Friday, August 10, 2018

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ሃያ አምስት


የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
ውድ አንባብያን!
       ይህችን "emene tsion" (እናታችን ጽዮን) የተባለችውን የጡመራ መድረክ ከጀመርን ጀምሮ፤ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ” በሚለው ርዕስ አራት ክፍሎችን፣“ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” በሚለው ርዕስ ስድስት ክፍሎችን፣“ ስን ዝም አልልም ” በሚለው ርዕስ አስራ አራት ክፍሎችን፤በድምሩ በሃያ አራት ክፍሎች፤ የተለያዩ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳዩች የሚዳስሱ ጽሁፎች እንዳስነበብናችሁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ "ን ዝም አልልም"በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር  "የዶግማና የቀኖና ጥሰት"በሚል ንዑስ ርዕስ በወቅታዊው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁኔታ ላይ እንወያያለን፡፡
መልካም ንባብ!
የዶግማና የቀኖና ጥሰት በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
       እንደሚታወቀው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ አሁን እኛ አለንበት ዘመን ላይ የደረሰችው፤ ዘመን ከሚወልደው ሥርዓተ ማህበር ጋር እየተለዋወጠች ሳይሆን ከፈጣሪዋ በተሰጣት በማይናወጥ እምነት ጸንታ በመቆየቷ ነው፡፡ለእምነቷ መጠበቅ ደግሞ የሥርዓቷ (የቀኖናዋ) አጥርነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡አጥር የሌለው ቤት የእንስሳውም የአራዊቱም መፈንጫ እንደሚሆን ሁሉ፤ የሥርዓት (የቀኖና) መፋለስም በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ የእምነት ተፋልሶን ያስከትላል፡፡ ቀደም ባሉት የአገራችን የኢትዮጵያ ታሪኮች የአገሪቱ መሪዎች እራሳቸው ክርስቲያኖች ስለነበሩና ሀገር የመምራቱንም ሥልጣን የሚረከቡት፤ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ቃለ መሐላ ፈጽመው ስለነበር፤ሥጋ ለባሽ እንደመሆናቸው የተለያየ ስህተት ቢሰሩም ቤተ ክርስቲያኒቱን አክብረውና አስከብረው ኖረዋል፡፡
       1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እስከ አሁን ያሉት የአገሪቱ መሪዎች ግን እራሳቸው ሃይማኖት የለሾች ከመሆናቸው ሌላ፤ "መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው" የሚል ህግ ቢያወጡም መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡በአንጸሩ ደግሞ እንደ ወንጌሉ ቃል "ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል" ብለው ለቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዓት መጠበቅ እራሳቸው ጸንተው ምእመናኑን መጠበቅና በሃይማኖት ማጽናት የሚገባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ከተልእኳቸው ውጪ የመንግሥት ፈቃድ አስፈጻሚ እስከ መሆን ደርሰው እንደነበር እራሳችን እያየነው ስለሆነ ሌላ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡
       ከነዚህም ችግሮች ውስጥ አንዱ፤ በ1983 ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው ወርደው ወደ አሜሪካ አገር እንዲሰደዱና በምትካቸው ሌላ ፓትርያርክ እንዲሾም መደረጉ ነው፡፡በዚህ ምክንያት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና አብረዋቸው የተሰደዱት ጳጳሳት "ምንም በስደት ላይ ብንሆንም በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ህጋዊው ሲኖዶስ የእኛ ነው፤ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾም የለባችሁም " ሲሉ፤ በአገር ቤት ያለው ሲኖዶስ ደግሞ "ፓትርርኩም ሆኑ ሌሎቹ ጳጳሳት በግል ይሰደዱ እንጂ "ሲኖዶስማ አይሰደድም ህጋዊዎቹ እኛ ነን" እያሉ በመወዛገብና በመወጋገዝ ወደ 26 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ከዚህም ሌላ ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ አህጉር የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በዘርና በምንፍቅና ምክንያት ያለው ልዩነት ሳይቆጠር በሦስት ተከፍለው ቆይተዋል፡፡አንዱ ክፍል በውጭው(በስደተኛው) ሲኖዶስ የሚመራ፣አንዱ በአገር ውስጥ ሲኖዶስ የሚመራና ሦስተኛው ከሁለቱም ያልሆነ ገለልተኛ አቋም ይዞ የሚያገለግል ነበር፡፡በዚህ      ኢ-ክርስቲያናዊ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኒቱን  ምእመናን በተለይ በውጭ ሀገር ያሉት  እጅጉን ተፈትነዋል፡፡
       ከላይ በመግቢያው በጥቂቱ እንደተገለጸው፤ ለአቡነ መርቆሬዎስ መሰደድ ትልቁ ምክንያት በጊዜው የነበረው የመንግሥት ተጽእኖ ቢሆንም፤ቤተ ክርስቲያኒቱ የተፈጠረውን ችግር ተቋቁማ በራስዋ ህግና ሥርዓት መሠረት ተገቢውን ነገር ማድረግ ሲገባት፤ከመንግሥት ጋር ተባብራ ወይም ቀኖና ጥሳ፤ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ ከአንድም የሁለት ፓትርያርኮች ሹመት ፈጽማለች፡፡አሁን ሰሞኑን በተደረገው ውይይት ግን ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት የቀኖና ጥሰት ያስከተለ መሆኑ በሁለቱም በኩል ባሉት አባቶች ስለታመነበት፤ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱና  በሁለት ተከፍሎ የነበረው ቅ/ሲኖዶስ  ወደ አንድነት እንዲመጣ በመደረጉ፤ ከእኛ ከቤተ ክርስቲያኒቱ  ልጆች  አልፎ በእምነት ከእኛ ጋር አንድነት የሌላቸው ክፍሎች ሳይቀሩ የደስታችን ተካፋይ ሆነው ስንብተዋል፡፡
 የተከበራችሁ አንባብያን! ይህ በሰፊው እንድንወያይበት ወደመረጥነው ርዕስ ዝርዝር ሃሳብ ከመግባታችን በፊት፤ ከ"ሐራ ተዋሕዶ " የጡመራ መድረክ ያገኘነውን  "የዕርቀ ሰላም ስምምነት" ሙሉ ቃል እንድትመለከቱ እንጋብዛለን፡፡
"ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላም ስምምነት"
1. ስለ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፤
 በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ የተነሣ አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት ተከፍላ በሁለት ፓትርያርኮች የሚመሩ አንድ ሲኖዶስ ለሁለት ሲኖዶሶች መፈጠራቸው ግልጽ ነው። በዚህም የተነሣ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በስደት ዓለም መቆየታቸው ይታወቃል። ስለኾነም የሁለቱን ቅዱሳን ፓትርያርኮች ቀጣይ ኹኔታ በተመለከተ በሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶሶች የተወከሉት የሰላም ልኡካን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም በአደረጉት የጋራ ስብሰባ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ እንደሚከተለው በአንድ ድምፅ ወስነዋል።
 ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፓትያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ/እንዲገቡ፤
 ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ኢትዮጵያ ሲመለሱ በክብር የሚያርፉበትን የመኖሪያ ቦታ በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ ቦታ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤
 ሐ/ የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
 1.1/ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤
 ሀ/ በሕገ ቤተ ክርቲያን መሠረት የአስተዳደር ሥራውን በመሥራት ቅድስት ቤተ ክርስቲንን እንዲመሩ፤
 ለ/ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
1.2/ የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ አባቶቻችን ስም በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ፤
 1.3/ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወተ ሥጋ እስከ አሉ ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንድትይዝ፤
 1.4/ይህ ስምምነት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ፣ የአገር ቤትና የውጭ አገር ሲኖዶስ የሚለው ስም ቀርቶ አንዲት ቤተ ክርስቲያንና አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲኾን፤
 2. ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፤
 ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ በልኡካኑ ታምኖበታል። ስለኾነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ኾነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋራ አብሮ በመሔዱ፣ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ኾነ ዛሬ ላይ ያሉትን በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልኡካኑ ጉባዔ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።
 ስለኾነም ከሁለቱም ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስሕተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲዘጋጅ የልኡካኑ ጉባዔ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።
 3. ስለ ነባር ሊቃነ ጳጳሳት፤
 ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተፈቶ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶአል።
 4. ከልዩነት በኋላ ስለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፤
 ከልዩነት በኋላ በሁለቱም ወገኖች የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ፦ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭ ዓለምም ኾነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ተስማምቶአል። ስም አጠራራቸውንም አስመልክቶ እንደ ሹመት ቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ… ወዘተ እየተባሉ እንዲጠሩ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ወስኖአል።
 5. ስለ ቃለ ውግዘት፤
 በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሁለቱም ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት እንደ ተላለፈ ይታወቃል። ስለሆነም ከዚህ ስምምነት በኋላ ቃለ ውግዘቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ የሰላም ልዑካኑ በአንድ ድምፅ ወስኖአል።
 6. በውጭ ዓለም በስደት የምትገኘውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ያገናዘበ መዋቅራዊ አስተዳደርን ስለማዘጋጀት፤
 እንደሚታወቀው በዘመናችን በየትኛውም ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በአሉበት ሁሉ ተስፋፍታ ትገኛለች። ይኹን እንጂ በውጭ ዓለም የምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋራ አንድነቷን፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ክብሯን ጠብቃ መኖር እንዳለባት ጉባዔው አምኖበታል።
 ስለኾነም የየሀገሩን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ የቃለ ዐዋዲውና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ገዥነት የሚረጋገጥበት መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያዘጋጅ ልኡካኑ በአንድ ድምፅ ወስኗል። እንዲሁም በውጭ ዓለም የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በመዋቅራዊ አስተዳደር መሠረት ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በመቀበል በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንድትመራም ወስኖአል።
 በተጨማሪም በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና የሁለቱንም ሲኖዶስ መዋሐድ ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም በስደት የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው፥ የቀደመውን ሰላምና አንድነት አጽንተው፥ ሁሉም በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ኹኔታ የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡካን እንዲያዘጋጁና እንዲከታተሉ የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡክ በአንድ ድምፅ ወስኗል።
 ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም.
ዋሽንግተን ዲሲ
       የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ከላይ በመግለጫው ከሰፈሩት ሃሳቦች ውስጥ አጽንኦት ስጥተን ልንወያይባቸው ይገባል የምንላቸውን ሃሳቦች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣዩ ክፍል ይዘን እንቀርባለን፡፡ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሔ የሚገኘው በጾምና በጸሎት ጭምር ስለሆነ መልካሞቹን ቀኖች ለማየት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡

ይቀጥላል……፡፡

No comments:

Post a Comment