Thursday, September 27, 2012

"ማንም አንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ" ማቴ ፳፬ ቁ. ፬ ክፍል ፭

ካለፈው  የቀጠለ...
     
     የተከበራችሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ቀደም ሲል“ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ” ቀጥሎም “ ማንም አንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ”  በሚሉት ርዕሶች ያስነበብናችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓቷ ምን ያህል እየተበረዘና እየተከለሰ እንደሆነ ሕዝቡም አሕዛቡም በገሃድ የሚያየውንና የሚሰማውን ችግር ሳይጨምር ቤተክርስቲያንን በሚመሩት በፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ በታላላቅ ሊቃውንትና በቤተ ክህነት ልዩ ልዩ የሃላፊነት ሥራ ላይ በሚገኙ አካላት የተዘጋጁትን ዜና ቤ/ክ ጋዜጣን ፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት፣ ስርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት የሚለውን መጽሐፍ  እንዲሁም የአጣሪ ኮሚሽኑን ሪፖርትና ሌሎችንም ተጨባጭ ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ  የተዘጋጁ ናቸው::
      ከቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን የተረከብናትን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ሳትበረዝና ሳትከለስ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ በዚህ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች መንፈሳዊና ታሪካዊ ግዴታችን ነው::  በመሆኑም ይህንን ግዴታችንን በአግባቡ ለመወጣት የምንችለው ያለብንን ችግር በትክክል ስንረዳው ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ዋና አላማም ችግሩን አውቀን የቤ/ክ ሥርዓት በሚፈቅድልን መሰረት ለመፍትሄው እንድንነሳሳ ለማድረግ ነው:: እንደኔ ሃሳብ እነ እገሌ ይህንንና ይህንን አደረጉ እያልኩ የማንንም ስም ባላነሳ እወድ ነበር ሆኖም ችግሩን ከችግሩ ባለቤት ለይቶ መናገር ስለማይቻል የችግሩን ፈጣሪዎች በዝርዝር ለማቅረብ ተገድጃለሁ::
      እንግዲህ  ከቀረበው ሰፊ ዘገባ ውስጥ አጽንኦት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ነጥቦችና ከእኛስ ምን  ይጠበቃል? በሚለው ሃሳብ ጽሁፋችንን እናጠቃልላለን::
ሀ / ለፓትርያርኩ ለአባ ጳውሎስ በማይገባ የተጠቀሱ ጥቅሶች
 1/  በኢሳ. 61፥1 “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ለድሆች የምሥራችን እስብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና ልባቸው ያተሰበረውን  እጠግን ዘንድ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል::" ተብሎ የተነገረው ትንቢት ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ እሱም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ወንጌልን ማስተማር ሲጀምር በሉቃ. 4፥19 ላይ "የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው ፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ለታሰሩትም መፈታትን ለእውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈለትን ስፍራ አገኘ:: መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ ፣ በምኩራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር:: እርሱ ዛሬ ይህ መጽሀፍ በጆሮአችሁ ተፈፀመ ይላቸው ጀመር::” በማለት አረጋግጦልናል:: እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የቤ/ክ አገልጋዮች ለፓትርያርኩ ለአባ ጳውሎስ ይህ ትንቢት የተነገረው ለእርሶ ነው በማለት በዜና ቤ/ክ ጋዜጣ ቁ. 163 "'ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ሆይ' ከላይ በርዕሱ እንደተጠቀሰው  'የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ለታሰሩትም መፈታትን፤ ለእውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ' በማለት ነብየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አስቀምጦታል፡፡ ይህ አባባል ቅዱስነትዎን ያለማመንታት የሚመለከት ነው፡፡” ሲሉ ገልጸውታል:: እንኳን እያጠፉ መልካምም ቢሰሩ ለእሳቸው የሚስማማ ጥቅስ የሌለ ይመስል እንዲህ ከፈጣሪያቸው ጋር አስተካክለው ሲጠቅሱላቸው ትንሽም አለማፈራቸው አቤት አቤት አቤት እንዴት ያሳዝናል!!!:: ደግሞም ከመላው የአ/አ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ከሰበካ ጉባዔ አባላት፣ከሰንበት ት/ቤት አባላትና ከየአጥቢያ ቤ/ክ ሠራተኞች  መካከል አንድም እንኳን ይህ እንዴት ይባላል የሚል መጥፋቱ ምን ያህል አዚም ቢደረግባቸው ይሆን?
