Tuesday, June 28, 2016

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ዘጠኝ

ክፍል ስምንት የቀጠለ
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
"ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ! ክፉውን ነገር ተጸየፉት…"በሚለው አምላካዊ ቃል መሰረት፤ዝግጅቶቹ የእኛ ባይሆኑም፤ የዓላማ አንድነት እስካለን ድረስ፤በተለያዩ የተዋህዶ ልጆች የሚተላለፉትን፤የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ትምህርትና ወቅታዊ መልእክቶች፤ስናካፋላችሁ እንደነበር ታስታውሳላቸሁ፡፡
ለዛሬ "ወልድ ዋሕድ"/www.weldwahed.blogspot.com/ ከተሰኘው ብሎግ ላይ ያገኘነውን
"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!
በሚል ርዕስ ሦስተኛውንና አራተኛውን ክፍል እንድትመለከቱት እንጋብዛለን፡፡
መልካም ንባብ፡፡

ሙሉ ዘገባው "የወልድ ዋሕድ" ብሎግ ነው፡፡
ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡ማቴ.716 ክፍል ሃያ ሦስት
 "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል ሦስት)
ከክፍል ሃያ ሁለት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
     ‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል ሃያ ሁለት ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ ሁለተኛውን ክፍል ተመልክተን በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡አሁን በገባነው ቃል መሠረት ሦስተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡በመግቢያችንና ቀደም ባሉት ክፍሎች እንደገለጽነው “የእምነት መግለጫ” ሰነዳቸው ብዙ የዋሃን ምዕመናንን ለማሳሳት  በተንኮል የተቀናበረ በመሆኑ ከቃላት አጠቃቀማቸው ጀምሮ ለእያንዳንዱ አንቀጽ መልስ ያስፈልገው ነበር፡፡ሆኖም የእነሱን አካሄድ ተከትለን ብንሄድ፤የእኛንም ሆነ የአንባብያንን ብዙ መልካም ሥራዎችን የምንሰራበትን ጊዜና አእምሮ በከንቱ ማባከን ስለሆነ በጣም ጎላ ብለው የሚታዩት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡
የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሁላችንም እውነትን እንድናስተውል አእምሯችንን ያብራልን፡፡

አንደኛ/ ከመግለጫቸው ገጽ 33 የተወሰደ፦ “ቤተ ክርስቲያን አንዲትና አለማቀፋዊት እንደመሆኗ መጠን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተለያየች ብትሆንም፤ እግዚአብሔር ወዳቀደላት አንድነትና ፍጹምነት እንድትመጣ የተቻለንን እናደርጋለን፡፡” ብለዋል፡፡

ከዚህ በላይ ባለው ሃሳባቸው ውስጥ የሚተኮርባቸው ሃሳቦች፤
1/ “ቤተ ክርስቲያን አንዲትና አለማቀፋዊት” መሆኗን ካመላከቱ በኋላ፤መልሰው በዚያው ዓረፍተ ነገር ላይ ቤ/ክ በየምክንያቱ የተለያየች መሆኗን በመግለጽ ያፈርሱታል፡፡ይህም የእነሱ እምነት ከተለያዩ የመናፍቃን የእምነት ድርጅቶች የተቃረመ ስለሆነ ያንን አሰባስበው ወደ አንድነት ለማምጣት አስበዋል ማለት ነው፡፡ከዚህ ሌላ “አንዲት፣ቅድስት፣ዓለማቀፋዊት…” የሆነችውን የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በጭፍን ከመንቀፍ በስተቀር ማንነቷን የማያውቁ፤ለማወቅም የማይፈልጉ መሆኑን ያጠይቃል፡፡
2/ በእግዚአብሔር ወልድ ደም የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያን ገና ፍጽምት እንዳልሆነች፤ ወደፊት በእነሱ ጥረት እግዚአብሔር ወዳቀደላት አንድነትና ፍጹምነት እንደምትመጣ እየተነበዩ ነውኮ! አይ ክርስትና! አይ ወንጌል ሰባኪነት! ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች ትታደስ የሚሉት አካላት እምነት እንግዲህ እስከዚህ ድረስ ነው፡፡በፈሊጣዊ አነጋገር "ለራሱ የማይበቃ ጠበቃ" እንደሚባለው፡፡

