Tuesday, August 14, 2012

"ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ" ማቴ ፳፬ ቁ. ፬ ክፍል ፬

"ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ" ማቴ ፳፬ ቁ. ፬ ካለፈው  የቀጠለ...
      የተከበራቸሁ አንባብያን ከላይ በተጠቀሰው ርእስ በሶስት ክፍሎች እንዳነበባችሁት በፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ስም የተዘጋጀው  የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ስርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት የተባለው የኑፋቄ መጽሀፍ በነገረ ማርያምና በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ላይ የሚያስተላልፈውን የተሳሳተ መልእክት ከብዙው በጥቂቱ ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ጽሁፍ  ደግሞ የምሥጢረ ሥጋዌን ትምህርት የሚያፋልሰውን ክፍል እንመለከታለን::
     ፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስና ተከታዮቻቸው ተዋህዶ ሃይማኖታቸንን ለመበረዝና ለመከለስ ብሎም ለካቶሊክና ለሌሎች የመናፍቃን ድርጅቶች የገቡትን ቃል ለመፈጸምና እኛን ለማታለል ሲነሱ የሄዱበት የተንኮል መንገድ በጣም ያስገርማል:: (ዝርዝሩን በኋላ እንመጣበታለን ) ይኸውም በመጽሐፉ ከገጽ 82-97 የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ቅድመ  ክርስትናና በዘመነ ክርስትና የነበራት የውጭ ግንኙነት በሚለው ርዕስ ቤተ ክርስቲያናችን የምትቀበላቸውን ሦስቱን ጉባኤያት ማለትም
1/  በ325 ዓ.ም 318 ሊቃውንት ተሰብስበው “  ወልድ ፍጡር ነው” የሚለውን አርዮስን ያወገዙበትን ጉባዔ ኒቅያን
2/ በ381 ዓ.ም 150 ሊቃውንት ተሰብስበው “  መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል” የሚለውን መቅዶንዮስን ያወገዙበትን ጉባዔ ቁስጥንጥያን
3/ በ431 ዓ.ም 200 ሊቃውንት ተሰብስበው “  እመቤታችን ወላዲተ አምላክ አትባልም ክርስቶስም ሁለት አካልና ሁለት ባህርያት አሉት” የሚለውን ንስጥሮስን ያወገዙበትን ጉባዔ ኤፌሶንን
 በመጠኑ ካሳዩ በኋላ በ451  ዓ.ም የተሰበበውን፤  ለቤ/ክ ሁለት መከፈል ምክንያት የሆነውንና የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  የማትቀበለውን የኬልቄዶንን ጉባዔ ግን  በዝምታ አልፈውታል::በገጽ 98 ደግሞ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የውጭ ግንኙነት ከኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ በማለት ይጀምራሉ:: እዚህ ላይ እንግዲህ ስለ ኬልቄዶን ጉባዔ ማብራሪያ ሳይሰጡ ያለፉት ቀጥሎ ለሚያመጡት የክህደት ስራቸው ምስክር እንዳይሆንባቸው በማሰብ ነው:: የማይገለጥ የተከደነ ስለሌለ እነሱ በዚህ ሁኔታ ይለፉት እንጂ  በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ነገሩ ከሆነ ጀምሮ ስለምታውቀው ይህ የክህደት ትምህርት ወደ ቤ/ክ እንዳይገባ  አጥሯን አጥብቃ ስትከላከል ቆይታለች:: ሆኖም የእኛ ሳይሆኑ እኛን መስለው በዲቁና፤በቅስና፤በምንኩስናና በጵጵስና እንዲሁም በሊቀ ጵጵስና ደረጃ ሳይቀር በተሰየሙ የቤ/ክ አገልጋዮች አማካይነት በፓትርያርኩ በአባ ጳውሎስ ትእዛዝ  ይህን አባቶቻችን ያወገዙትን የክህደት ትምህርት ወደ ቤ/ክ በማስገባታቸው የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ይህ ነው ለማለት የማንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል::በዚህ አጭር ጽሁፍ አወዛጋቢውን የኬልቄዶን ጉባዔ ዝርዝር ጉዳይ ለማሳየት ስለማይቻል ለግንዛቤ ያህል ብቻ ጥቂት እንመለከታለን::
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የኬልቄዶንን ጉባዔ የማትቀበልባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች
1/ በ431 ዓ.ም 200 ሊቃውንት ያወገዙትን “ ክርስቶስ ሁለት አካልና ሁለት ባህርያት አሉት”የሚለውን የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት በማደስ  ልዮንና ተከታዮቹ “ አንድ አካል ሁለት ባህርይ” በማለታቸው ሲሆን በሌላ አገላለጽ አካል የሌለው ባህርይ ስለሌለ ባህርይውን ሁለት ካሉ አካሉንም ሁለት ማለታቸው ስለሆነ::
2/ ጉባዔውን ያዘጋጁት ክፍሎች እራሳቸው መናፍቃን ስለሆኑ
3/ ንጉሡ መርቅያንና ንግሥቲቱ ብርክልያ በማያገባቸው የሃይማኖት ጉዳይ ገብተው ለራሳቸው ዝና ለማትረፍ  ብቻ ሲሉ ያዘጋጁት ጉባዔ ስለሆነ
4 /እንደ ሦስቱ ጉባዔያት የጉባዔው ዓላማ በግልጽ ታውቆ አውጋዡና ተወጋዡ ያልተለየበት በመሆኑ
5/እውነተኞቹ የሃይማኖት አባቶቻችን እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በጉባዔው የመናገር እንኳን እድል ሳይሰጣቸው ተገፍተውና ተደብድበው እንዲገለሉ የተደረበት ስለሆነ
    በነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ይህ ጉባዔ ” ጉባዔ ከለባት” ወይም “የውሾች ጉባዔ“ ተብሎ ይጠራል::ይህም አባባል አዲስ አይደለም ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ የቤ/ክንን ሰላም ከሚያውኩ መናፍቃን እንድንጠበቅ ” ከውሾች ተጠበቁ፤ከክፉዎች ሰራተኞች ተጠበቁ፤----”(ፊሊጵ. 3፥2) በማለት አስጠንቅቆናል::
    እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ  ከራሳቸው አልፈው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክንን የካቶሊክና የሌሎቹም የመናፍቃን ድርጅቶች አባል ለማድረግ አልመው የተነሱት አባ ጳውሎስና ተከታዮቻቸው” ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነች ይሏታል “ እንድሚባለው የኬልቄዶንን ጉባዔ ውግዘት ምክንያቱ እስከ ዛሬ የማይታወቅ ይመስል ስለ ውግዘቱ አዲስ ጥናት እንዳደረጉና የጥናቱንም ድምዳሜ ለመግለጽ በመጽሐፉ ከገጽ 105 - 111 ደረስ ካቀረቡት ጽሁፍ ውስጥ ለግንዛቤ ያህል አለፍ አለፍ ብለን እንመለከታለን::
ምእራፍ 27 ገጽ 108—111 (በከፊል)
በኦየንታል  ኦርቶዶከስ አብያተ ከርስትያናትና በምስራቅ  ኦርቶዶከስ አብያት ክርስትያናት መካከል ምሥጢረ ሥጋዌን በተመለከተ የተደረገ ውይይት
    የክልቄዶን ጉባኤ  እስክተደረገበት እስከ 451 ዓ.ም ድረስ ቤተ ክርስቲያን በእምነትና በሥርዓተ አምልኮት አንዲት እንደነበረችና አሁንም ክርስቶስ አንድ እስከሆነ ድረስ ቤተክርስቲያንም ምንግዜም አንድ እንደሆነች መላው የክርስትና ዓለም ያምናል:: ከኬልቂዶን ጉባኤው በኋላ ግን በጉባዔው ላይ በምሥጢረ ሥጋዌ ምክንያት ቤተክርስቲያን ለሁለት ተከፋፍላ ቆይታለች:: ለመለያየትም ምክንያት የነበረው ዐቢይ ነጥብ የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት  ወገኖች ስለ ክርስቶስ ምሥጢረ ሥጋዌ ያላቸውን እምነት “በአንድ አካል ሁለት ባህርይ : ሁለት ፈቃድ : ሁለት ግብር” በሚል ቃል ሲገልጹ የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ “ አሐዱ ባህርይ ዘእግዚአብሔር ቃል ሥግው” የሚለውን የቅዱስ ቄርሎስን የእምነት አገላለጽ መሠረት በማድረግ “ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን  ከነፍሷዋ ነፍሱን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ ያለመከፋፈል ፤ያለመነጣጠል ፤ያለመጠፋፋት ፤ያለመለወጥ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ በተዋህዶ ነው” ብለው እምነታቸውን ስለሚያረጋግጡ ነው::
     ይህ የእምነት አገላለጽ ልዩነት ከኬልቄዶን ጉባኤ ከ451 ዓም እስከ አለንበት ዘመን ድረስ ለረጅም ጊዜ አለያይቶን ቆይቷል::
