Saturday, June 11, 2016

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1

ክፍል ሰባት
ክፍል ስድስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
     ይህንን "እምነ ጽዮን" ብለን የሰየምነውን የመወያያ መድረክ ስንጀምር “ጆሮ ያለው መሰማትን ይስማ”  በሚል ርዕስ ፤በአራት ተከታታይ ክፍሎች፤ እንዲሁም "ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ"በሚለው ርዕስ በስድስት ተከታታይ ክፍሎች፤ ባቀረብነው ጽሁፍ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን በበላይነት የሚመሩት ክፍሎች እያደረሱ ያለውን ጥፋት በማሳየት ከእኛስ ምን ይጠበቃል በሚል ማጠቃለያ ሰፊ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡አንባብያን ሀሳቡን በጥሞና እንድትከታተሉት በማሰብና ዛሬ ለምንወያይበት ርዕስም አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው "ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ"በሚለው ርዕስ በክፍል አራት ያቀረብነው ጥሁፍ እንዳለ አምጥተነዋል፡፡

(www.emenetsion.blogspot.com Tuesday August 14,2012)  
"ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ" ማቴ ፳፬ . :: ክፍል
      የተከበራቸሁ አንባብያን ከላይ በተጠቀሰው ርእስ በሶስት ክፍሎች እንዳነበባችሁት በፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ በኢ///ቤተ ክርስቲያን ስም የተዘጋጀው  የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ስርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት የተባለው የኑፋቄ መጽፍ በነገረ ማርያምና በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ላይ የሚያስተላልፈውን የተሳሳተ መልእክት ከብዙው በጥቂቱ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ጽሁፍ  ደግሞ የምሥጢረ ሥጋዌን ትምህርት የሚያፋልሰውን ክፍል እንመለከታለን::
     ፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስና ተከታዮቻቸው ተዋህዶ ሃይማኖታቸንን ለመበረዝና ለመከለስ ብሎም ለካቶሊክና ለሌሎች የመናፍቃን ድርጅቶች የገቡትን ቃል ለመፈጸምና እኛን ለማታለል ሲነሱ የሄዱበት የተንኮል መንገድ በጣም ያስገርማል:: (ዝርዝሩን በኋላ እንመጣበታለን ) ይኸውም በመጽሐፉ ከገጽ 82-97  የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ቅድመ  ክርስትናና በዘመነ ክርስትና የነበራት የውጭ ግንኙነት በሚለው ርዕስ ቤተ ክርስቲያናችን የምትቀበላቸውን ሦስቱን ጉባኤያት ማለትም
1/  325 . 318 ሊቃውንት ተሰብስበው  ወልድ ፍጡር ነው” የሚለውን አርዮስን ያወገዙበትን ጉባዔ ኒቅያን
2/ በ381 ዓ.ም 150 ሊቃውንት ተሰብስበው “  መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል” የሚለውን መቅዶንዮስን ያወገዙበትን ጉባዔ ቁስጥንጥያን