2/  በዚሁ ጋዜጣ በመጽሐፈ መክብብ  9፥7 (ጥቅሱን እናንተ አንብቡት) ተጠቅሶ ለቃሉም የማይገባ ትርጉም ተሰጥቶ ፓትርያርኩ አባ ጳውሎስ በጾምና በጸሎት ፈንታ ያለሃሳብ እንጀራችውንና የወይን ጠጃቸውን በደስታ እንዲበሉና እንዲጠጡ የማበረታቻ ገጸ በረከት አቅርበውላቸዋል:: ነጩ ልብሳቸውም ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮቱ ሲገለጥ ከታየው ከብርሃነ መለኮቱ ጋር ( ማቴ. 17፥1 ) በማነጻጸር  እንዲህ ብለውላቸዋል::  "እግዚአብሔር ስራህን ተቀብሎታል ሂድ እንጀራህን በደስታ ብላ የወይን ጠጅህንም ጠጣ ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ መክብብ 9፡7"  "... ይህም የዘወትር መንፈሳዊ ስራዎ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ልብስህ ነጭ ይሁን በማለት ጥልቅ በሆነ እውቀትዎ እና በመለኮተ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ የሚመሰል ልብስዎ በደብረ ታቦር የታየው ጉልህ ሚስጢር ነው::” እሳቸውም ከዚህ አያይዘው በመጋቢት 7 ቀን 2003_ዓ.ም ከሬድዮ ፋና ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  ነጩ ልብሳቸው የጌታችን የብርሃነ መለኮቱ ምሳሌ መሆኑን በመጥቀስ እራሳቸውን ከጌታችን ጋር ካመሳሰሉ በኋላ ጥቁር ልብስ ደግሞ የባርነት ምሳሌ መሆኑን ከጥያቄው ጋር የማይገናኝ የቱርክን አገር ታሪክ ጠቅሰው ተናግረዋል:: በእኛ ቤ/ክ ሥርዓት ግን መነኮሳት ጥቁር የሚለብሱት ዓለምን የመናቃቸው ምልክት እንጂ ለማንም ባርያ ሆነው አይደለም::
ለ/ ፓትርያርኩ አባ ጳውሎስ ቤ/ክንን የመናፍቃን ድርጅቶች ጥገኛ ጋር  ሁኔታ
       በዜና ቤ/ክ ጋዜጣ ቁ. 165 “የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በዓለም ያለች እንደመሆኗ መጠን ከራስዋ ውጪ ስለሌላው ማወቅም ማየትም መስማትም የለብኝም በሚል የብቸኝነትና የምናኔ ጠባይ ደጅዋን ዘግታ የተቀመጠች ቤ/ክ አይደለችም::” በማለት እስከዛሬ ለመናፍቃን አጥሯን አጥብቃ በሯን ዘግታ ማለትም  ሃይማኖቷን ከነ ሥርዓቷና ከነትውፊቷ  አጽንታ የኖረችውን ቤ/ክን ፓትርያርኩ አባ ጳውሎስ የተባበሩት የዓለም መናፍቃን ድርጅቶች ማህበርተኛ አድርገዋታል::  አባ ጳውሎስ ለስሙ መነኮሱ እንጂ የምናኔን ጉዳይ አያውቁትም ስለዚህም አይፈልጉትም  ደግሞም የኖሩት አሜሪካን አገር የተማሩት በፕሮቴስታንት ዩኒቨርሲቲ ስለሆነ አይፈረድባቸውም::  የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ግን እሳቸውና መሰሎቻቸው እንደሚሉት ምድራዊት ሳትሆን ሰማያዊት ነች:: አገልግሎቷም ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሕብረት ያለው በመሆኑ በሚታይ አገልገሎት የማይታይ ሰማያዊ ፀጋ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ለልጆችዋ እያሰጠች ገነትን ብሎም መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ የምታደርገን ነች:: ከመንፈሳዊው እውቀትም ሆነ ከፀጋ እግዚአብሔር የጎደላት ነገር ስለሌለ ወደ ሌሎቹ ቅልውጥ መሄድ አያስፈልጋትም::