      ይሁን እንጂ በአሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ለልዩነቱ ምክንያት ሆኖ የቆየው ይህ የምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ሆኖ እያለ በምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ቤተ ክርስቲያን ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት የሆነው በቃላት የአገላለጥ ልዩነት እንጂ በሁለቱም በኩል የተዋህዶው መሠረተ እምነት አንድ መሆኑ ተጠቅሶ ወደፊት ወደ አንድነት ሊያመጣ የሚችል የጋራ ውይይት መድረክ ተደረገ:: በዚሁ መሰረት ይፋ ያልሆኑና የሆኑ ሰባት የጋራ ጉባኤያት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ተካሂደዋል::
ጉባኤያቱም:
1/ በአርሁስ ዴንማርክ እኤአ ነሐሴ 11 - 15 ቀን 1964
2/ በብሪስትል ኢንግላንድ እኤአ ነሐሴ 25 - 29 ቀን 1967
3/ በጄንቫ ስዊዘርላንድ እኤአ ነሐሴ 16 - 21 ቀን 1971
4/ በአዲስ አበባ ኢትዮጲያ እኤአ ጥር 21 - 22 ቀን 1971
5/ በአባይ ቢሾይ ገዳም ግብጽ እኤአ 1989
6/ ቻምቤዚ ስዊዘርላንድ እኤአ 1990
7/ ቻምቤዚ ስዊዘርላንድ እኤአ ህዳር 1 6 ቀን 1993 የተካሄዱት ነበሩ::
በነዚህ ጉባኤያት ሁሉ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ከ በመልዕክተኞቿ መሰረት ተሳትፋለች::
    በጉባኤያቱ ሁሉ የክልቀዶኑ ውግዘት መነሻ ምክንያቶች ተመርምረዋል:: በመጨረሻም ቻምቤዚ ስዊዘርላንድ  ህዳር 1 6 ቀን 1996 ዓ.ም እ.ኤ.አ በተደረገው ጉባኤ በምሥጢረ ሥጋዌ ስለ ክርስቶስ ተዋህዶ የሚሰጠው ትምህርት ልዩነት በሁለቱም ወገኖች የቃላት አገላላጽ እንጂ የእምነት አለመሆኑን ተገንዝበዋል:: ንስጥሮስንና አውጣኬን ግን የሁለቱም ወገን አብያተ ክርስቲያናት የሚያወግዟቸው መሆኑን ተገልጿል:: በመጨረሻዎቹ ሶስት ጉባኤያት ላይ በሁለቱም ወገን ያሉትን ውግዘቶች ማንሳት ስለሚቻልበት ሁኔታ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል:: ...
    ስለዚህም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ባሁኑ ጊዜ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብ : ከመለያየትም ይልቅ በኣንድነት መተሳሰብና መረዳዳት ጊዜው የሚጠይቀው መንፈሳዊና ማህበራዊ ግዴታ ከመሆኑም በላይ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው የምሥጢረ ስጋዌ ትምህርት ልዩነት ከሚወገድበት ደረጃ ላይ እንዲህ ከተደረሰ በእምነትና በሥርዓት ከሚመስሏት እህት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በአንድነት መክራ ወደ ፊት በሚደረገው ጉባኤ አንድ አካል ሁለት ባህርይ በተዋህዶ  ከማለት ይልቅ ያለመከፋፈል ፤ያለመነጣጠል ፤ያለመጠፋፋት ፤ያለመለወጥ (በተሃቅቦ) ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ በተዋህዶ  አሐዱ ባህርይ ዘእግዚአብሔር  ቃል ሥግው በሚለው እምነት ከአንድነት ደረጃ ላይ ቢደረስ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የመቀራረቡን ሃሳብ የማትቃወም መሆኗን ታረጋግጣለች::
         እንግዲህ ከላይ ከመጽሐፉ ጠቅሰን  እንዳየነው እነ አባ ጳውሎስ የሄዱበትን የተንኮል መንገድ ለአንባብያን ግልጽ ለማድረግ ዋና ዋናዎቹን ችግሮች እንመለከታለን ::
1 /በአሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና  በምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በማለት የገለጹትም አንዱ የማጭበርበሪያ ስልታቸው ነው::ምክንያቱም ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል ሁለቱም አንድ ናቸው ለማለት ያሰቡትን የክህደት ሃሳብ ይደግፍልናል ብለው ስላሰቡ ሲሆን እውነቱን ግን
 ሀ/ የአሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሚለው ስም ሰው የሆነው አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  አንድ አካልና አንድ ባህርይ ነው ብለን የምናምን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናትን ይወክላል::
