Sunday, March 6, 2016

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1 ክፍል ስድስት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

"ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" ሉቃስ 16፤13
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች!
እንደምን ሰነበታችሁ?
ን ዝም አልልም ” በሚለው ርዕስ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ክፍሎች በቅድስት ቤ/ክ ውስጥና በዙሪያዋ በማንኛውም ሁኔታ የሚከናወነው ንግድ የተወገዘ እንደሆነ የጌታችንን ወንጌል መሰረት አድርገን ብዙ ተማምረናል፡፡እንዲሁም በክፍል አራትና አምስት ደግሞ ይኸው አላስፈላጊ የቤተ ክርስቲያን የንግድ ሥራ እያስከተለ ያለውን ችግር በማስመልከት ‹‹ሐራ ዘተዋህዶ›› ከተባለው ድረ ገጽ ያገኘነውን ጽሁፍ ተመልክታችሁ ስለ ችግሩ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ "ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" በሚል ርዕስ እንማማራለን፡፡ 
መልካም ንባብ!
     ‹‹ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ወይም አንዱን ይጠላልና ኹለተኛውንም ይወዳል፤ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ኹለተኛውንም ይንቃል፤ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡›› ሉቃ.16፤12-13 በማለት ጌታችን አምላካችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግልጽና የማያሻማ በሆነ ቃል አስተምሮናል፡፡ እዚህ ላይ ገንዘብ ሲባል ለተለያየ የንግድ ልውውጥ የምንጠቀምበትን የገንዘብ ዓይነት ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ሀብትና ንብረትን ያጠቃልላል፡፡
     እንግዲህ እግዚአብሔር በልዩ አጠራሩ ለቅድስና ከጠራቸው ቅዱሳን በስተቀር፤ (ለምሳሌ እንደ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያሉ መናንያን) የሰው ልጅ በዚህ በዓለመ ሥጋ በሕይወት ለመኖር ምግብ፤ልብስና መጠለያ ያሰፈልጉታል፡፡እነዚህን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ደግሞ ማንኛውም ሰው ወጥቶ ወርዶ ላቡን አንጠፍጥፎ መስራት ይጠበቅበታል፡፡አስቀድሞም ልዑል እግዚአብሐር ለአባታችን ለአዳም ፦ "ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ " ዘፍ.3፥19 በማለት አዝዞታል፡፡ማንኛውም ሰው በእውነትና በጉልበቱ ሠርቶ ካገኘውን ገንዘብ /ሀብት/ ላይ አሥራቱን፤ በኩራቱንና ቀዳምያቱን ለቤተ እግዚአብሔር እየሰጠ፤ለራሱ ለመጠነኛ ኑሮው የሚያስፈልገውን በአግባቡ እየተጠቀመ፤ቀሪውን ደግሞ መሥራት ለማይችሉ ደካሞችና አካለ ስንኩላን እያካፈለ እንዲኖር ነው የታዘዘው፡፡በሀብቱ ብዛትና በጥበበኛነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ንጉሡ ሰሎሞንም እንኳን ‹‹ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፡፡››ብሎ ፈጣሪውን በመማጸኑ አብነት ሆኖናል፡፡ ምሳሌ 30፤8፡፡
     ይህንን ክፍለ ትምህርት በሚገባ ለመረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት "ለእግዚአብሔር መገዛት" የሚለውንና "ለገንዘብ መገዛት" የሚለውን ፍሬ ሃሳብ ከብዙው በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
/ ለእግዚአብሔር መገዛት ማለት ፦ አምላካችን እግዚአብሔር  ሰማይንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ መሆኑን በህገ ልቦና አምኖ /ተቀብሎ/፤እንዲሁም በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ህጉና ትእዛዙን ጠንቅቆ ማወቅና ይህንንም በተግባር መፈጸም ማለት ነው፡፡
