ካለፈው የቀጠለ...
“ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ ይልቁንም ግለጡት እንጂ” ኤፌ. ፭፥፲፩
የተከበራችሁ አንባብያን“ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ” እና "ማንም አንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ" በሚሉት ርዕሶች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መሪዎች የቤ/ክ እምነትና ሥርዓቷን ምን እያዛቡ እንደሆነና እንዲሁም እኛ ምዕመናን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጥፋታቸው ተባባሪ በመሆን ቤ/ክንን ከጸጋ እግዚአብሔር እንድትራቆት ማድረጋችንን በተመለከተ ሰፊ የሆነ ዘገባ ማቅረቤ የሚታወስ ነው:: ያለንበት ችግር ይህንን ከመሰለ ከእኛ ምን ይጠበቃል? በሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ዙሪያ እንደምንቀጥል ተስፋ በማድረግ በይደር አቆይተነው ነበር:: ይህንንም ችግር እየተመለከተ የሰላም እንቅልፍ የሚተኛ የተዋህዶ ልጅ ሊኖር ስለማይገባ ምናልባት ያንቀላፋንም ካለን ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ “አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስም ያበራልሃል” ኤፌ. 5፥14 ያለውን ቃል ማስታወስ አለብን:: በመሆኑም መመሪያችን ቃለ እግዚአብሔር እንደመሆኑ መጠን ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል ወደሚለው የማጠቃለያ ሃሳብ ከመሄዳችን በፊት ጸሎትን በተመለከተ ጥቂት ማሳሰብ እፈልጋለሁ::
ስለ ጸሎት አጭር መልእክት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውና ቅ/ማቴዎስም በወንጌሉ ምዕ.7፥7 እንደጻፈው “ ለምኑ ይሰጣችሁማል፣ፈልጉ ታገኙማላችሁ...” በማለት በገባልን ቃል መሰረት ሐዋርያው ቅ/ያዕቆብም በመልእክቱ በምዕ. 5፥16 “ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ስለሌላው ይጸልይ...”፤ እንዲሁም ሐዋርያው ቅ/ዮሐንስም በ1ኛ ዮሐ.5፥14 “ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል”:: በማለት የጸሎትን አስፈላጊነትና ጠቃሚነት አስተምረውናል:: ከላይ የተገለጹትንና ሌሎችንም ኃይለ ቃሎች ስንመለከት የምንረዳው አንዱ ስለሌላው መጸለይ እንዳለበት ፤ ለዚህም የሃይማኖት አንድነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ፤ እንዲሁም ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን መጠየቅ አለብን:: በአንጻራዊ መልኩ ለማይገባቸው ሰዎች ማለትም ለከሃድያንና ለመናፍቃን መጸለይ እንደማይገባ የሚያስተምሩንን ኃይለ ቃሎች ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን::
ሀ/ በመጽሐፈ ሳሙኤል ከምናገኘው ሰፊ ታሪክ ውስጥ በ1ኛ ሳሙ. ምዕ. 13፥8-12 ስንመለከት እንደ ኦሪቱ ህግ በቤተ መቅደስ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ የነቢዩ ሳሙኤል ድርሻ ሆኖ ሳለ ንጉሡን ሳኦልን ግን ሳሙኤል ቢዘገይም እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ ሲገባው ወደ ጦርነት የሚሄድበት ጊዜ ስለደረሰበት እራሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አሳረገ:: ይህንን ሲጨርስ ሳሙኤል መጣ እንዲህም አለው “ አላበጀህም አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም ፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶት ነበር:: አሁንም መንግሥትህ አይጸናም...” በማለት ገስጾታል:: በዚህ ሁኔታ ሳኦል ወደ ጦርነት ሲሄድ አማሌቃውያንንና ያላቸውንም ሁሉ አጥፋ የሚል ሌላ ትእዛዝ ተሰጠው:: እሱ ግን ከእንስሳቱ የተናቁትንና ምናምንቴዎቹን አጥፍቶ የሰቡትንና የወፈሩትን እንስሳት ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ :: ነቢዩ ሳሙኤልም ያደረገውን ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ቢጠይቀው ሳኦል እንዲህ ብሎ መለሰለት:: ምዕ.15፥21-35 “ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልሌላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው :: ሳሙኤልም በውኑ እግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን ? እነሆ መታዘዝ ከመሥዋዕት ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል:: ... እግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ ::” ይላል:: በቁጥር 35 ላይ “ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ::” ይላል:: ይህ ብቻም አይደለም በምዕ. 16፥1 “እግዚአብሔርም ሳሙኤልን በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው ? ” በማለት የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት ይልቅ በራሱ የተሳሳተ መንገድ መሄድን በመምረጡ የእግዚአብሔር መንፈስ ለተለየው ለሳኦል ጸሎት እንኳን እንዳይጸልይለት እንዳያለቅስለትም ሳሙኤልን ከልክሎታል:: ከዚህ ታሪክ የምንረዳው እግዚአብሔር ደስ ብሎት የሚቀበለው ጸሎትም ሆነ መሥዋዕት ህጉንና ሥርዓቱን ጠብቀን በትህትና ስናቀርበው ብቻ ነው::
ለ/ እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ “እንግዲህ አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ አትማልድላቸውም ” ኤር. 7፥16 በማለት የተናገረው በዚያን ጊዜ የእስራኤላውያን ኃጢአት ከመጠን ያለፈ ስለነበረ ነው ::
ሐ/ ወደ ኋላ መለስ ብለን የሰውን ልጅ ይልቁንም የእስራኤላውያንን ታሪክ ስንመለከት በዘፍ. 1፥27 “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ ” ይላል:: ይህም ማለት ሰውን ከሌሎቹ ፍጥረታት ለይቶ አክብሮ እንደፈጠረው ያሳየናል:: በዘፍ.6፥6 “እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ ” ይላል:: ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሥራው ፍጹም በመሆኑ እንደ ሰው ጸጸት ያለበት ባይሆንም ተጸጸተ የተባለው የሰዎች ልጆች ኃጢአት ምን ያህል የከበደ እንደነበረ ለመግለጽ መሆኑ እሙን ነው:: እንዲሁም ከዚህ ጋር አያይዘን ዘፀ. 25፥8 “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ ” ያለ እግዚአብሔር በኢሳ. 66፥1 ላይ ደግሞ “ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት የምትሰሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው ?”ብሏል:: የመሥዋዕት አቀራረብንም በተመለከተ ዘፀ. 29፥1 “እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግባቸው ነገር ይህ ነው፤ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ:: ቂጣ እንጀራ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ ” በማለት እግዚአብሔር ለሙሴ ካዘዘበት ጊዜ ጀምሮ የብሉይ ኪዳኑ ካህናት እንደ ታዘዙት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: በትንቢተ ሚልክያስ 1፥ 6-10 ስንመለከት ደግሞ “ እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፣ልጅ አባቱን ፣ባሪያም ጌታውን ያከብራል፣እኔስ አባት ከሆንኩ ክብሬ ወዴት አለ ? ጌታስ ከሆንኩ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር.....ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን ? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን ? .....በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም ፣ ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፤ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር:: ” እንዲሁም በኢሳ. 1፥10-20 ስንመለከት “ የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል ?፤ምናምንቴውን ቁርባን ጨምራችሁ አታምጡ ፤ዕጣናችሁም በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም ...” በማለት እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ አድሮ ሲናገርና ይህንንም ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል ...፤ ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ..፤.ክፉ ማድረግንም ተዉ...” ብሏል ::እንግዲህ እነዚህንና ሌሎችንም ክፍለ ትምህርቶች በተናጠል ስንመለከታቸው እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሊመስለን ይችላል :: ነገር ግን አስቀድሞ እግዚአብሔር መቅደስ ሥሩልኝ ፤ መሥዋዕትን ቁርባንን እንዲሁም ዕጣንን አቅርቡልኝ ያለው እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዙን አክብረው በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ፤ እግዚአብሔርን ሕግ ጥሰው በኃጢአት በረከሰ ሕይወታቸው ያቀረቡትን ያልተገባ ጸሎትና መሥዋዕት ግን አልቀበልም ብሏል::እንዲሁም በኦሪት ዘሌዋ. 26፥2“መቅደሴን ፍሩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ” እንዳለ ጸሎታችንም ሆነ መሥዋዕታችን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነን እስካላቀረብነው ድረስ በሕይወት ፋንታ ሞትን በበረከት ፋንታ መርገምን ከምናተርፍ በስተቀር በዘፈቀደ በምናቀርበው አገልግሎት ብቻ የእግዚአብሔርን ጸጋ ማግኘት አይቻልም::ከዚህ የምንረዳው እግዚአብሔር ከአማኞቹ የሚፈልግው የጸሎትና የመሥዋዕትን ብዛት ሳይሆን አስቀድሞ ሕጉንና ትእዛዙን እንድንጠብቅለት ነው:: ቅዱስ ዳዊትም በመዝ.50፥17 “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው” ያለው ለዚህ ነው::
እንግዲህ ለአማናዊቷ ቤ/ክ ምሳሌዋ ለሆነችው ለብሉይ ኪዳኗ ቤተ መቅደስና የዓለምን ኃጢአት ያስወገደው የእግዚአብሔር በግ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ለነበረው የብሉይ ኪዳን የእንስሳት መሥዋዕትና የእህል ቁርባን እንዲሁም ይህንን አገልግሎት ይፈጽሙ የነበሩት የብሉይ ኪዳን ካህናት እንዲህ ንጽህናና ቅድስና የሚያስፈልጋቸው ከሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም የተመሰረተችውን ቤተ ክርስቲያንማ ምን ያህል የበለጠ ልናከብራት እንዲሁም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደራሴ የሆኑ የአዲስ ኪዳን ካህናት በምን ያህል ንጽህናና ቅድስና ማገልገል እንደሚገባቸው በቃላት ለመግለጽ ስለሚያስቸግረኝ ቅ/ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች የጻፈውን መልእክት በይበልጥም ምዕራፍ ዘጠኝን በሙሉ እንድታነቡ እጋብዛለሁ ::
መ/ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርብ ሊሰቀል ሐሙስ ማታ ስለሁላችን ወደ አባቱ ባቀረበው የጌቴሴማኔ ጸሎቱ በዮሐ. 17፥ 9 “ እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፣ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ-- ” በማለት ለጊዜው አብረውት ለነበሩት ሐዋርያት ቀጥሎ ደግሞ እስከ ዓለም ፍጻሜ በስሙ ለሚያምኑት ደግሞ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሳ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም ” ዮሐ. 17፥20 በማለት በጸለየው ጸሎቱ የቤዛነቱንና የአርአያነት ሥራውን ፈጽሞ እኛም እሱን እንድንከተል አዝዞናል::
እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በእኛ ዘመን ታዲያ ክመናፍቅነታቸውና የክህደታቸው የተነሳ በአብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሥም ከመታሰራቸው ( ከመገዘታቸው) አልፎ የሚጠይቅ ቢኖር በዓለማዊው ህግ ሳይቀር ሊያስጠይቃቸው የሚችል ወንጀል በአደባባይ እየፈጸሙ ለስም ብቻ ፓትርያርክ ፣ጳጳስ ፣ኤጲስ ቆጶስ ስለተባሉ ብቻ በቤተ ክርስቲያን በጸሎትና ይልቁንም በቅዳሴ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ እየተባሉ መወደሳቸው እነሱም በጸሎቱ ስለማያምኑበት የማይጠቀሙበት ከመሆኑ ሌላ ካህናትና ዲያቆናትም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በሚፈተትበት በታላቁ የቅዳሴ ጸሎት ላይ የማይገባቸውን ሰዎች ስም በመጥራታቸው ከእነሱ አልፎ እኛም የእኩይ ሥራቸው ተባባሪዎች ሆነናል:: የበደልነውን ክሰን የቀማነውን መልሰን በንስሃ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን ሥርየተ ኃጢአት የምናገኝባት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ በአሁኑ ጊዜ የወንበዴዎች ዋሻ በመሆኗ የተቀደሰውን አገልግሎት ልናገኝባት አለመቻላችን እጅግ ያሳዝናል::