ለ/ የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት  የሚለው ስም ደግሞ ክርስቶስ “አንድ አካል ሁለት ባህርይ : ሁለት ፈቃድ : ሁለት ግብር” አለው ብለው የሚያምኑና  እነ ቅ/ዲዮስቆሮስ ያወገዟቸው  የኬልቄዶን ጉባዔ አባላት ናቸው::
2/  የኬልቄዶን ጉባዔ አባላት እምነት “በአንድ አካል ሁለት ባህርይ ሁለት ፈቃድ ሁለት ግብር” በማለት የሚገልጹት ሥጋ የሥጋን ሥራ ይሰራል፤መለኮትም የመለኮትን ሥራ ይሰራል የሚል ትርጉም ያለው  ሲሆን በዚህ እምነታቸው  እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን  ከነፍሷዋ ነፍስን ነሥቶ  አንድ አካልና አንድ ባህርይ መሆኑን ይክዳሉ :: እነ አባ ጳውሎስ ግን ይህንን የብርሃንና የጨለማ ያህል የተራራቀውን ልዩነታችንን  የቃላት ልዩነት ብቻ ነው በማለት ለማጭበርበር ሞክረዋል::
         በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቀድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ግን አስቀድሞ ከነቢያት፤ቀጥሎም ከጌታችን ከዚያም ከሐዋርያት ባገኘችው የምሥጢረ  ሥጋዌ ትምህርት እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን  ከነፍሷዋ ነፍስን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ በአንድ አካልና  በአንድ ባህርይው  በጽንስ ጀምሮ በመስቀሉ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራውን  ታምናለች፤ታሳምናለች:: ምስክሯም
      1/  ማቴ .16፥16 “ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ”
     2/  ማር .1፥1 “ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ ”
     3/ ሉቃ.1፥35 “ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ”
     4/ ዮሐ. 1፥ 14 ”ቃልም ሥጋ ሆነ “  የሚሉትና ይህንን የመሳሰሉት ሁሉ ናቸው::
3 / እነ አባ ጳውሎስ በዚህ አባባላቸው እውነተኞቹን የተዋህዶ አባቶች እነ ቅ/ዲዮስቆሮስ  የሁለት   ባህርይና  የአንድ ባህርይ ትርጉም እንኳን ያልተረዱ “ጨዋዎች” (ያልተማሩ)  እንደሆኑ ተናግረዋል::
4/ በሃይማኖት ከማይመስሉን ሁሉ እንድንለይ በወንጌል ታዘናል::ቅ/ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮ. 6፥14-18 --  ”ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ---” ብሎ ያስተማረውን መሰረት በማድረግ ቅዱሳን አባቶቻችን መናፍቃንን እየለዩና እያወገዙ ሃይማኖትን አጽንተው ለኛ አስረክበዋል::እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የተለያየነውም ከላይ እንደገለጥነው በምሥጢረ ሥጋዌ  ምክንያት መሆኑ እየታወቀ አሁን በእነ አባ ጳውሎስ ምክንያት ከመናፍቃኑ ጋር መደባለቃችን የሰይጣን ሥራ መሆኑ ቀርቶ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሆነ በመግለጻቸው  የሰው አንሷቸው በእግዚአብሔርም ላይ ዘብተዋል:: መንፈስ ቅዱስንም  የሰደበ ኃጢአቱ አይሰረይለትም::
5 / “ አንድ አካል ሁለት ባህርይ በተዋህዶ ” ያሉትም ሌላው የማጭበርበሪያ መንገዳቸው ነው::
ሁለት ባህርይ  ካሉ ተዋህዶ የሚለውን ቃል መጠቀም የለባቸውም::ምክንያቱም ሁለት ባህርይ “ ቃልም ሥጋ ሆነ ” የሚለውን የወንጌል ቃል ስለሚያፈርሰው ነው::
        ውድ አንባብያን እንግዲህ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና ሥርዓታችን በመሪዎችዋ ምክንያት ምን ያህል እየተዛባ እንደሆነ ከብዙ በጥቂቱ  ለማሳየት ሞክረናል::
 የዚህን ጽሁፍ ማጠቃለያ ደግሞ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን ለዛሬው ይቆየን::

No comments:

Post a Comment