v  ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፡፡መዝ.2፤11
v  ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ፡፡ዮሐ.14፤15 እንዳለ፡፡
ለእግዚአብሔር ብቻ በመገዛት የምናገኘው ጥቅም፦
  1. በምድር ላይ ያለ ጭንቀትና ያለ ስጋት በሰላምና በመንፈሳዊ ደስታ እንኖራለን፤
  2. የምድርን በረከት እንበላለን፤
  3. ነፍስንም ሥጋንም ከሚጎዳ ከማንኛውም ክፉ ነገር እንጠበቃለን፤
  4. ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ጋር ሕብረት ይኖረናል፤
  5. በመጨረሻም የዘላለም ሕይወት ባለቤት እንሆናለን፡፡
ለ/ ለገንዘብ መገዛት፦ ማለት በእውነተኛ መንገድ ሰርቶ በማገኘት ፋንታ ፤ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ብቻ ከሚዛናዊ ህሊና ወጥቶ የተለያዩ የሐሰት ሥራዎችን በመስራት፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ሁሉን ያደርግልኛል ብሎ በማመንና በመታመን ፋንታ በገንዘብ /በሀብት/ መታመን ወይም መመካት ማለት ነው፡፡ የገንዘብ ፍቅር ያደረበት ሰው የእግዚአብሔር ድርሻ የሆነውን አስራቱንና በኩራቱን አያወጣም፡፡በሐሰተኛም ሆነ በእውነተኛ መንገድ ያገኘውን ገንዘብ ሁሉ ለራሱ ከማግበስበስ በስተቀር ለተራበ ላብላ ለታረዘ ላልብስ… አይልም፡፡
ለገንዘብ መገዛት የሚያስከትለው መዘዝ
1/ የፈጠረውን አምላክ እስከ መሸጥ አድርሷል፤
‹‹በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሌዎች መልሶ፦ንጹህ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡እነርሱ ግን ፦እኛስ ምን አግዶን አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ፡፡›› ይላል፡፡ ማቴ.27፤3-5፡፡ዛሬም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ሀብትና ንብረት በመስረቅ /በመዝረፍ/ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ሁሉ ዉሉደ ይሁዳ /የይሁዳ የግብር ልጆች/ በመሆናቸው እጣ ፈንታቸው እንደ ይሁዳ መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡
2/ ከመንፈሳዊ ሕይወት ብሎም ከሃይማኖት ያወጣል
  • ‹‹የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና፤ተጠንቀቁ፤ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው፡፡››ሉቃ.12፤15
  • ‹‹አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፤ያላችሁ ይብቃችሁ፡፡››ዕብ.13፤5
  • ‹‹ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፤ከሃይማኖት ተሳስተው  በብዙ ሥራይ ራሳቸውን ወጉ››1ኛ ጢሞ.6፤10፡፡
3/ ቅስፈትን /ሞትን/ ያስከትላል፡፡
ሐናንያና ሚስቱ ሰጲራ መሬታቸውን ሸጠው ወደ ሐዋርያት ማህበር ሊገቡ ከወሰኑ በኋላ ከገንዘቡ ከፍለው አስቀርተው፤ እኩሌታውን ለሐዋርያት አቀረቡ፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ሌብነታቸውን በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ‹‹እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም››አለው፡፡‹‹ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ፤ሞትም፡፡ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሚስቱ መጣች፡፡‹‹ቅዱስ ጴጥሮስም የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለምን ተስማማችሁ? አላት፡፡ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም፡፡››የሐ.ሥራ 5፤1-11፡፡