ሐ / ስለ ውግዘት (ግዝት ) አጭር ግንዛቤ
       ግዝት (ውግዘት) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ 18፥15 “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው ቢሰማህ ወንድምህን ጠቀምከው ባየሰማህ ግን በሁለት ወይን በሶስት ምንክር ኣፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና ዳገመኛ ኣንድ ወይንም ሁለት ካንተ ጋር ውሰድ እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት እንደ ኣረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ:: እውነት እላችኋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል ፤ በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል::” ባለው ቃሉ መሰረት የቤ/ክ ኣባል ሆኖ እያለ የሃይማኖት ወይም የከፋ የምግባር ሕጸጽ ሲገኝበት ተደጋግሞ ተመክሮ ኣልመለስ ያለ ሰው ከቤ/ክ ኣንድነት የሚለይበት የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ ነው:: በዘመነ ሐዋርያትም በሐ.ሥ.8፥18-23 እንደምናነበው ሲሞን የተባለ መናፍቅ የማያምንበትን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በገንዘብ ለመግዛት ፈልጎ ቅ/ጴጥሮስን በጠየቀው ጊዜ ቅ/ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መልሶለታል::”የእግዚኣብሄርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ ኣስበሃልና ብርህ ከኣንተ ጋር ይጥፋ:: ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር እድል ፋንታ የለህም:: እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሃ ግባ ፡ ምናልባት የልብህን ሃሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ  ወደ እግዚአብሔር ለምን ፡ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና::” በማለት አውግዞታል:: ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅዱሳን አባቶቻችን በየጊዜው የሚነሱትን መናፍቃን እያወገዙ ሃይማኖትንና ስርዓትን እያጸኑ አሁን ላለው ትውልድ አስረክበዋል:: የተወገዘው ሰው ከቤ/ክ አንድነት ይለያል ከምሥጢራተ ቤ/ክ አይሳተፍም ጳጳስ ከሆነ በማንኛውም  በጸሎትም ሆነ በቅዳሴ ስሙ ተጠርቶ አይጸለይለትም  ቢሞት ጸሎተ ፍትሃት አይደረግለትም::ሊቃውንት አባቶቻችንም ለመናፍቃንና ለከሐድያን እንዳንጸልይ ያዘዙንን ሃይማኖተ አበው የተባለውን መጽሐፍ መመልከት ነው::  መናፍቁ ተወግዞ የሚለይበት ምክንያት በተሳሳተ ትምህርቱና በመጥፎ ምግባሩ ሌሎች ምእመናንንም እንዳይበክልና እሱም ከምእመናን አንድነት በመለየቱ ተጸጽቶ ከጥፋቱ እንዲመለስ ነው:: በእንቢታው ጸንቶ ንሰሃ ሳይገባና  አስፈላጊውን ቀኖና ተቀብሎ ከግዝቱ ሳይፈታ ከሞተ እንደታሰረ ሲኦል ይወርዳል::
   በኛ ዘመን ያለውን ለሰሚው ግራ የሆነውን የሃይማኖት ሁኔታ ስንመለከት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መሪዎች በሐ.ሥ 20፥28 “ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚኣብሔር ቤ/ክ ትጠብቌት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት ኣድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ::” ተብሎ የተሰጣችውን ሥልጣንና ኣደራ ችላ በማለት በተቃራኒው በማቴ. 23፥13 “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግስተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዩላችሁ እናንተ ኣትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ::” ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን እንደዘለፋቸውና በዚህ ምክንያት በመስቀል ላይ በኣምስት ችንካሮች ቸንክረው እንደሰቀሉት እንደ ኣይሁድ ካህናት ሆነው ተገኝተዋል:: ይህም ቀደም ባሉት ሁለት ርእሶች ማለት “ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ” እና “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” በሚሉት ርዕሶች በቂ  ትንታኔ ተሰቶበታል:: ለዚህም በዋናነት ፓትሪያርኩ ኣቡነ ጳውሎስና ተከታዮቻቸው ፤ ችግሩን እያወቁ እውነቱን በመመስከር ፋንታ ገና ለገና ከቤ/ክ እንባረራለን በሚል ፍርሃትና በምን ቸገረኝነት ዝምታን የመረጡ ጳጳሳትና ሊቃውንት በእለት ተእለት ኣገልግሎታቸው ምእመናንን በጥምቀት በቁርባን ከእግዚኣብሔር የጸጋ ልጅነት የማሰጠት ከፍተኛ ሃላፊነት ያለባቸው ካህናትና ዲያቆናት ሁሉ ከሰው ይልቅ ለእግዚኣብሔር መታዘዝ ሲገባቸው ለደሞዝና ለጊዜያዊ ጥቅም ብቻ ሲሉ የተወገዘውን ሰው ብፁዕ ወቅዱስ እያሉ በጸሎትና በቅዳሴ በመጥራታቸው እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የነሱኑ ዓላማ ለማሳካት በገንዘብም ሆነ በማንኛውም ነገር የሚራዱ ምዕመናን ጭምር ለቤ/ክ ጥፋት ተጠያቂ ናቸው:: ታላቁ ሊቅ ኣለቃ ኣያሌውም ግን ጥፋተኞችንና ተባባሪዎቻቸውን ኣውግዘው በሥጋ ከዚች ዓለም በሞት ተለይተዋል::
መ/  ውግዘቱን ላለመቀበል የሚቀርቡ ኣጉል ምክንያቶች
 1/  ማንም ካህን ቢያሳልመን መስቀሉ የክርስቶስ እስከሆነ ድረስ እኛ ምን ኣገባን? የሚሉ ሰዎች ኣሉ:: ለዚህ መልሱን በጥያቄ ብንመልሰው መስቀሉ የክርስቶስ መሆኑ የሚያጠያይቅ ኣይደለም ግን መስቀሉን ከብረት የሰራው ኣንጥረኛ ከእንጨት የቀረጸው ኣናጢ ወይንም ደግሞ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውጭ የሆነ የእምነት ድርጅት መሪ ሊያሳልመን ይችላል ወይ  ቢባል የማንም ኦርቶዶክሳዊ መልስ ኣይደረግም ኣይታሰብም ነው መልሱ:: ምክንያቱስ ቢባል በጌታችን መስቀል የሰውን ኃጢኣት ሊያስርና ሊፈታ የሚችለው ሥልጣን ክህነት ያለው ካህን ብቻ ስለሆነ ነው:: ስለዚህ ክህነት የሌለው ወይንም ክህነቱ በውግዘት የተያዘበት ካህንም ይሁን ፓትርያርክ ለይስሙላ ቢባርከን የሚገኝ በረከት እንደሌለ መረዳት ይኖርብናል::