ማጠቃለያ
ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ “ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላትያ 3፥1 ) ብሎ የገላትያን ክርስቲያኖችን እንደጠየቃቸው እኛንም እየጠየቀን ስለሆነ አሁን ምን እናድርግ? ወደሚለው ጥያቄ እንመለስ::
ሀ/ ለቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት መበላሸት ከምዕመናን ጀምሮ እስከ ከታላላቆቹ አባቶቻችን ጳጳሳት ድረስ እንደየ ጥፋታችን ዓይነት ሁላችንም ተጠያቂዎች እንደሆንን ቀደም ባሉት ጽሁፎች ተመልከተናል:: ቤ/ክንን በከበረ ደሙ የመሰረታት ልዑል እግዚአብሔር ይህንን ሁሉ ጥፋታችንን እያየ የታገሰንኮ ንስሃ የምንገባበት ጊዜ መስጠቱ ነው::ታላቁ አባት ሲራክም “ እግዚአብሔር ቸርነቱ ብዙ ነው እያልክ በኃጢአት ላይ ኃጢአት አትስራ ” :: (ሲራክ ምዕ.5፥5) በማለት አስጠንቅቆናል:: ስለሆነም በየግላችን ለሰራነው ለቀደመው ኃጢአታችን ንስሃ መግባትና ለወደፊቱም ከኃጢአት ተጠብቀን ከዚህ ዓለም በሞት እስክንጠራ ድረስ የንስሃ ፍሬ የሆኑትን መልካም ሥራዎች እየሰራን በጥንቃቄ መኖር ሲሆን በአደባባይ የሰራነውን ጥፋት ግን በኛ ምክንያት የተሳሳቱትም ሁሉ መታረም ስላለባቸው ጥፋታችንን በግልጽ ማመንና መመለስ ፤ ሥርዓተ ቤ/ክ የሚያዝዘንንም ቀኖና ሁሉ መፈጸም ይገባናል::
ለ/ አባታችን ነቢዩ ዳዊት በመዝ. 52፥3 “ ሁሉ በደሉ አብረውም ረከሱ” እንዳለው ከደቂቅ እስከ ልሂቅ ፤ በግልም ሆነ በጋራ ፤በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያጠፋነውን የቤ/ክ እምነትና ሥርዓት ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን ስትመራበት ወደነበረው ህግና ሥርዓት ለመመለስ ትልቁ ሃላፊነት የቅ/ሲኖዶስ ቢሆንም አንዳችን በአንዳችን ማመካኘቱን ትተን የራሳችንን በኃጢአት የጎሰቆለ ሕይወት በንስሃ ከማደስ ጀምሮ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀት አለብን::
ሐ/ በኢሳ.6፥1 ላይ እግዚአብሔር ለነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረውን ቃል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ንጉሱ ዖዝያን በሞተበት ወራት ጌታ በመንበረ ፀባኦት እንዳለ ሆኖ ለኢሳይያስ ታየው:: ያ ታፍረው ታከብረው የነበረ ንጉሥ ሞተ አለፈ እኔ ግን ኅልፈት ውላጤ የለብኝም:: አለው::” ብሎ ተርጉሞታል:: ይህም የፍርሃት መንፈስ ምንም እንኳን በኋላ ቢመለስለትም ነቢዩ ኢሳይያስን ሀብተ ትንቢቱን አስነጥቆት ነበር :: ለእኛም ቤተ ክርስቲያን ችግር ዋነኛው ምክንያት በህመም በሞት የሚለወጠውን ሰው ያለአግባብ መፍራትና የምንቸገረኝነት መንፈስ ስለሆነ ይህንን ትተን የማያልፈውን እግዚአብሔርን ብቻ ማክበር ትእዝዙንም መጠበቅ አለብን:: አባቶቻችን ሐዋርያትም በሐዋ.ሥራ. 5፥29 “ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል::” እንዳሉት ::
መ/ በአሁኑ ጊዜ የምናየውን ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ሊስተካከል የሚችለው የእያንዳንዳችን ድርሻ እንዳለ ሆኖ የእግዚአብሔር ኃይል ሲጨመርበት ስለሆነ ከቂምና ከበቀል ርቀን ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዑል እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት መማጸን አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው::
እንግዲህ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና የድርሻዬን ለመወጣት ከዚህም ከዚያም የቃረምኳቸውን የተወሰኑ የቤ/ክ ችግሮችና መፍትሄ ይሆናሉ ያልኳቸውን ሃሳቦች አቅርቤያለሁ: : ቤ/ክ የሰው ድሃ አይደለችምና ችግሩንም ሆነ መፍትሄውን ከዚህ የተሻለ የሚያውቁ እንዳሉ አምናለሁ :: ስለሆነም አስተያየትም ለመቀበል ዝግጁ መሆኔን እየገለጽኩ ለዛሬው እሰናብታለሁ :: እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን::
ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን በምህረትና በሃይማኖት እንድትከፈት ያድርግልን ::
አሜን::
AMEN!
ReplyDelete