Sunday, January 13, 2013

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1 ክፍል አንድ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
“የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ፤አንባቢው ያስተውል…”ማቴ.24፥15

    የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ልጆች፦ እንደምን ሰንብታችኋል? በቸርነቱና በቅዱሳኑ ቃል ኪዳን እየጠበቀ እዚህ ያደረሰን ፈጣያችን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ  እስከ ዘለዓለም ድረስ የተመሰገነ ይሁን፡፡ “ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ ” እና “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ” በሚት ርዕሶች በቤ/ክ ስም የተዘጋጁ ነገር ግን የቤ/ክንን እምነትና ሥርዓት እንዲሁም ትውፊቷን ሳይቀር የሚያፋሱትን መጻሕፍት በመጥቀስ የተዘጋጀውን ሰፊ ዘገባ እንደተመለከትን ሁሉ በዚህም ርዕስ ደግሞ በቅድስት ቤ/ክ ሊደረጉ የማይገባቸው ነገር ግን በስፋት እየተፈጸሙ ያሉትን ­­­­­­­­­­­ጥፋቶች እንመለከታለን፡፡የዚህም ጽሑፍ አዘጋጅ ዋና ዓላማ ሁላችን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ልጆች ወደ ማስተዋል ተመልሰን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከምንሰራው ስህተት እንድንመለስ ለማሳሰብ ነው፡፡   
   ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማይንና ምድርን ለማሳለፍ የሚመጣበት ጊዜ ሲቃረብ የሚታዩትን ምልክቶች ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝርዝር የነገራቸውን በወንጌል ስናነብ (በማቴ.24፥1-ፍጻሜ፤ ማር.13፥1-ፍጻሜ፤ ሉቃ.21፥5-36 ) እኛ ያለንበት ዘመን ትንቢቶቹ በብዛት እየተፈጸሙ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ከነዚህም የዓለም ፍጻሜ የመቃረቡ ምልክቶች አንዱ “የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ፤አንባቢው ያስተውል…ማቴ.24፥15 በማለት ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ነው፡፡ጌታችንም ይህንን ትምህርት ያስተማረው አስቀድሞ ነቢዩ ዳንኤል  የተናገረውን  በመጥቀስ ሲሆን ትንቢቱም እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ ፤መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ የጥፋትንም ርኩሰት ያቆማሉ፡፡” ዳን.11፥31 ፡፡ ይህ የርኩሰት ሥራ በኢአማንያኑ ብቻ የሚፈጸም ቢሆን ባላሰደነቀም ነበር፡፡የበለጠ የሚያሳዝነው ግን ቤ/ክ እናከብራለን የምንለው ሰዎች የእግዚአብሔርን ማደሪያ ቅድስት ቤ/ክንን በተለያየ ነገር እያረከስናት መሆኑ ነው፡፡ከነዚህም ጥፋቶች ውስጥ በቅድሚያ አንዱን ብቻ እንመለከታለን፡፡

ሀ/  “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት”  ዮሐ.2፥16
    ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን አስቀድሞም በነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕ.56፥7 “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና…” ተብሎ  የተጻፈውን በመጥቀስ ያስተማረውን ትምህርት በማቴ.21፥13 “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ”በማር.11፥17 “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ” ፤በሉቃ.19፥45 “ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ” በዮሐ.2፥16 “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት”  በሚል ኃይለ ቃል ተገልጾ እናነባለን፡፡እነዚህም በተለያየ አገላለጽ የቀረቡት ኃይለ ቃላት አጠቃላይ መልእክት በቤ/ክ ከጸሎት በስተቀር ምንም ዓይነት ሥጋዊ ሥራ እንዳይሰራባት የሚከለክል ነው፡፡ ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን በዚህ ምድር ሲመላለስ በነበረበት የሥጋዌ ዘመኑ ዕለት ዕለት ወደ ቤተ መቅደስ እየሄደ ያስተምር እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ጌታችን የቤዛነት ሥራውን በመስቀል የሚፈጽምበት ጊዜ ሲቃረብ በበዓለ ሆሳዕና በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ጡት ከሚጠቡት ህፃናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን አባቶችና እናቶች ድረስ የነበረው ሕዝብ ሁሉ “ ሆሳዕና በአርያም ” እያሉ እያመሰገኑትና እየሰገዱለት ቤተ መቅደስ ደረሱ፡፡በዚያን ጊዜ ግን የአይሁድ ካህናት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተለያዩ እንስሳትንና አእዋፍን ሲሸጡና ሲገዙ እንደነበር ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ በወንጌሉ የጻፈልንን እንመልከት፡፡ “ በመቅደስም በሬዎችንና በበጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፤የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፤ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ሻጪዎችንም ‘ይህን ከዚህ ውሰዱ ፤የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉትአላቸው፡፡” ዮሐ.2፥14-16 ፡፡ እንግዲህ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ከጸሎት በስተቀር ምንም ዓይነት ሥጋዊ ሥራ ሊሰራበት እንደማይገባ በቃልም በተግባርም አስተምሮናል፡፡
   የተከበራችሁ ምዕመናን ፦ይህ ከላይ አጠር አድርገን የተመለከትናቸው ኃይለ ቃላት ለበሉይ ኪዳኗ ቤተ መቅደስ ማለትም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ የነበሩት እንስሳት ይሰዉባት ለነበረችው ቤተ መቅደስ እንዲህ ዓይነት ክብር የሚያስፈልጋት ከሆነ የዘላለም ሕይወትን የምንወርስበት የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ  ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለሚፈተትባት ለአዲስ ኪዳኗ ቤተ መቅደስ (ቤተ ክርስቲያን) በምን ያህል የበለጠ ክብር ልንጠብቃት ይገባን ይሆን ? መልሱን የቤ/ክ ጉዳይ ሚመለከተው ሁሉ ሊያስብበት ይገባል፡፡
   እንግዲህ ስለ ቤ/ክ የወንጌሉ ቃል የሚያዝዘን እንዲህ ከሆነ አሁን እኛስ በዚህ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች ምን እያደረግን ነው? የጌታችንን ቃል አክብረን ቤ/ክንን ለጸሎት ብቻ እየተገለገልንባት ነው ወይስ እንደ አይሁድ ካህናትና ጻፎች ከእነርሱም በባሰ ሁኔታ መሸጫና መለወጫ አድርገናታል? በሚለው ሃሳብ ዙሪያ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡  ይቆየን፡፡

No comments:

Post a Comment