 2/  በቅዳሴውም በኩል ያለው ኣስተያየት ከላይኛው ሃሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው ክህነቱ ከተያዘበት ሕብስቱን ወደ ክርስቶስ ሥጋነት ወይኑን ወደ ክርስቶስ ደምነት መለወጥ እንዴት ይችላል? ይችላል የሚል ካለ እንስማውና እንማርበት:: ከዚህ በተጨማሪ ካህናቱ ቢወገዙም  የሚቀድሱት መላእክት ናቸው የሚባልም ኣባባል ይደመጣል:: ይህም ኣያስኬድም እንዲያውም ለመላእክት ያልተደርገ ለካህናት ተደረገ ተብሏል:: ካህናት የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን በእጃቸው ሲፈቱት መላእክት ግን ለዚህ ኣገልግሎት ኣልተመደቡም:: በቅዳሴ ማርያም ትርጕም ቁ . 8 “ከእሳት ከነፋስ የተፈጠሩ ኪሩቤል ሱራፌል ሊይዙት የማይቻላቸው መለኮት የተዋሐደው ቁርባን ነው ” በማለት አባ ሕርያቆስ  አረጋግጦልናል ::የመላእክትም ቅዳሴያቸው “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚኣብሔር ምሥጋናህ በሰማይና በምድር የመላ ነው...” ኢሳ. 6፥3 እያሉ ማመስገን ነው::
3/  ሌላው እንደ ምክንያት የሚቀርበው ሃሳብ እግዚአብሔር ፈቅዶ ስላስቀመጣቸው ምንም ማድረግ አንችልም የሚለው ነው:: ሆኖም ይህ ሃሳብ የራሳችንን መንፈሳዊ ግዴታ መወጣት ስላቃተን እራሳችንን በራሳችን እያታለልን እንደ ማምለጫ የምንጠቀምበት ሃሳብ ካልሆነ በስተቀር ብዙ የሚያስኬደን ሃሳብ አይደለም:: ምክንያቱም እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን ለመናፍቅ ወይንም ለከሃዲ አሳልፎ ይሰጣታል ወደ ማለት ይወስደናል:: ጌታችንም ቤቴ የጸሎት ነች እንጂ የወንበዴዎች ዋሻ አይደለችም ብሎ ቤተ መቅደሱን ካጸዳ በኋላ እኛም እንዲሁ እንድናደርግ አዝዞናል::ምናልባት ደግሞ የሕዝብ ኋጢያት ሲበዛ እግዚአብሔር የአገርም ሆነ የቤ/ክ ክፉ መሪ ያስቀምጣል ብለንም አስበን ከሆነ ከኋጢያታችን በንሰሃ ተመልሰን ፈጣሪያችን አብያተ ጣኦታት ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ የሚል የቤ/ክ መሪ እንዲሰጠን አጥብቀን ባለማልቀሳችን ይኸው እንደምናየው የቤ/ክ ችግሮች ከእለት ወደ እለት እየጨመሩ ናቸው::
4/  ሌላው ምክንያት ካህን ጳጳስን ብሎም ሊቀ ጳጳስን መገዘት አይችልም እንዲሁም ካህን ያወገዘውን ጳጳስ ይፈታዋል የሚለው ሲሆን ለዚህም መልሱ እንደሚመለከተው ነው::
     ሀ/ ካህንና ሊቀ ጳጳስ (ፓትሪያርክ) ልዩነታችው የአስተዳደር (የሹመት) እንጂ ኋጢያትን የማሰርና የመፍታት ሥልጣናቸው አንድ ነው:: ማረጋገጫውም የሁሉም አለቃቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናት አለቃ ተብሎ መጠራቱ ነው:: ስለዚህ ሊቀ ጳጳስ ለውግዘት የሚያበቃው ጥፋት ካጠፋ  ካህኑ ሊያወግዘው ይችላል::
    ለ/ ካህን ሊቀ ጳጳስን መገዘት አይችልም የሚለው በፍትሐ ነገሥት የተቀመጠው ህግም ጳጳሱም ሆነ ሊቀ ጳጳሱ እውነተኛ የተዋህዶ አባቶች በሆኑብት ሥርዓት እንጂ አሁን እኛ እንዳለንበት ዘመን መሪዎሹ ስተው የሚያስቱ በሆኑበት ሁኔታ አይደለም::