     ከዚህም ሌላ ተገልጋዩ ምዕመን ሊረዳውና ሊከላከለው ያልቻለው ጉዳይ፤የተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ዶግማ፣ሥርዓትና ትውፊት የሚያፋልሱ መዝሙሮች፣መጻሕፍትና ስብከቶችም በተለያየ መንገድ እየተዘጋጁ በሽፋናቸው ላይ ‹‹በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እምነትና ሥርዓት መሰረት የተዘጋጀ›› የሚል ማስመሰያ ተለጥፎባቸው የሚሸጡት በዚሁ በተቀደሰው አደባባይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡እነዚህ ደግሞ ጥፋታቸው በሁለት በኩል ነው፡፡አንዱ በቤተ ክርስቲያን ስም ገንዘብን ያለ አገባብ መሰብሰባቸው ሲሆን ሌላው ደግሞም የዋሁ ምዕመን በቤተ ክርስቲያን  አውደ ምሕረት ላይ ስላገኘው ብቻ ስህተት አለው ብሎም ስለማይገምት በገዛ ገንዘቡ የክህደትና የኑፋቄ ሸቀጣ ሸቀጥ እየገዛ እንዲሰማና እንዲያነብ መደረጉ ነው፡፡በመሆኑም ምዕመኑ የቤተ ክርስቲያን  የሆኑትንና ያልሆኑትን መለየት ተስኖት እንደ ውሃ ላይ ኩበት ሲዋልል ይስተዋላል፡፡
የተከበራችሁ አንባብያን!
       ከዚህ በላይ ቃለ እግዚአብሔርን መሰረት በማድረግ፤ያለ አግባብ የሚሰበሰብ ገንዘብ በነፍስም በሥጋም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያሰከትል ከብዙው በጥቂቱ ተመልክተናል፡፡ጉዳዩ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ዓለሙንና በዓለም ያለውን ነገር ለጊዜው ትተን፤ ከተራው ምዕመን አልፎ ‹‹አትስረቅ፣አታመንዝር፣አትግደል፣በሐሰት አትመስክር….››እያሉ የሚያስተምሩ ‹‹መምህራን›› የሌብነቱ መሪና አስተባባሪ ሆነው መገኘታቸው፤የሚሰረቀው ገንዘብ ደግሞ የራሱ የእግዚአብሔር መሆኑ እጅግ ያሰፍራል፡፡‹‹እግዚአብሔር የተጣላው ሌባ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ይሰርቃል›› እንደተባለው ዘይቤያዊ አነጋገር ማለት ነው፡፡ በዚህ በአዲስ አበባ ብቻ በተደረገው ጥናት ስርቆት በህግ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ፤ተለያዩ ገዳማትና አድባራት የሚከናወነውን አስከፊ የሆነ የሌብነትና የማጭበርበር ሥራዎች ቀደም ባሉት ዘገባዎች ተመልክተናል፡፡በሙዳየ ምጽዋት ከሚሰበሰበው ፣ ከህንጻዎች፣ ከሱቆችና ከቦታዎች ኪራይ ከሚገኘው ገቢ፣እንዲሁም በተለያዩ የልማት ሥራዎች ምክንያት ከሚወጣው ወጪ ላይ የተለያየ የአሰራረቅ ስልት እየተጠቀሙ የእግዚአብሔርን (የቤተ ክርስቲያንን) ንብረትና ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉት፤እራሳቸው ቤተ እግዚአብሔርን ደፍረው ሌላውን የሚያደፋፍሩ  ‹‹አገልጋይ›› ተብዬዎች መሆናቸው ደግሞ እጅግ እጅግ ያሳዝናል፡፡  
       እንግዲህ ከላይ የተመለከትነውን ዓይነት አጸያፊ ኃጢአት የሚሰሩ ሁሉ የበደሉትን ክሰው፤ የዘረፉትን መልሰው፤ ንስሃ ካልገቡ በስተቀር በፍርድ ቀን በስርቆት የሰበሰቡት ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፡፡
ለዚህም ሐያርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ ብሎ አትሞታል፡፡
     "ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው፡፡አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች አገር ወጥተው ይሄዳሉ፡፡እሊህም ሥራይን የሚያደርጉ፣ሴሰኞች፣ነፍሰ ገዳዮች፣ጣዖትን የሚያመልኩና የሐሰትን ሥራ የሚወዱት ሁሉ ናቸው፡፡"ራእይ 22፥14-15፡፡

እኛም ከልዩ ልዩ የኃጢአት ሥራ ተጠብቀን የጽድቅ ሥራ በመስራት ወደ ሕይወት ዛፍ የሚያደርሰውን መንገድ እንድንከተል፤
የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፤
የእመቤታችን የእናት አማላጅነት፤
የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና በረከት፤
ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡

ይቆየን፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ርዕስ እንመለሳለን፡፡

No comments:

Post a Comment