3/ በ431 ዓ.ም 200 ሊቃውንት ተሰብስበው “  እመቤታችን ወላዲተ አምላክ አትባልም ክርስቶስም ሁለት አካልና ሁለት ባህርያት አሉት” የሚለውን ንስጥሮስን ያወገዙበትን ጉባዔ ኤፌሶንን በመጠኑ ካሳዩ በኋላ በ451  . የተሰበበውን፤  ለቤ/ ሁለት መከፈል ምክንያት የሆነውንና የኢ////  የማትቀበለውን የኬልቄዶንን ጉባዔ ግን  በዝምታ አልፈውታል::በገጽ 98 ደግሞ የኢ//// የውጭ ግንኙነት ከኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ በማለት ይጀምራሉ:: እዚህ ላይ እንግዲህ ስለ ኬልቄዶን ጉባዔ ማብራሪያ ሳይሰጡ ያለፉት ቀጥሎ ለሚያመጡት የክህደት ስራቸው ምስክር እንዳይሆንባቸው በማሰብ ነው:: የማይገለጥ የተከደነ ስለሌለ እነሱ በዚህ ሁኔታ ይለፉት እንጂ  በኢ//// ነገሩ ከሆነ ጀምሮ ስለምታውቀው ይህ የክህደት ትምህርት ወደ / እንዳይገባ  አጥሯን አጥብቃ ስትከላከል ቆይታለች:: ሆኖም የእኛ ሳይሆኑ እኛን መስለው በዲቁና፤በቅስና፤በምንኩስናና በጵጵስና እንዲሁም በሊቀ ጵጵስና ደረጃ ሳይቀር በተሰየሙ የቤ/ አገልጋዮች አማካይነት በፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ  ይህን አባቶቻችን ያወገዙትን የክህደት ትምህርት ወደ ቤ/ክ በማስገባታቸው የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ይህ ነው ብለን ለይተን ለመናገር የማንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል::በዚህ አጭር ጽሁፍ አወዛጋቢውን የኬልቄዶን ጉባዔ ዝርዝር ጉዳይ ለማሳየት ስለማይቻል ለግንዛቤ ያህል ብቻ ጥቂት እንመለከታለን::
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የኬልቄዶንን ጉባዔ የማትቀበልባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች
1/ በ431 ዓ.ም 200 ሊቃውንት ያወገዙትን “ ክርስቶስ ሁለት አካልና ሁለት ባህርያት አሉት”የሚለውን የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት በማደስ  ልዮንና ተከታዮቹ ክርስቶስን አንድ አካል ሁለት ባህርይ” በማለታቸው ሲሆን በሌላ አገላለጽ አካል የሌለው ባህርይ ስለሌለ ባህርይውን ሁለት ካሉ አካሉንም ሁለት ማለታቸው ስለሆነ::
2/ ጉባዔውን ያዘጋጁት ክፍሎች እራሳቸው መናፍቃን ስለሆኑ
3/ ንጉሡ መርቅያንና ንግሥቲቱ ብርክልያ በማያገባቸው የሃይማኖት ጉዳይ ገብተው ለራሳቸው ዝና ለማትረፍ  ቻ ሲሉ ያዘጋጁት ጉባዔ ስለሆነ
4 /እንደ ሦስቱ ጉባዔያት የጉባዔው ዓላማ በግልጽ ታውቆ አውጋዡና ተወጋዡ ያልተለየበት በመሆኑ
5/እውነተኞቹ የሃይማኖት አባቶቻችን እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በጉባዔው የመናገር እድል እንኳን  ሳይሰጣቸው ተገፍተውና ተደብድበው እንዲገለሉ የተደረበት ስለሆነ
    በነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ይህ ጉባዔ "ጉባዔ ከለባት" ወይም “የውሾች ጉባ" ተብሎ ይጠራል::ይህም አባባል ዲስ አይደለም ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ የቤ/ክንን ሰላም ከሚያውኩ መናፍቃን እንድንጠበቅ ” ከውሾች ተጠበቁ፤ከክፉዎች ሰራተኞች ተጠበቁ፤----”(ፊሊጵ. 3፥2) በማለት አስጠንቅቆናል::
    እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ  ከራሳቸው አልፈው የኢ////ክንን የካቶሊክና የሌሎቹም የመናፍቃን ድርጅቶች አባል ለማድረግ አልመው የተነሱት አባ ጳውሎስና ተከታዮቻቸው” ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነች ይሏታል እንድሚባለው የኬልቄዶንን ጉባዔ ውግዘት ምክንያቱ እስከ ዛሬ የማይታወቅ ይመስል ስለ ውግዘቱ አዲስ ጥናት እንዳደረጉና የጥናቱንም ድምዳሜ ለመግለጽ በመጽሐፉ ከገጽ 105 - 111 ደረስ ካቀረቡት ጽሁፍ ውስጥ ለግንዛቤ ያህል አለፍ አለፍ ብለን እንመለከታለን::
ምእራፍ 27 ገጽ 108—111 (በከፊል)
"በኦየንታል  ኦርቶዶከስ አብያተ ከርስትያናትና በምስራቅ  ኦርቶዶከስ አብያት ክርስትያናት መካከል ምሥጢረ ሥጋዌን ተመለከተ የተደረገ ውይይት
