Monday, August 13, 2018

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ሃያ ስድስት

ከክፍል ሃያ አምስት የቀጠለ
የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤ ክፍል ሁለት
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
       ባለፈው ጽሁፋችን በክፍል ሃያ አምስት ሁለቱን ሲኖዶሶች ወደ አንድነት ለማምጣት የተደረገውን የጋራ ስምምነት መግለጫ አስነብበናችሁ፤ቀጣዩን ክፍል በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡በገባነው ቃል መሠረት እነሆ ዛሬ ሁለተኛውን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡
መልካም ንባብ!

       የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ፤ ለዚህ ጸሁፉ መነሻ ያደረገው፤የእርቅ ስምምነቱ በተካሄደበት በአሜሪካ አገር ዋሽንግተን ዲሲ ላይ፤ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ለአንድነቱ ማብሰሪያ የሆነው "ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላም ስምምነት"ን ነው፡፡ዓላማውም በስምምነቱ ላይ ከሰፈሩት ሃሳቦች ውስጥ የቤ/ክ ልጆች የሆንን ሁሉ አጽንኦት ስጥተን ልንወያይበትና ካህን ምእመን ሳይባል ከጾምና ጸሎት ጋር ከልብ በመሥራት፤ በአባባይ ሲዘበትባት የኖረችውን ቤተ ክርስቲያናችንን  ወደ ነበረችበት ልንመልሳት ይገባል ብሎ ያመነበትን ፍሬ ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡   መግለጫው በስድስት ነጥቦች ተከፍሎ የተቀመጠ ሲሆን ለዛሬው ውይይታችን የፈለግነው በተራ ቁ.2 "ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት" ከሚለው ርዕስ ውስጥ ፤
ሀ/ "የቀኖና ጥሰት...ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን"
ሐ/ "ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን አለመወጣቱ"
መ/ "በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቤ/ክ ልጆች…ይቅርታ እንዲጠይቅ" …..በሚሉት ላይ ሃሳቦች ላይ ሲሆን፤ በቅደም ተከተል ጥቂት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡
       ወደ ዋናው ሃሳብ ከመግባታችን በፊት ስለ ፓትርያርክ ሹመት፤ የህግና የሥርዓት ባለጸጋ የሆነችው ቅድስቲቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤ "ፍትሐ ነገሥት" በተባለው የሥርዓት መጽሐፍ፤ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አራት ላይ፤ "በአንድ ዘመን በአንድ ወንበር ሁለት ሰዎች ሊሾሙ አይገባም…..በአንድ ሀገር ሁለት ሰዎች ተሹመው ቢገኙ አስቀድሞ ለተሾመው ሰው ትጽናለት" የሚለውን ቁልጭ ያለና የማያሻማ ቃል በአንክሮ ልንመለከተው ይገባል፡፡
 ሀ/ "የቀኖና ጥሰት"
       ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን የፍትሐ ነገሥቱን ህግ ይዘን ወደ ዕርቀ ሰላም ስምምነቱን ሃሳብ ስንሄድ፤ በአንድ በኩል 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው መሰደዳቸውና እሳቸው በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ በመሾሙ የቀኖና ጥሰት ስለተፈጸመ እሳቸው ወደ መንበራቸው ተመልሰው ቡራኬ እየሰጡ እንዲቀመጡ ሲወሰን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቀኖና ተጥሶ ለተሾሙት 6ኛው ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ  ማትያስ ተገቢው ቦታ መስጠት ፋንታ ፓትርያርክነታቸውን እንደያዙ ቡራኬ መስጠቱንና የአስተዳደሩን ሥራ እንዲሰሩ የሚል ውሳኔ አሳልፎዋል፡፡ይህ አካሄድ ደግሞ "ተጣሰ"ተባለውን ቀኖና የሚያስተካክል ሳይሆን በሁለቱም በኩል ያለውን ፍላጎት ጠብቆ እርቁን እንደምንም ለመጨረስ ብቻ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ ቀድሞ በነበረው ላይ ሌላ የቀኖና ጥሰትን አስከትሏል፡፡በእውነት ቀደም ብሎ የተጣሰውን ቀኖና ለማስተካከል ታስቦ ቢሆን ኖሮ፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በእድሜም መርዘምም ሆነ በሕመም ምክንያት መሥራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የፓትርያርኩ እንደራሴ ሆነው ይሰሩ እንደነበረው፤ዛሬም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ተገቢውን ሥራ ለማከናወን የማይችሉ ቢሆን እንኳን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሁን የሚሰሩትን ሥራ በፓትርያርክነት ሳይሆን በእንደራሴነት እንዲሰሩ መደረግ ነበረበት፡፡
       በሌላ በኩል  ደግሞ ምንም እንኳን ሁላችንም እርቁ በተከናወነበት ጊዜና ቦታ ባንገኝም፤ በህሊናችን እነሱ ወደ ነበሩበት ቦታ ተጉዘን ስንመለከተው፤ ስምምነቱን የፈጸሙት አባቶችና በአሸማጋይነት የተላኩት የኮሚቴ አባላት እርቁን እውን ለማድረግ፤ ከነበሩበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስንመለከተው በጊዜው ከዚህ የተሻለ የስምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጁ አይጠበቅባቸውም፡፡ምክንያቱም፤
አንደኛ/ የእርቁ ጉዳይ ለብዙ ጊዜያት ተሞክሮ ሳይሳካ በመቆየቱና፤ አሁንም በሁለቱም በኩል ያለውን ፍላጎት የሚያሟላ ውሳኔ ካልተወሰነ በስተቀር ጉዳዩ ሊሰምር አይችልም የሚል ስጋት በሁሉም ዘንድ ስለነበረ እንደምንም አቀራርቦ ለመጨረስ ሲባል፤
ሁለተኛ/ ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የቤ/ክ አባቶችን "እናንተ ሰላምና አንድነት ፍጠሩና ለእኛም አርአያ ሁኑን" እያሉ ባለማሰለስ ሲያሳስቡ ቆይተው( የአባቶች ልብ ወደ ልጆች ስለ ዞረ) በመጨረሻም ስምምነቱን ለመፈጸም ሲኖዶሱን ወክለው ወደ አሜሪካ የሄዱትን አባቶችና የሽምግልና ኮሚቴ አባላቱን እርቁን በአጭር ጊዜ እንዲፈጽሙ በሰጡት ጠንከር ያለ መመሪያ ስለነበረ፤
ሦስተኛ/ በመጨረሻ እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርቁ በተፈጸመበት ሳምንት ለሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ሄደው ስለነበር ሲመለሱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና ሌሎቹንም ጳጳሳት አብረዋቸው እንዲመጡ ስለወሰኑ፤…ወዘተ፡፡
      አሁን እየሆነ ያለውን ነገር በዚህ ሚዛናዊ በሆነ አስተሳሰብ ተመልክተን፤ የአንድ ጎልማሳ ሰው እድሜ ያስቆጠረ ችግር ቅጽበታዊ በሆነ ሁኔታ ሊስተካከል ስለማይችል ሁሉንም በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል፤አባቶቻችንም ሁኔታዎች ሲረጋጉ ለዚህ መፍትሔ ያመጡልናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡በተቃራኒው ይህንን ተስፋችንን የሚያጨልሙና የተሰራውን ስህተት ትክክል የሚያስመስሉ ሃሳቦች መንጸባረቅ ጀመሩ፡፡ሁላችንም እንዳየነው ይህንን ሰላምና አንድነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማብሰር ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም  በሚሊኒየም አዳራሽ የተደረገውን ዝግጅት፤ወደ አዳራሹ ለመግባት እድሉን ያገኘው ከሃያ ሺህ በላይ የሆነ ሕዝብ፤ በቦታው መገኘት ያልቻሉትና ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉት ሁሉ ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ሲከታተሉት ነበር፡፡(በቤ/ክ ታሪክም ተመዝግቦ የሚቀመጥ መሆኑን ልብ ይሏል)