5/  አለቃ አያሌው ከዚህ ዓለም በሞት ከመለያታቸው በፊት ግዝቱን መፍታት ነበረባቸው የሚልም ሃሳብ አለ:: ለዚህም መልሱ አጭር ነው:: ይኸውም ግዝት ሊፈታ የሚችለው  በመጀመሪያ  የተወገዘው ሰው ስህተቱን አምኖና አርሞ የቤ/ክ ሥርዓት በሚያዘው መሰረት ቀኖናውን ተቀብሎ ሲቀርብ ነው:: ታዲያ ከምዕመናን ጀምሮ እስከ ፓትርያርኩ ድረስ  አሁን ከምናያው ጥፋት ምን የታረመ ነገር አለ? እንኳን ሊታረሙ ቀርቶ ከጥፋቱ ዓይነት ምንም እንዳይቀራቸው የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ መሆናቸው በአደባባይ የሚታይ ስለሆነ ማስረጃ አያስፈልገውም::
6/  ቤ/ክንን ከመናፍቃን እንድንከላከል እኛም ከተወዘ ስራቸው እንድንጠበቅ አለቃ አያሌው  ያስተላለፉትን አጠቃላይ መልእክት በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ ቤ/ክ አትሂዱ፣ መስቀል አትሳለሙ ፣አትቁረቡ፣ ማለታቸው ነው እያሉ  ምዕመናንን የሚያደናግሩ አንዳንድ ተንኮለኞችም አሉ:: እውነቱ ግን ከላይ በዝርዝር የተቀመጠው ነው::
        እንግዲህ ማንም ሰው አስቀድሞ የተወገዘን ሥራ ከሰራ በራሱ የተወገዘ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያረጋግጡልናል:: የቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን ባስተላለፉት ግዝት እስከ ምፅአት ድረስ የሚነሱ መናፍቃን ሁሉ የታሰሩ (የተገዘቱ) ናቸው:: በጥቂቱ ለመጥቀስ ቅዱስ ጳውሎስ በገላ 1፥ 8  “እኛም ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን::” እንዲሁም በሥርዐተ ቅዳሴ ላይ ዲያቆኑ የቅ/ጳውሎስን መልእክት ሊያነብ ሲወጣ የሚናገረው “ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወደው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በሁለት ወገን ድንግል ከምትሆን ከቅድስት ማርያም መወለዱን የማያምን ሁሉ እንግዳ እስከሚሆን ምጽአቱ ድረስ ጳውሎስ እንደተናገረ የተለየ ይሁን ” የሚለው ቃሉ እና ሌሎችም አባቶች ያስተላለፉት ግዝት በህይወተ ሥጋ እያሉም ሆነ ከሞቱ በኋላ ቃላቸው ይሰራል::  ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌውም ያደረጉት ይህንኑ ነው :: እኛም በጊዜው የእሳቸው ጥሪ ተከትለን ቅድስት ቤ/ክንን ከጥፋት ለማዳን ባለመተባበራችን ስንፍናችንን የተመለከቱ  የቤ/ክ  የውጭና የውስጥ ጠላቶች ሃይማኖታችንንና ሥርዓታችንን ማበላሸታቸው አንሷቸው ይኸው እንግዲህ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን እስከ ማፍረስ ደርሰዋል:: እንግዲህ ለእኛ የሚስማማን ዘይቤያዊ አነጋገር “ ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ ::
     ያለንበት ችግር ይህንን ከመሰለ ለመፍትሔው  ከእኛ ምን ይጠበቃል? መልሱን የእግዚአብሔር ቃል ይሰጠናል:: እንደ  ፈቃዱ በሌላ ጊዜ እንገናኝ ::

No comments:

Post a Comment