ሁለተኛ ከመግለጫቸው ከገጽ 29-36 ባለ እምነት መግለጫዎቹ ተሐድሶዎች፤ አእማደ ምሥጢራትን በራሳቸው አገላለጽ "መሠረተ እምነት" ብለው ከአምስቱ ምሥጢራት መካከል ሁለቱን ብቻ ገልጸዋል፡፡ይህም ምሥጢረ ሥላሴን “ትምህርተ ሥላሴ፣”ምሥጢረ ሥጋዌን “ትምህርተ ሥጋዌ”…..እያሉ እያድበሰበሱ ካለፉ በኋላ ወጉ እንዳይቀርባቸው ምሥጢራተ ቤ/ክ ብለው ከላይ በተጠቀሱት ገጾች ላይ አስፍረዋል፡፡ በእነርሱ እምነት ምሥጢራተ ቤ/ክ ያሏቸው 3ቱ ማለትም ምስጢረ ጥምቀት ፣ምሥጢረ ቁርባን፣ ምስጢረ ተክሊል  ብቻ ሲሆኑ “ሌሎች ምሥጢራት” ብለው የሰየሟቸውን፤ ምስጢረ ሜሮን፣ምስጢረ ክህነት፣ምስጢረ ንስሃ እና ምስጢረ ቀንዲልን ግን “መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን” ብለዋል፡፡

ወደ ትንታኔው ሳንገባ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል አለብን፡፡ ሁልጊዜ በመደጋገም እንደምንገልጸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት አራማጆች ከሌሎቹ የእምነት ድርጅቶች የሚለዩበት ልዩ ጠባያቸው ኦርቶዶክሳዊ ሳይሆኑ መስለው ለመታየትና ሰዎችን ለማሳሳት ብቻ የሚጥሩ መሆናቸው ነው፡፡ዓላማቸው ይህ ባይሆን ኖሮ የራሳቸው የሆነውን እምነት ብቻ ከመግለጽ አልፈው፤ የማያምኑባቸውን አእማደ ምሥጢራትና ምሥጢራተ ቤ/ክ ስማቸውን እየጠቀሱ "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን" በማለት ባልዘባረቁ ነበር፡፡በዚህ አባባላቸው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ የምትመራበት ትምህርተ ሃይማኖትና ለምዕመናን ጸጋን የምታድልባቸው ምሥጢራተ ቤ/ክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገኙ ናቸው ማለታቸው ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠል በእነርሱ እምነት ምሥጢራተ ቤ/ክ ያሏቸው 3ቱ ምስጢረ ጥምቀት ፣ምሥጢረ ቁርባን፣ ምስጢረ ተክሊልን  እና ቀሪዎቹን 4ቱን ምስጢረ ሜሮን፣ምስጢረ ክህነት፣ምስጢረ ንስሃ እና ምስጢረ ቀንዲልን በተመለከተ እነሱ የሚከተሉትን የተሳሳተ አተረጓጎምና ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ የምትሰጠውን ትርጉም እያስተያየን በማቅረብ በቅደም ተከተል እንስቀምጣለን፡፡
1/ ምስጢረ ጥምቀት
      1.1/ በተሐድሶ እምነት፤ “የጥምቀት ዓላማ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባባር ነው፡፡” አለቀ፡፡በቃ፡፡

እንግዲህ አንባብያን እናስተውል! ያለ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንደማይቻል ወንጌሉ እየተናገረ፤እነሱ ይህን የጌታችንን ቃል ወደ ጎን ትተው የተብብር ማሳያ /ድራማ/ ብቻ አድርገውታል፡፡

       1.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
ሀ/ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ፡፡ዮሐ.3፥ 1-15 ፤ማር፤16፥16
ለ/ ጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ለማግኘትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለመቀበል፡፡የሐ.ሥራ 2፥38
ሐ/ ጥምቀት አሮጌውን ሰውነት አስወግደን በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፡፡ሮሜ.6፥1-11 እና ሌሎችም፡፡

2/ ምሥጢረ ቁርባን
   2.1/ በተሐድሶ እምነት፤
“ምስጢረ ቁርባን የሚያስፈልገው ጌታ እስኪመጣ ድረስ የክርስቶስን ሞትና መከራ ለማሰብ፤ትንሣኤውንም ለመመስከር፤የዳግም ምጽአቱን ተስፋ ለማስታወስ፤ከክርስቶስ ጋርና እርስ በርሳችን ህብረት ለማድረግ ነው፡፡በጌታ እራት መሳተፋችን እስከ ዳግም ምጽአተ ክርስቶስ ሲሆን፤በዚያን ጊዜ በበጉ ሠርግ እራት፤ማለት በጌታ ጋር በሚደረግ የእራት ግብዣ ይጠናቀቃል፡፡”

