Friday, May 11, 2018

ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል አስራ አራት

ክፍል አስራ ሦስት የቀጠለ

ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡

የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣እንደምን ሰነበታችሁ?
       በተለያየ አገልግሎት መብዛት ምክንያት በዚች የመወያያ መድረክ ተገቢውን መልእክት ሳናሰተላልፍ በመዘግየታችን አስቀድመን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ለዛሬው ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ የፌስ ቡክ ገጻቸው ያስነበቡን ግጥም፤ ሁላችንም እራሳችንን እንድናይና አጥብቀንም እንድንጸልይ የምያበረታታ ስለሆነ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኃል፡፡
መልካም ንባብ፡፡

"የዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ስብከቶች"

"ይህችን ዓመት ተወኝ!"
ከዓመት እስከ ዓመት - ፍሬን ሳላፈራ - ደረቅ እንደሆንኩኝ
በራድ ወይም ትኩስ - ሁለቱንም ሳልሆን - እንዲያው ለብ እንዳልኩኝ
አለሁኝ በቤትህ - ለሙን መሬትህን - እያጎሳቆልኩኝ
አውቃለሁ አምላኬ - ፍሬዬን ለመልቀም - እንዳመላለስኩህ
ዛሬም ሳላፈራ - እሾህን አብቅዬ - ደርቄ ጠበቅሁህ
ያልተደረገልኝ - ያላፈሰሰክብኝ - ያልሰጠኸኝ የለም
ነገር ግን ይህ ሁሉ - አላርምህ አለኝ - አልለየኝም ከዓለም
የማትሰለቸኝ ሆይ - ተነሥቼ እስክቆም - እባክህ ታገሠኝ
የእኔን ክፋት ተወው - መልአክህን ሰምተህ - ይህችን ዓመት ተወኝ!
አውቃለሁ ታውቃለህ - ቀጠሮን ሰጥቼ - እንደማላከብር
ብዙ ጊዜ አቅጄ - ብዙ ጊዜ ዝቼ - በወሬ እንደምቀር
‹ዘንድሮስ…!› እንዳልኩኝ - አምና ይሄን ጊዜ - ሰምተኸኝ ነበረ
ምንም ሳልለወጥ - ‹ዘንድሮዬ› አልፎ - በአዲስ ተቀየረ
ፍሬ የማይወጣኝ - እኔን በመኮትኮት - እጆችህ ደከሙ
እኔ ግን አለሁኝ - ዛሬም አልበቃኝም - በኃጢአት መታመሙ
የቃልህን ውኃ - በድንጋይ ልጅህ ላይ - ሳትታክት ስታፈስስ -
ዘመን ተቆጠረ
ወደ ልቤ ሳይሰርግ - ሕይወቴን ሳይለውጥ - እንዲያው ፈስሶ ቀረ
ቃልህን ጠግቤ - እያገሳሁት ነው - ሌሎች እስኪሰሙ
በቃልህ መኖር ግን - አልያዝህ አለኝ - ከበደኝ ቀለሙ
ብዙ ጥቅስ አገኘሁ - ከቅዱስ መጽሐፍህ - ገልጬ አይቼ
ከራሴ ላይ ብቻ - አንድ ጥቅስ አጣሁኝ - በበደል ተኝቼ
ውጤቴ ደካማ - ትምህርት የማይሠርጸኝ - ተማሪ ብሆንም
ይህችን ዓመት ተወኝ - ደግሞ ትንሽ ልማር - ታገሠኝ አሁንም!
እባክህ አልቆረጥ - በቅዱስ መሬትህ - ልቆይ ፍቀድልኝ
ያፈሩት ቅዱሳን - የፍሬያቸው ሽታ - መዓዛ እንዲደርሰኝ
የተሸከምከኝ ሆይ - ዛሬም ተሸከመኝ - አትሰልቸኝ አደራ
ማን ይታገሠኛል - ጠላት እየሆንኩት - አይሠሩ ስሠራ!
አታውጣኝ ከቤትህ - ብዙ ቦታ አልይዝም - ፍሬ ስለሌለኝ
ስፍራ የማያሻኝ - ቤት የማላጣብብ - ፍሬ አልባ በለስ ነኝ!
ቦታስ የሚይዙት - ባለ ምግባሮቹ - ቅዱሳንህ ናቸው
ልክ እንደ ዘንባባ - የተንዠረገገ - ተጋድሎ ጽድቃቸው!
ከሊባኖስ ዝግባ - እጅጉን የበዛ - ገድል ትሩፋታቸው!
እኔ አይደለሁም - ቦታስ የምትይዘው - የአንተው እናት ናት
ሥሮቿ በምድር - ጫፎቿ በሰማይ - ሲደርሱ ያየናት
ይሀችን ዓመት ተወኝ - ከሥርዋ እሆናለሁ - ባፈራ ምናልባት!..
ይህችን ዓመት ተወኝ - እባክህ አምላኬ - አንድ ዓመት ምንህ ናት
ሺህ ዓመት አንድ ቀን - አይደለም ወይ ለአንተ - ዓመት ኢምንት ናት!
ይሄ ዓመት አልፎ - ዳግም ‹ዓመት ሥጠኝ› - እስከምልህ ድረስ
እባክህን ጌታ - ይህችን ዓመት ተወኝ - የወጉን እንዳደርስ!
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
አዘጋጁን ዲ/ሄኖክ ኃይሌን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ርዕስ እንመለሳለን፡፡


No comments:

Post a Comment