    የክልቄዶን ጉባኤ  እስክተደረገበት እስከ 451 . ድረስ ቤተ ክርስቲያን በእምነትና በሥርዓተ አምልኮት አንዲት እንደነበረችና አሁንም ክርስቶስ አንድ እስከሆነ ድረስ ቤተክርስቲያንም ምንግዜም አንድ እንደሆነች መላው የክርስትና ዓለም ያምናል:: ከኬልቂዶን ጉባኤው በኋላ ግን በጉባዔው ላይ በምሥጢረ ሥጋዌ ምክንያት ቤተክርስቲያን ለሁለት ተከፋፍላ ቆይታለች:: ለመለያየትም ምክንያት የነበረው ዐቢይ ነጥብ የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት  ወገኖች ስለ ክርስቶስ ምሥጢረ ሥጋዌ ያላቸውን እምነት “በአንድ አካል ሁለት ባህርይ : ሁለት ፈቃድ ሁለት ግብር” በሚል ቃል ሲገልጹ የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ “ አሐዱ ባህርይ ዘእግዚአብሔር ቃል ሥግው” የሚለውን የቅዱስ ቄርሎስን የእምነት አገላለጽ መሠረት በማድረግ “ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን  ከነፍሷዋ ነፍሱን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ ያለመከፋፈል ፤ያለመነጣጠል ፤ያለመጠፋፋት ፤ያለመለወጥ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ በተዋህዶ ነው” ብለው እምነታቸውን ስለሚያረጋግጡ ነው::
     ይህ የእምነት አገላለጽ ልዩነት ከኬልቄዶን ጉባኤ 451 . እስከ አለንበት ዘመን ድረስ ለረጅም ጊዜ አለያይቶን ቆይቷል::
      ይሁን እንጂ በአሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ለልዩነቱ ምክንያት ሆኖ የቆየው ይህ የምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ሆኖ እያለ በምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ቤተ ክርስቲያን ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት የሆነው በቃላት የአገላለጥ ልዩነት እንጂ በሁለቱም በኩል የተዋህዶው መሠረተ እምነት አንድ መሆኑ ተጠቅሶ ወደፊት ወደ አንድነት ሊያመጣ የሚችል የጋራ ውይይት መድረክ ተደረገ:: በዚሁ መሰረት ይፋ ያልሆኑና ይፋ የሆኑ ሰባት የጋራ ጉባኤያት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ተካሂደዋል::
ጉባኤያቱም:
1/ በአርሁስ ዴንማርክ እ..አ ነሐሴ 11 - 15 ቀን 1964
2/ በብሪስትል ኢንግላንድ እ..አ ነሐሴ 25 - 29 ቀን 1967
3/ በጄንቫ ስዊዘርላንድ እ..አ ነሐሴ 16 - 21 ቀን 1971
4/ በአዲስ አበባ ኢትዮጲያ እ..አ ጥር 21 - 22 ቀን 1971
5/ በአባይ ቢሾይ ገዳም ግብጽ እ..አ 1989
6/ ቻምቤዚ ስዊዘርላንድ እ..አ 1990
7/ ቻምቤዚ ስዊዘርላንድ እ..አ ህዳር 1-6 ቀን 1993 የተካሄዱት ነበሩ::
በነዚህ ጉባኤያት ሁሉ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ በመልዕክተኞቿ መሰረት ተሳትፋለች::
    በጉባኤያቱ ሁሉ የክልቀዶኑ ውግዘት መነሻ ምክንያቶች ተመርምረዋል:: በመጨረሻም ቻምቤዚ ስዊዘርላንድ  ህዳር 1-6 ቀን 1993 . .. በተደረገው ጉባኤ በምሥጢረ ሥጋዌ ስለ ክርስቶስ ተዋህዶ የሚሰጠው ትምህርት ልዩነት በሁለቱም ወገኖች የቃላት አገላላጽ እንጂ የእምነት አለመሆኑን ተገንዝበዋል:: ንስጥሮስንና አውጣኬን ግን የሁለቱም ወገን አብያተ ክርስቲያናት የሚያወግዟቸው መሆኑን ተገልጿል:: በመጨረሻዎቹ ሶስት ጉባኤያት ላይ በሁለቱም ወገን ያሉትን ውግዘቶች ማንሳት ስለሚቻልበት ሁኔታ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል:: ...