የተወደዳችሁ አንባብያን! “ጥምቀቱም፣ቁርባኑም፣ሌላውም መታሰቢያ ነው እንጂ ለድህነታችን ምንም አስተዋጽኦ የለውም” የሚለውን ቀልድ በፕሮቴስታነቱ ዓለም ስንሰማው የነበረ፤እነሱም/ተሐድሶዎቹ/ የእነሱው ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመሆናቸው ከዚያው የተቀበሉት በመሆኑ አይደንቀንም፡፡ከዚህ በተጨማሪ ግን እንደምንም ከሌላው የተለዩ ለመምሰል ብለው አዲስ የፈለሰፏት "በጌታ እራት መሳተፋችን እስከ ዳግም ምጽአተ ክርስቶስ ሲሆን፤በዚያን ጊዜ በበጉ ሠርግ እራት፤ማለት ከጌታ ጋር በሚደረግ የእራት ግብዣ ይጠናቀቃል፡፡” የምትለዋ የእራት ግብዣዋ ነገር ነች፡፡ በዚህ አባባላቸው የሐሰተኛው ክርስቶስ መንገድ ጠራጊዎች ለመሆናቸው  ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡እንግዲህ እነሱ ጌታ የሚሉት በብዙ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የክፋቱና የጥፋቱ ሁኔታ ትንቢት የተነገረበት፤በይበልጥም በዮሐ.ራዕይ ምዕ.13 በአውሬው ምሳሌነት የተገለጠው ሐሰተኛው ክርስቶስ መሆኑ ነው፡፡ይህ ዓለሙን ሁሉ በክህደት ትምህርቱ የሚቆጣጠረው ሐሰተኛው ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ42 ወራት  ለመንገሥ ሲመጣ፤እነሱ ቀደም ብለው ቤተ ክርስቲያንን በማጥፋት ሥራ መንገድ ጠራጊዎች ሆነው ስለተገኙለት ምናልባት ምሳም እራትም ሊጋብዛቸው ይችል ይሆናል እንጂ፤እውነተኛው  ጌታ ሰማይንና ምድርን ሊያሳልፍ ሲመጣ  እራት ያበላኛል ብሎ የሚቋምጥ ሃይማኖተኛ ሰው በምንም ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ እንዴ! “አይወልድም፤አይወለድም፤ነቢይ ነው፤” የሚሉት እንኳን እምነታቸው ትክክል ባይሆንም የሚመጣው ለፍርድ መሆኑን ይናገራሉኮ፡፡ጭራሽ ከእነሱም አንሶ መገኘት? ኧረ ተሐድሶ ነን የምትሉ ወደ አእምሯችሁ ተመለሱ! እባካቸሁ ትንሽ እፍረት ይኑራችሁ! በእግዚአብሔር ቃል በደሙ የተመሠረተችዋን ፤የማትፈርሰዋን ቤ/ክ ለማፍረስ ቀን ከሌሊት ከምትደክሙ እስቲ መጀመሪያ እናምንበታለን በምትሉት በ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን የራሳቸሁን እምነት መርምሩት፡፡"በሃይማኖት ብትኖሩ እራሳችሁን መርምሩ" እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡2ኛ ቆሮ.13፥5

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን የምናምነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም የሚነግረን እውነት፤ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም የሚመጣው ለሁሉም እንደየሥራው ሊከፍል ነው፡፡ " እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከኔ ጋር አለ፡፡አልፋና ዖሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው፤መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡" ዮሐ.ራዕይ 22፥12-13፡፡

 2.2/ ምሥጢረ ቁርባን በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
እኛ የተዋህዶ ልጆች ምስጢረ ቁርባን ከሌሎቹ ምሥጢራት ሁሉ በተለየ ሁኔታ ነው የምናከብረው፡፡ምክንያቱም ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሥጋ ተዋህዶ የእኛን ሞት በሞቱ ለመደምሰስ፤በጽንስ የጀመረውን የቤዛነት ሥራ በሞቱ ለመፈጸም ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ እስከ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ብዙው አንድ እየተባለ 13ቱን ህማማት በፈቃዱ ተቀብሎ የሰጠን ስለሆነ ነው፡፡ይኸውም በአይሁድ እጅ በመደብደብ፣በጥፊ በመመታት፣በመገረፍ፣የሾክ አክሊል በመቀዳጀት፣መስቀል ተሸክሞ በመውደቅና በመነሳት፣ በችንካሮች በመቸንከርና በመስቀል በመሰቀል፤በመጨረሻም ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በፈቃዱ በመለየት፤ሥጋውን ቆርሶ፤ደሙንም አፍሰሶ፤እኛ በበደልን እሱ ክሶ የሰጠን ነው ቅዱስ ቁርባን፡፡
ስለሆነም ከቅዱስ ቁርባን የምናገኘው ጥቅም፤
ሀ/  የዘለዓለም ሕይወት ለመውረስ ዮሐ.6፥54
ለ/ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ዮሐ.6፥56
ሐ/ የኃጢአት ሥርየት ለማግኘት፤ማቴ.26፥28
መ/ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ እስኪመጣ ድረስ ሞቱንና ትንሣኤውን እንድንመሰክር፤--1ኛ ቆሮ. 11፥26

