Sunday, January 13, 2013

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1 ክፍል አንድ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
“የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ፤አንባቢው ያስተውል…”ማቴ.24፥15

    የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ልጆች፦ እንደምን ሰንብታችኋል? በቸርነቱና በቅዱሳኑ ቃል ኪዳን እየጠበቀ እዚህ ያደረሰን ፈጣያችን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ  እስከ ዘለዓለም ድረስ የተመሰገነ ይሁን፡፡ “ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ ” እና “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ” በሚት ርዕሶች በቤ/ክ ስም የተዘጋጁ ነገር ግን የቤ/ክንን እምነትና ሥርዓት እንዲሁም ትውፊቷን ሳይቀር የሚያፋሱትን መጻሕፍት በመጥቀስ የተዘጋጀውን ሰፊ ዘገባ እንደተመለከትን ሁሉ በዚህም ርዕስ ደግሞ በቅድስት ቤ/ክ ሊደረጉ የማይገባቸው ነገር ግን በስፋት እየተፈጸሙ ያሉትን ­­­­­­­­­­­ጥፋቶች እንመለከታለን፡፡የዚህም ጽሑፍ አዘጋጅ ዋና ዓላማ ሁላችን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ልጆች ወደ ማስተዋል ተመልሰን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከምንሰራው ስህተት እንድንመለስ ለማሳሰብ ነው፡፡   
   ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማይንና ምድርን ለማሳለፍ የሚመጣበት ጊዜ ሲቃረብ የሚታዩትን ምልክቶች ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝርዝር የነገራቸውን በወንጌል ስናነብ (በማቴ.24፥1-ፍጻሜ፤ ማር.13፥1-ፍጻሜ፤ ሉቃ.21፥5-36 ) እኛ ያለንበት ዘመን ትንቢቶቹ በብዛት እየተፈጸሙ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ከነዚህም የዓለም ፍጻሜ የመቃረቡ ምልክቶች አንዱ “የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ፤አንባቢው ያስተውል…ማቴ.24፥15 በማለት ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ነው፡፡ጌታችንም ይህንን ትምህርት ያስተማረው አስቀድሞ ነቢዩ ዳንኤል  የተናገረውን  በመጥቀስ ሲሆን ትንቢቱም እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ ፤መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ የጥፋትንም ርኩሰት ያቆማሉ፡፡” ዳን.11፥31 ፡፡ ይህ የርኩሰት ሥራ በኢአማንያኑ ብቻ የሚፈጸም ቢሆን ባላሰደነቀም ነበር፡፡የበለጠ የሚያሳዝነው ግን ቤ/ክ እናከብራለን የምንለው ሰዎች የእግዚአብሔርን ማደሪያ ቅድስት ቤ/ክንን በተለያየ ነገር እያረከስናት መሆኑ ነው፡፡ከነዚህም ጥፋቶች ውስጥ በቅድሚያ አንዱን ብቻ እንመለከታለን፡፡