    ስለዚህም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ባሁኑ ጊዜ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብ : ከመለያየትም ይልቅንድነት መተሳሰብና መረዳዳት ጊዜው የሚጠይቀው መንፈሳዊና ማህበራዊ ግዴታ ከመሆኑም በላይ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው የምሥጢረ ስጋዌ ትምህርት ልዩነት ከሚወገድበት ደረጃ ላይ እንዲህ ከተደረሰ በእምነትና በሥርዓት ከሚመስሏት እህት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በአንድነት መክራ ወደ ፊት በሚደረገው ጉባኤ አንድ አካል ሁለት ባህርይ በተዋህዶ  ከማለት ይልቅ ያለመከፋፈል ፤ያለመነጣጠል ፤ያለመጠፋፋት ፤ያለመለወጥ (በተሃቅቦ) ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ በተዋህዶ  አሐዱ ባህርይ ዘእግዚአብሔር  ቃል ሥግው በሚለው እምነት ከአንድነት ደረጃ ላይ ቢደረስ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የመቀራረቡን ሃሳብ የማትቃወም መሆኗን ታረጋግጣለች::"
 ተጨማሪ ማስገንዘቢያ፤
ከዚህ በላይ ያቀረብነው በ1988 ዓ.ም በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ ከታተመው የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ስርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 82-97 ላይ ያለው ጽሁፍ፤ በ2000 ዓ.ም በታተመው "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም (2000) " በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 12 ክፍል 5 ገጽ 302 ላይ ካለው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን፤ይህም የጥፋት አድማሳቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ያህል እያሰፉት እንደሆነ ያሰገነዝበናል፡፡
     ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ የመሠረታት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚል እኩይ ዓላማ ይዘው በተደራጀ ሥጋዊ ጥበብ እየተመሩ ብዙ የዋሃን ምዕመናንን እያሳሳቱ ከሚገኙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነውና ማኅበረ በኵር የተባለው ማህበር፤በመሠረት ስብሐት ለአብ አዘጋጅነት ከሚታተሙት መጽሔቶች መካከል "ጮራ" በተባለው መጽሔታቸው ላይ፤ከላይ የተመለከትነው የእነ አባ ጳውሎስ  የክህደት ትምህርት በተመሳሳይ መልኩ ተዘግቦ እናገኘዋለን፡፡(ይህ ማህበር ቅሰጣውን የጀመረው ገና በ1980ዎቹ አካባቢ ሲሆን፤ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን ቅ/ሲኖዶስ በ2004 አውግዞታል፡፡)
ጮራ ("ራ" ላልቶ ይነበብ) መጽሔት ቁጥር 11 ገጽ 20 በቀጥታ የተወሰደ፤
"የኬልቄዶን ጉባኤና ውሳኔው"
"በ451 ዓ.ም በኬልቄዶን ተደርጎ የነበረው ጉባኤ የተለያዩ ጉዳዮችና የአውጣኪን ትምህርት መርምሮ ነበር፡፡በጉባኤው ላይ የተነሱት ሃሳቦች ስለ ቃልና ሥጋ ተዋህዶ ሲሆን በሁለት ጎራ የተከፈሉ ነበር፡፡


አንደኛው ጎራ
የቃልና ሥጋ ተዋህዶ ያለመለያየትና ያለ መከፋፈል፤ያለመቀላቀልና ያለመጠፋፋት በተዐቅቦ አንድ ባሕርይና አንድ አካል ሲል፤
ሁለተኛው ጎራ
የቃልና ሥጋ ተዋህዶ ያለመለያየትና ያለ መከፋፈል፤ያለመቀላቀልና ያለመጠፋፋት በተዐቅቦ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል ይላል፡፡….."