3/ ምስጢረ ተክሊል
3.1/ በተሐድሶ እምነት፤
ስለ ምስጢረ ተክሊል ዓላማውንም ሆነ ጥቅሙን ሳይገልጹ “ወንድ ለወንድ ወይም ሴት ለሴት የሚፈጸም ጋብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ የተከለከለና አጸያፊ ርኩሰት ስለሆነ በእግዚአብሔር ቃል እንቃወማለን፡፡”ብለዋል፡፡እዚህ ላይ ስለ ምስጢረ ተክሊል ጀምረው ወደ ግብረ ሰዶም ተቃውሞ የሄዱበትን ጉዳይ ማንሳቱ አሰፈላጊ ነው፡፡እነዚህ ቤ/ክ እናድሳለን ባዮች በተለያዩ ግለሰቦችና ማህበራት ስም የተመሰረቱ ናቸው፡፡የሁሉም  ዋነኛ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖትን ማጥፋት ሲሆን በየራሳቸው ደግሞ ልዩነት አላቸው፡፡ከነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዱ የግለሰብ ድርጅት በዚህ የግብረ ሰዶም ልክፍት መያዙንና በጓደኝቹ ተመክሮ ተመክሮ አልመለስ ማለቱን የራሰቸው ድረ-ገጽ “አባ ሰላማ” አስነብቦናል፡፡/ያልሰማን መስሏቸው ነው?/

አንባብያን እንግዲህ ልብ በሉ፤ይህንን በኖህ ዘመን የሰው ልጅ በንፍር ውሃ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ያደረገውን፤በሎጥ ዘመን ደግሞ ሰዶምና ገሞራ የተባሉትን ከተሞች በእሳት እንዲጠፉ፤ደረገውን አጸያፊ የዝሙት ኃጢአት እየሰሩ ነው ወንጌል እንሰበካለን የሚሉት፡የተዋህዶ ልጆች እባካችሁ እንንቃ! እኩይ ዓላማቸውንም እንቃወም!

3.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
ምሥጢረ ተክሊል፦አንድ በንጽህና በድንግልና የኖረ ወንድና አንዲት በንጽህና በድንግልና የኖረች ሴት በጸሎተ ተክሊልና በቅዱስ ቁርባን ጋብቻ አንድ የሚሆኑበት ምሥጢር ሲሆን መነሻዎቹ አዳምና ሔዋን ናቸው፡፡ ዘፍጥ.2፥22-24፡፡
ዓላማውና ጥቅሙም፦ ለመባዛትና ምድርን ለመሙላት፤/ ዘር ለመተካት/ ዘፍጥ.1፥28፣ ከዝሙት ለመጠበቅ 1ኛ ቆሮ.7፥2፣ለመረዳዳት ዘፍጥ.2፥18 ሲሆን፤ የቅዱስ ጋብቻ ክቡርነት ለክርስቶስና ለቤ/ክ ምሳሌ እስከ መሆን ድረስ ከፍ ያለ ነው፡፡ኤፌ.5፥22-33

4/ “ሌሎች ምሥጢራት” ብለው የጠቀሷቸው፦ምስጢረ ሜሮን፣ምስጢረ ክህነት፣ምስጢረ ንስሃ፣ምስጢረ ቀንዲል፤ 
4.1/ በተሐድሶ እምነት፤
ከላይ የተጠቀሱትን 4ቱን ምሥጢራት " መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረኑበት መንገድ እንጠቀምባቸዋለን" ከማለት በስተቀር የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡

4.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት
የሁላችንም ዳኛ መጽሐፍ ቅዱስ ስለነዚህ ምሥጢራት የሚለውን ቀጥለን እንመልከት፤
1/ ምስጢረ ሜሮን፦ "እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፡፡…..1ኛ ዮሐ.2፥20፡፡
2/ ምስጢረ ክህነት፦ …"ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡/ሥልጣነ ክህነትን/፡፡ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡"ዮሐ.20፥21-23፡፡በተጨማሪ ማቴ.16፥18-19፣ ዮሐ.21፥15-17፣የሐ.ሥራ.20፥28 ማንበብ ይቻላል፡፡
3/ ምስጢረ ንስሃ፦ ከምሥጢረ ክህነት ጋር የተያያዘ ሲሆን "ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል" በሚለው ቃል መሰረት ኃጢአተኛው ጥፋቱን አምኖ ሲጸጸት ለካህኑ ይናዘዛል፤ካህኑ አስፈላጊውን ሥርዓት አስፈጽሞ እግዚአብሔር ይፍታህ ሲለው ሥርየት ያገኛል፡፡ኑዛዜን በተመለከተ ያዕ.5፥16፣…፡፡
4/ ምስጢረ ቀንዲል፦ "ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤ/ክ ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራ፤በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት፡፡"የያዕ.መል. 5፥14

ማሳሰቢያ ለአንባብያን፤ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረኑበት መንገድ" በማለት ላቀረቡት ጭፍን አስተሳሰባቸው መልስ ለመስጠት ያህል እንጂ እንደ ውቅያኖስ የሰፋውን የቤ/ክ ትምህርት ለማስተማር ስላልሆነ ተገቢውን ትምህርት ወደ ሊቃውንት በመቅረብ እንድንማር እግረ መንገዳችንን እንመክራለን፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡ማቴ.716 ክፍል ሃያ አራት
 "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል አራት)
ከክፍል ሃያ ሦስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል ሃያ ሦስት ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ ሦስተኛውን ክፍል ተመልክተን በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡በገባነው ቃል መሠረት አሁን አራተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡

ሦስተኛ-ከመግለጫቸው ገጽ 37-ነገረ ማርያም፦
5.1/ በተሐድሶ እምነት፤
1/ "በትውፊታዊ ታሪክ ትውልዷና ነገዷ የተገለጠው ቅድስት ድንግል ማርያም….. “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤መንፈሴም በአምላኬ በመድሐኒቴ ሐሴት ታደርጋለች እንዳለችው በልጇ በወዳጇ ቤዛ መሆን ከዳኑት ቅዱሳን አንዷ እንደሆነች እናምናለን፡፡” ብለው ደግሞ ሌላ አስገራሚ ክህደት ጽፈዋል፡፡

እንደ እነ አስራት ገ/ማርያምና ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስን የመሳሰሉት ቀደም ያሉት አሳቾች፤ ክብር ምሥጋና ይግባትና እመቤታችን የውርስ ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ ነበረባት፤መልአኩ ትጸንሻለሽ ብሎ ባበሰራት ጊዜ ኃጢአቱ ተወግዶላት ጌታን ጸንሳለች እያሉ ለሚዘላብዱበት ልብ ወለድ ሃሳባቸው የቤ/ክ ሊቃውንት መልስ እየሰጡ አፋቸውን አዘግተዋቸው ኖረው ነበር፡፡ዛሬ ደግሞ ሁሉም ዝም ባለበት ሰዓት የነሱ ቡችሎች ክህደቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ አሳድገው፤ "በልጇ በወዳጇ ቤዛ መሆን ከዳኑት ቅዱሳን አንዷ ነች" ብለው አረፉት፡፡ይገርማል! በነሱ ቤት የወላዲተ አምላክን ክብር ዝቅ ያደረጉ መስሏቸው ነው፡፡ግን ከእሷም አልፈው ተርፈው ወልደ እግዚአብሔር የተዋሐደው ሥጋም ያው መርገም ነበረበት ማለታቸው ነው፡፡ታዲያ ለእነዚህ ምን ዓይነት መልስ ቢሰጣቸው አምነው ይቀበላሉ? ከመጸሐፍ ቅዱስም ሆነ በአጠቃላይ ከክርስትናው መንፈስ ጋር የሰማይና የመሬትን ያህል የተራራቁ ስለሆኑ፤ ለመወያየትም ለመከራከርም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