       በዚህ መካከል ከመርሐ ግብር መሪው "ታሪክ እራሱን ይደግማል፤ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ አብርሃና አጽብሃ የተባሉት ወንድማማች ነገሥታት በአንድ ዙፋን ነግሠው አገሪቱን ሲመሩ እንደነበር፤ ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችን በአንድ መንበር ሁለት ፓትርያርኮች እንዲመሩ አድርጋለች፡፡" የሚል ጆሮ ጭው የሚያደርግ ንግግር ተሰማ፡፡ይህንን የእርቁን ስምምነት በፈጸሙት አባቶችና በአሸማጋዮቹ የመወሰን አቅም ማጣት የተነሳ የተሠራውን ስህተት፤ ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ ምሳሌ በማቅረብ ትክክለኛ አስመስሎ ለማሳየት መሞከር "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" እንደሚባለው የቀደመው የቀኖና ጥሰት በአግባቡ ሳይስተካከል አሁን ደግሞ ሌላ ያልነበረ ሕግ ቤ/ክ ላይ ተጫነበት ማለት ነው፡፡
       ምናልባት ሃሳቡ የተናጋሪው የግል ምልከታ ነው ቢባል እንኳን፤ ይህንን ትልቅ ጉባኤ እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው፤ በግል ሙያውም በቤ/ክ ታሪክ ተመራማሪነቱ የሚታወቅና ብዙ መጻሕፍትን ጽፎ ያበረከተ የሥነ ጽሁፍ ባለሙያ በመሆኑ፤ የንጉሥና የፓትርያርክ ልዩነት ይጠፋዋል ተብሎ ስለማይታሰብ፤ ማንም ሰው ሃሳቡን ስህተት ነው ብሎ ሊጠራጠር አይችልም፡፡እንግዲህ ይህ እንደ ዘበት የተነገረ እንግዳ ትምህርት በጊዜው ካልታረመ፤ ትውልዱ ለወደፊትም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በቤ/ክ በአንድ ዘመን ሁለትም ሦስትም ፓትርያርክ መሾም ይቻላል የሚል ትምህርት ይዞ ይቀርና ለቤ/ክ ሌላ ትልቅ የቤት ሥራ ተቀመጠላት ማለት ነው፡፡ከዚህም በተጨማሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እሳቸውና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሲመተ ጵጵስናቸውን ከ3ኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት የተቀበሉት በአንድ ቀን መሆኑን በማውሳት፤ አሁንም ሁለቱም ፓትርያርክነታቸውን እንደያዙ ቤተ ክርስቲያንን መምራት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ 
    እንግዲህ ይህንን ሁሉ ሁኔታ "ብልጥ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል" እንደሚባለው፤ቢያንስ የሲኖዶሱን አንድ መሆን እንደ ቀላል የሚታይ ስላልሆነ፤ ይህንን እያመሰገንንና ለሚቀረው ደግሞ እያለቃቀስን ብንነተወው እንኳን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በየትኛው የአስተዳደር ተሞክሮዋቸው ነው የአስተዳደሩን ሥራ የተረከቡት? መላዋን የኢትዮጵያን ቤ/ክ ይቅርና ልዩ ሀገረ ስብከታቸው የሆነውንና በመንበረ ፓትርያርኩ የተወሰነ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትን እንኳን በአግባቡ መርተዋል ወይ? ቀደም ብለው የነበሩት የአ.አ.ሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በሥራቸው ያሉትን የዋና ክፍል ሃላፊዎችን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያን በምትጸየፋቸውና በምታወግዛቸው እንደ ሌብነት፣ዘረኝነት፣ምንፍቅናና በመሳሰሉት አስነዋሪ ድርጊቶች ተዘፍቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሌቦች፣የወንበዴዎችና የመናፍቃን  ዋሻ ሲያደርጓት፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህግ የሚዳኝ አባት ጠፍቶ፤ ካህናትና ምእመናን ለመንግሥት ባቀረቡት አቤቱታ ሥራ አስኪያጁና ግብረ አበሮቻቸው ሳይወዱ በግድ ከሃላፊነታቸው የተነሱት በመንግሥት ህግ ተገደው አይደለም ወይ? አሁን ደግሞ ከሲኖዶሱ አንድነት ወዲህ ሀገረ ስብከቱ ሰፍቶ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡እናም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  የአመራር አቅም ይዘለቃል ወይ ብለን ስናስብ፤ ለዚህ እረኛ አጥቶ እዚህም እዚያም ለተበተነው ምእመን ልዑል እግዚአብሔር የሚበጀውን ያምጣ ብሎ ከመጸለይ በስተቀር አማራጭ የለንም፡፡
የተከበራችሁ አንባብያን!
"የቀኖና ጥሰት" በሚለው ርዕስ የጀመርነውን ጸሁፍ አላጠቃለልንም፡፡
በቀጣዩ ክፍል ይዘን እንቀርባለን
ለዛሬው ይቆየን፡፡





No comments:

Post a Comment