ይሁንና ይህቺ አንዲት ቅድስት ቤ/ክ በ5ኛው  መቶ ዘመን በ451 ዓ.ም በጉባኤ ኬልቄዶን ላይ በደረሰባት ሃይማኖት ለበስ የሥልጣን ጦርነት ከምንጊዜውም የከፋ ዕድል ገጥሟት ከሁለት ተከፈለች፡፡ልጆችዋም አውጣኪያውያንና ንስጥሮሳውያን መባባል ጀመሩ፡፡ ‹‹ጠላት ይቀባል ጥላት›› እንደተባለው ሁሉ አንዱ ክፍል ሌላውን ጥላት መቀባት ጀመረ፡፡ ጠቡ ተካረረ፡፡ እርስ በርሳቸው መወጋገዝ እግዚአብሔርን እንደ ማገልገል ተቆጠረ ካለ በኋላ ጥቂት እልፍ ብሎ (ወሕቀ ተአቲቶ)‹‹እነሆ ያቺ አንዱዋ ሐዋርያዊት ቤ/ክ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መገኘትዋ ለስምዋ መጥፋት ለተቃራኒዎችዋም ምቾት መሆኑን የተገነዘቡ በኬልቄዶንና የቅድመ ኬልቄዶን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንት የክርስቲያኖችን አንድነት የሚፈጠርበትን፤የቤ/ክ ስም የሚታደስበትን መንገድ በመሻት በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማህበር የእምነትና ሥርዓት ክፍል አማካይነት ልዩ ውይይት ሲያደርጉ አሁን አራተኛ ጊዜያቸው ነው›› ይላሉ ጸሐፊው፡፡
ቤ/ክ ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት የሆነውን የክርክር መነሻና በአሁኑ ውይይት የተደረሰበትን ስምምነት የሚያመለክት የጋራ መግለጫ ይዘት ምን እንደሚመስል ሲያብራሩ እንዲህ ብለው ነበር፡፡‹‹ቤ/ክ ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት የሆናት የኬልቄዶን ጉባኤ 451 ዓ.ም ስለነበረ ያንን ጉባኤ አንስተው፤….ተነጋገሩ፤ተከራከሩ፤…በመጨረሻም አለያይቷቸው የኖረ የፓለቲካ ጉዳይ እንጂ የአንድ ባሕርይና የሁለት ባሕርይ ይትበሐል አለመሆኑን ተረዱ፡፡እኛ በአንድ አካል አንድ ባሕርይ በፍጹም በተዋሕዶ ስንል ፤እነሱም በአንድ አካል ሁለት ባሕርያት በተዋሕዶ በሚሉበት ጊዜ፤ሁለቱም ወገኖች ያለመከፈል፤ያለመነጣጠል፤ያለመጠፋፋት፤ያለመለወጥ፤የባሕርየ መለኮትን ፍጹም ተዋሕዶና መገናዘብ ስለሚያምኑ፤ልዩነቱ የቃላት አገላለጥ እንጂ የእምነት አለመሆኑን በጋራ መግለጫቸው በአንድ ቃል አጸደቁ››…ሁሉም የሚመኙትን አንድነት ለማምጣት ሲሉ ጉልበታቸውን፤አእምሮቸውን፤ጊዜያቸውን፤ገንዘባቸውን የለገሱትን ሁሉ ጌታ አብዝቶ ይባርካቸው በማለት እኛም በመተባበር እንመርቃለን፡፡"
ይላል ጮራ መጽሔታቸው፡፡
አጭር ማጠቃለያ
     ውድ አንባብያን ከላይ በጥቂቱ ለማሳየት እንደሞከርነው በሁለቱም ወገን ማለትም ቤ/ክ በሚመሩት በእነ አባ ጳውሎስና የፕሮቴስታንትን ዓላማ ይዘው ቤ/ክ መታደስ አለባት በሚሉት የምንፍቅና ድርጅቶች መካከል ምን ያህል የሃሳብ ትስስር እንዳላቸው እንድታስተውሉ አጠንክረን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ይኸውም፦