5.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት 
የእመ አምላክ፤ የወላዲተ አምላክ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አጠቃላይ ትምህርት በዚህ ርዕስ ሥር ለመግለጽ የሚሞከር ባለመሆኑ አሁንም ወደ ሊቃውንት ቀርበን እንድንማር እያሳሰብን፤ወደዚያ የሚያመራንን ጥቂት ጥቅሶችን ብቻ እንመለከታለን፡፡
1/ ተኩላዎቹ /ተሐድሶዎቹ/  "እመቤታችን ትውልዷና ነገዷ በትውፊት ብቻ የተገለጠ ነው" እንደሚሉት ሳይሆን፤በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ምሳሌና ትንቢት ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፤ ተስፋ ፍጸሜ ሲያገኝ ደግሞ ፤በማቴ.1፥1 ከአብርሃም በመጀመር እስከ እጮኛዋ/ጠባቂዋ/ ዮሴፍ ድረስ፤በሉቃ.3፥23 ከጠባቂዋ ከዮሴፍ ጀምሮ ወደ ላይ አስከ አዳም ድረስ የተቆጠረው ዘር አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችው የእመቤታችን ትውልድና ነገድ ዝርዝር ነው፡፡በቅዱስ ዮሴፍ በኩል የተቆጠረውም፤በእስራኤላውያን ህግ በሴት በኩል ዘር ስለማይቆጠር ነው፡፡እነሱ ይህንን የወንጌል ቃል ለማን ሊሰጡት ይሆን? ምናልባትም ቃሉ የሚለው  የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ ነው የሚሉ ከሆነ፤ እኛ ደግሞ ጌታ ከማን ተወለደ ብለን እንጠይቃቸዋለን?

2/ እመቤታችን የውርስ ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ አላገኛትም፡፡
ሀ/ "…እግዚአብሔር ዘርን ባያሰቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር…" ኢሳ.1፥9፡፡የዚህ ትንቢት ፍጻሜ "የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም..፡፡"ዕብ.2፥16 የሚለው ሲሆን፤ መርገም ያልወደቀባት ንጽህት ዘር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን ብሉይ ኪዳኑም አዲስ ኪዳኑም በመተባበር አረጋግጦልናል፡፡
ለ/ "መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፤ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤አንቺ ከሴቶች መካካል የተባረክሽ ነሽ አላት"  ሉቃ.1፥26 ይላል፡፡/ምዕራፉን በሙሉ ያንብቡ / ይህም ቅዱስ ገብርኤል ወደ እርሷ እንደገባ የመጀመሪያው ሰላምታ "ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ"…የሚለው ቃል እንከን የሌለባት፣ንጽህት፣ቅድስት መሆኗን ያረጋግጣል፡፡ይህንን የተሟላ ክብርና ቅድስና የሰጣት ለተዋህዶ የመረጣት እራሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው እንጂ እኛ የተዋህዶ ልጆች ስለወደድናት ብቻ የሰጠናት ክብር አይደለም፡፡
እንግዲህ ከዚህ ከቅዱስ ገብርኤል ቃል በተቃራኒው የሚናገር ሁሉ ከእውነት የራቀ፤ሃሳቡም ቅዠት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

እንዲያው ለነገሩ የጥርጥርና የክርክር ዘመን ላይ መሆናችን ነው እንጂ፤ያልተጻፈ እያነበቡ፣የተጻፈውንም ያልሆነ ትርጉም እየሰጡ፣የማያስፈልግ ምርምር ውስጥ እየገቡ፣ ለራስ ግራ ተጋብቶ ሌላውን ግራ ከማጋባት ይልቅ፤  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንዳለው "ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም" ብሎ በቀና ልቡና መቀበሉ የተሻለ ነበር፡፡እግረ መንገዳችንን  መልአኩ ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ ከመርገም አነጻት የሚሉትን እነ አስራት ገ/ማርያምን፤ለመሆኑ በመላእክት ቃል ጥንተ አብሶ የሚሻር ከሆነ ለምን ጌታችን ሰው መሆን፤ለምንስ ደሙን ማፍሰስ አስፈለገው? ብለን እንጠይቃቸዋለን! ግን ከነሱ መልስ አንጠብቅም!

አራተኛ- ከመግለጫቸው ገጽ 39 ያሰፈሩት አጽዋማትን በተመለከተ ሲሆን፦ጾመ ፍልሰታ ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበሉ፣ባለፈ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ያሏቸውንም አጽዋማት መፈተሸ እንዳለባቸው፣ጾመ ነቢያትና ጾመ ሐዋርያት ደግሞ መታሰቢያው እንዳይጠፋ ብቻ በጾሙ መጨረሻ ያለው አንድ ሳምንት ብቻ ቢጾም፤የሚል ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ይህንን ያሉት ያው እንደተለመደው ለማስመሰል ያህል ነው እንጂ በአጠቃላይ ጾምን እንደማይቀበሉ በተለያዩ ጹሁፎቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡የማያምኑበትን ጾም ከመተቸትና ማስተካካያ ከመስጠት ጥቅልል አድርገው ጾም አያስፈልግም ቢሉ የተሻለ ነበር፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት ስንመለከት ግን ፤በአጭር አገላላጽ፤/ ወደ ዝርዝሩ ለመግባት ርዕሳችን ስለማይፈቅድልን / ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ጾሞ እንድንጾም፤ጸልዮ እንድንጸልይ በአጠቃላይ መልካም ሥራዎችን ሰርቶ እኛም እንድንሰራ አዝዞናል፡፡ወደፊት ለፍርድ ሲመጣም ዋጋችንን የሚከፍለን እንደየስራችን መሆኑን አስረግጦ ነግሮናል፡፡በመሆኑም ከጾም ጀምሮ ሌሎችም ምግባረ ሰናያት በአግባቡ ከተፈጸሙ ለሥጋችንም ለነፍሳችንም ጠቃሚዎች ናቸው፡፡

