዱስ ነውና ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ በእውነት ቅብአት መንፈስ ቅዱስ የሚሆነው በምን ተሰልቶ ነው? እኛ ትንሽ ተማርን የምንል ሰዎች ይህንን መለየት የሚከብድ አይመስለኝም ምክንያቱም ቅዱስ ቅብአት የምንለው እንዳለ ሁሉ ቅዱስ ያልሆነ ቅብአትም አለና፡፡ስለዚህ ቅብአት ማለት መንፈስ ቅዱስ ነው ካልን ቅዱስ ያልሆነው ቅብአትም መንፈስ ቅዱስ ነው ልንል ነው ማለት ነው፡፡ገበያ ወጥታችሁ ቅብአት ስትገዙ መንፈስ ቅዱስን ገዛችሁ ማለት ነው በእናንተ ቤት፡፡ ራሳችሁን ፊታችሁን ቅብአት ስትቀቡ መንፈስ ቅዱስን ተቀባችሁ ማለት ነው በእናንተ ቤት፡፡ ይኼ ከንቱ ትርጓሜ ነው እነርሱው የፈጠሩት የመንደር ትርጉም!
7. “በማኅጸነ ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ በአብ ባይወለድ ኖሮ ወልድ እንደ አብ አይገዛም ነበር” የሚለው ክህደታቸው ውላጤን ሚጠትን ትድምርትን ህድረትን የያዘ ነው፡፡
8. አብ ባለበት ወልድና መንፈስ ቅዱስ፣ ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስ ባለበት አብና ወልድ እንዳሉ አለመረዳታቸው፡፡ ወልድ ሥጋን ለበሰ ሲባል ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ሥጋን የለበሰ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ቢለብስም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ግን አልተለየም፡፡
9. ምሥጢራት ላይ ክፍተት እንዳለባቸው ያሳያል፡፡ “ወልደ አብ” የሚለው የክህደት መጽሐፋቸው አእማደ ምሥጢራትንና ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን የሚያፋልስ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሃሳብ ያጠራቀመ የዐቃቤ ድግስ ነው፡፡ እሱን መጽሐፍ አንብቡት ኑፋቄያቸውን በሚገባ ትረዳላችሁ የሚጠቅሱትን ጥቅስ አንድ በአንድ በሚገባ ተመልከቷቸው ሃይማኖተ አበውንም ተመልከቱት ከዚያ የትኛው ትክክል እንደሆነ መርምሩ፡፡
10. በቅብአት ካህን የተጠመቀ ሰው ዳግመኛ መጠመቅ ይገባል አይገባም ለሚለው ጥያቄ መልሱ በደንብ ሆኖ ይገባል የሚል ነው፡፡ ጥምቀት አንዲት ናት አትደገምም አትሰለስም አትከለስም፡፡ ነገር ግን ፍትሐነገሥቱም ሃይማኖተ አበውም እንደሚለው ከመናፍቅ የተጠመቀ ቢኖር ዳግመኛ ይጠመቅ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ ከመናፍቅ የተጠመቀ አማኒ አይደለም ይላል ስለዚህ አማኒ ለመሆን ምን ያስፈልጋል ስንል ጥምቀት ነው መልሱ፡፡ ስለዚህ ከቅብአት ካህን የተጠመቀ ሰው ዳግም መጠመቅ አለበት፡፡ ከዚህ በላይ ክህደት ምን አለ ወልድን ፍጡር እንለዋለን እያሉ እየመሰከሩ እየተከራከሩ! ከተዋሕዶ በኋላ መለኮትንና ሥጋን እየከፋፈሉ፡፡ ሎቱ ስብሐት!!!
11. በመጨረሻ መልእክት አለኝ›››››› “ወልደ አብ” የተሰኘው የኑፋቄ መጽሐፍ የታተመው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥር ባለች ቆጋ ኪዳነምሕረት ገዳም አሳታሚነት በ “መምህር” ገብረመድኅን እንዳለው አዘጋጅነት ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም በምትችሉት አቅም ሁሉ ይህ ለምን እንደተደረገ በያላችሁበት አካባቢ ላሉ አባቶች በተለይ ለጳጳሳትና ለሊቃውንት ጉባኤ አባላት እንድታሳውቁና መፍትሔ በጋራ እንድንፈልግ አሳስባለሁ፡፡ ስለሁሉም ነገር ግን ጸሎት ያስፈልጋልና ሁላችሁም በጸሎት ቤተክርስቲያናችንን አስቧት፡፡ እኔም በሰው ኅሊና ከማይደረስበት መለኮት ጥቂት ነገሮችን ስጽፍ ስጨልፍ ባለማወቅ አጥፍቸ ተሳስቸ ከሆነ ወንድሞቸ አባቶቸ መምህሮቸ በመልካም ትምህርታችሁ አቅኑኝ።
ተፈጸመ፡፡
ለመምህራችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቀጣዩ በሌላ ርዕስ እንመለሳለን፡፡
ደህና ቆዩን፡፡





No comments:

Post a Comment