1/ ሊመሳሰል ይቅርና ፈጸሞ ሊቀራረብ እንኳን የማይችለውን "አንድ አካል አንድ ባህርይ" የሚለውንና "አንድ አካል ሁለት ባህርይ" የሚለውን ትልቁን የሃይማኖት ልዩነት ፤ሁለቱም ክፍሎች የቃላት የአገላላጥ ልዩነት እንጂ የሃይማኖት ልዩነት አይደለም በማለታቸው ፤
2/ እንደ ዘመኑ የስም ክርስቲያኖችና "የሃይማኖት አባቶች" በሥጋዊና ደማዊ አመለካከት ሳይሆን፤ እንደ ወንጌሉ ቃል  በእግዚአብሔር መንፈስ እየተመሩ፤እውነተኛይቱን የተዋህዶ ሃይማኖት እየመሰከሩ፤ መላ ሕይወታቸውን በሰማዕትነት ያሳለፉትን እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን የመሰሉ ቅዱሳን አባቶች መንበር ላይ ተቀምጠው፤ እነሱን መተቸታቸውና መንቀፋቸው፤ እጅግ በሚያሳዝንና በሚያሳፍር መልኩ ከተሰየሙበት ዓላማ ወጥተው ከለየላቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር ህብረት እንደመሰረቱ፤
3/ በጽኑ ዓለት ላይ የተመሰረተችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ ይችላሉ የሚል ሥጋት ባይኖረንም፤በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት የቤ/ክ መሪዎችና  ከቤ/ክ ውጪ ያሉት የመናፍቃን ድርጅቶች በመተባበር እየፈጸሙት ያለው ሃይማኖትንና ሥርዓትና የመበረዝና የመከለስ እኩይ ተግባራቸው ግን ብዙ የዋሃንን ምዕመናንንና የነገ ቤ/ክ ተረካቢ የሆነውን ወጣቱን ትውልድ የሚይዘውንና የሚጥለውን እያሳጡት መሆኑ እያየን ነው፡፡
      ስለሆነም ችግሩ የገባንና ጉዳዩ የሚመለከተን የተዋህዶ ልጆች፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና ሥርዓታችን በመሪዎችዋ ምክንያት ምን ያህል እየተዛባ እንደሆነ ስንመለከት ከምን ጊዜውም በላይ በጾምና በጸሎት ከመትጋት ጋር፤ በያለንበት አጥቢያ ቤ/ክ ነቅተን ካልጠበቅንና በአቅማችን በተሰጠን መክሊት አትርፈን ካልተገኘን፤የእኛ ቸልተኝነት ከአጥፊዎቹ ያልተናነሰ እንደሆነና ከህሊና፣ከታሪክና ከእግዚአብሔርም ወቀሳ እንደማናመልጥ ተገንዝበን ለመፍትሄው የምንነሳበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
የቅዱሳን አምላክ ለሁላችንም ማስተዋሉን ይስጠን፡፡
ይቆየን፡፡ለቀጣዩ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡



No comments:

Post a Comment