ከዚህም ሌላ ከመግለጫቸው በገጽ 25 ላይ "የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና" ብለው ባስቀመጡት ዝርዝር ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ አንቀበልም ብለዋል፡፡/ይሄ መብታቸው ነው፤የሉተር ልጆች ስለሆኑ ከዚያም ማሳነስ ይችላሉ/ በዚህኛው ርዕስ ሥር   በገጽ 43 ደግሞ፤ ስሙን ብቻ እንጂ ትርጉሙን፣ ምሥጢሩንና ጥቅሙን የማያውቁትን ማሕሌቱን፣ ሰዓታቱን፣ ቅዳሴውን፣ ቅኔውን፣ ዜማውን፣ ምጽዋቱን፣ አስራቱን፣ በኩራቱን፣ በዓላቱን፣የአብነትና የነገረ መለኮት ትምህርቶችን፣ገድላቱን ድርሳናቱን /አዋልድ መጻሕፍቱን/ ሌሎችንም ሁሉ "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን" በማለት በማይመለከታቸው ጉዳይ ገብተው ሲጨነቁና ሲጠበቡ ይታያሉ፡፡
አቤት ድፍረት! አቤት ባዶ ጩኸት! አቤት ግራ ተጋብቶ ግራ ማጋባት! ለመሆኑ በየትኛው እውቀታቸው ነው ይህንን ሁሉ የቤ/ክ ዶግማውን፣ ቀኖናውን፣ትውፊቱን፣ ዜማውን፣ ቅኔውን፣ ድርሳናቱን፣ ገድላቱን፣…ወ.ዘ.ተ መርምረው! በመጽሐፍ ቅዱስ መዝነው! የሚቀበሉትንና የማይቀበሉትን የሚለዩት? በዚህ ከንቱ ውትወታቸውስ እነማን ይታለላሉ ብለው ይሆን እንዲህ የሚደክሙት?

በጣም የሚገርመው ደግሞ "አባ ሰላማ" በተባለው ድረ-ገጻቸው ላይ በፈረንጆቹ አቆጣጠር Thursday, June 23,2016 በለጠፉት ጹሁፍ፤ድርሳናትንና ገድላትን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡፡"…በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የሆኑና ቤተክርስቲያኒቱ ከወንጌል ጋር አንዳንዴም ከወንጌል በላይ ስፍራ የምትሰጣቸው ትውፊቶች፣ድርሳናት፣ገድላት ከዚያም ባለፈ ልዩ ልዩ አስማትና ተረቶች የእግግዚአብሔርን የክብር ሥፍራ ወስደውና ጋርደው መገኘታቸውን ያስተዋሉና ከውስጥ የተነሱ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ከነበሩበት ሁኔታ እየሰፉና እያደጉ መጥተዋል፡፡ " / በነገራችን ላይ "አባ ሰላማ" ተብየው ድረ-ገጻቸው ላይ የሚለጥፉት ጽሁፍ ከስድብ፣ ከአሉባልታና በሬ ወለደ ከማለት ያልተናነሰ የግለሰቦችን ስም ከማጥፋት በስተቀር ቁም ነገር የሌለው መሆኑን እግረ መንገዳችንን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡/
አንባቢዎች እዚህ ላይ ልብ በሉ እንግዲህ! በዚያው በአንድ እራሳቸው ስንት ምላስ እንዳለቸው! "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን" ያሏቸውን መጻሕፍት "የእግግዚአብሔርን የክብር ሥፍራ ወስደውና ጋርደው መገኘታቸውን…" በማለት መልሰው እንደ እንቧይ ካብ ይንዱታል፡፡ይህንን ሁሉ ለማሳየት የፈለግነው እንኳን ወንጌል አስተምረው ሌላውንም ወደ እውነት ሊመሩ ይቅርና ለራሳቸውም የሚመሩበት ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ አቋም የሌላቸው መሆኑን ሁሉም ሰው እንዲረዳው ለማደረግ ብቻ ነው፡፡
እንዴ! አይገርማችሁም? አሁን ያሉት የተሐድሶ ድርጅቶኮ እኛ እያየናቸው የተመሰረቱ ናቸው፡፡ገና 30 አመት እንኳን አልሞላቸውም፡፡እባካችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በጭፍን ከመንቀፋቸሁ በፊት በቀና ልቡና ሆናችሁ ተማሩ፤ያልገባችሁን ጠይቁ፤አትቸኩሉ፤ሃይማኖቱ ካልተመቻችሁ ደግሞ በመሰላችሁ መንገድ መሄድ እንጂ በግድ የተያዛችሁ ይመስል የማታምኑበት ቤ/ክ ውስጥ ሆናችሁ አታውኩን እያልናቸው ነበር፡፡ግን አልሰሙንም፡፡ምክንያቱም እነሱ የተሰማሩት ለመንፈሳዊ ሥራ ሳይሆን፤በመንፈሳዊ ካባ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ሌላ ደባ ለመፈጸም ስለሆነ፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ከአዲስ ኪዳን ጀምረን እንኳን ብንቆጥር 2000 ዘመናት ያሳለፈችውን ቀጥተኛይቱን የተዋህዶ ሃይማኖት የሚተቹት፣የሚነቅፉትና የሚሳደቡት!

የማጠቃለያ መልእክት
እንግዲህ "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን! በሚል ርዕስ በአራት ተከታታይ ክፍሎች ከብዙው በጣም በጥቂቱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክረናል፡፡ባለ 44 ገጹ የእምነት መግለጫቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ለመመዘንም እንኳን የማይበቃ ባዶ የቃላት ጋጋታ፣ ፉከራና ስድብ ብቻ መሆኑን ቁልጭ አድርገን አሳይተናል፡፡ተገቢውን ምላሽ ግን ከኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሊቃውንት እንጠብቃለን፡፡በእኛ በኩል ለጥፋት መልእክተኞቹ ለተሐድሶዎች አጭር መልእክት አስቀምጠን ርዕሳችንን እንቋጫለን፡፡
ለተሐድሶዎች እንቅስቃሴ አራማጆች በያላቸሁበት፤
እባካችሁ !
በብእር ስምና በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ጀርባ ተደብቃችሁ፤
በተለያዩ የቤ/ክ አገልግሎት ክፍሎችና በየአጥቢያ ቤ/ክ ተሰግስጋቸሁ፤
በማታመኑበት እምነት ውስጥ አዩኝ አላዩኝ በማለት እየተጨነቃችሁ ፤
የእመቤታችንና የቅዱሳን ስም ሲጠራና መስቀል ስታዩ እየበረገጋችሁ፤
ማህሌቱን ቅዳሴውን ስትሰሙ እየተቃጠላችሁ፤ የምትኖሩት እስከ መቼ ነው?
ከተደበቃችሁበት ውጡና ፊት ለፊት እንነጋገር፡፡ሃሳባችሁን በመናገራችሁ ተፈለጡ ተቆረጡ የሚላችሁ የለም፡፡ብዛ ቢል ስህተታችሁን ካመናችሁ ንስሃ ግቡ፤ ካላመናችሁ ደግሞ የማታምኑባትን ቤ/ክ ለቃችሁ ውጡ ብትባሉ ነው ፡፡በእውነት በወንጌል የምታምኑ ከሆነ  አስመሳይነት በሃይማኖት ውስጥ ቦታ ስለሌለው ኮራ ብላችሁ እራሳቸሁን ችላችሁ እምነታችሁን በአደባባይ ስበኩ፡፡ለአዳራሽ ኪራይና ለአጠቃላይ እንቅስቃሴያችሁ ሙሉ ወጪ የሚሸፍኑ ፈረንጆች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ገንዘቡን ለቤ/ክ ማጥፊያ ከምትበትኑት ለራሳችሁ የሚጠቅም ነገር ብትሰሩበት ይሻላል፡፡ እኛ ግን ያለችን አንድ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ሃይማኖታችንም መተኪያ የሌላት አንዲት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብቻ ስለሆነች ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ እጃችሁን አንሱ! እያልን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡
ለቀጣዩ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡
አነሳስቶ ላሰጀመረን ፤አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ምሥጋና ይድረሰው፡፡








No comments:

Post a Comment