Saturday, August 18, 2018

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ሃያ ስምንት

ከክፍል ሃያ ሰባት የቀጠለ
የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤ ክፍል አራት
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ክፍሎች (ከ25-27) በስምምነቱ መግለጫ በተራ ቁ.2 "ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት" በሚለው ርዕስ ውስጥ የተወሰኑ ሃሳቦችን ተመልክተናል፡፡በዚህ ክፍል ደግሞ ፤ቃለ ውግዘትን በተመለከተ እንቀጥላለን፡፡
መልካም ንባብ!

ከመግለጫው ተራ  5. ተወሰደ
"ስለ ቃለ ውግዘት፤"
 "በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሁለቱም ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት እንደ ተላለፈ ይታወቃል። ስለሆነም ከዚህ ስምምነት በኋላ ቃለ ውግዘቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ የሰላም ልዑካኑ በአንድ ድምፅ ወስኖአል።" ይላል የሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ ሰምምነት፡፡
       ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ውግዘትና(ግዝት) ስለሚባሉት ቃላት ጥቂት ግንዛቤ እንጨብጥ፡፡"ውግዘት" ማለት አንዱ ሰው (ቡድን) የሌላውን ሰው(ቡድን) ሃሳቡንም ይሁን ሥራውን ለመቃወም የሚጠቀምበት ቃል ሲሆን፤ እንደ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ እምነትና ሥርዓት፤ደግሞ "ግዝት" ማለት፤አንድ ክርስቲያን ከማህበረ ምእመናን አንድነትና አጠቃላይ ከምሥጢራተ ቤ/ክ እንዳይሳትፍ መለየት ማለት ነው፡፡ሆኖም የትርጉሙ ልዩነቱ የጎላ ስላልሆነ ግዝቱን ውግዘት በማለት የሚገለጽበትም ጊዜ እንዳለ መዘንጋት የለብንም፡፡እንግዲህ ግዝት ማለት ይህ ከሆነ፤ አንድ ክርስቲያን ላይ ይህ የግዝት ሰይፍ የሚመዘዝበት ዋነኛው ምክንያት በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸችውን የቅ/ቤ/ክ እምነትና ሥርዓት የሚያፋልስ ትምህርት በአፍም ሆነ በመጽሐፍ ሲያስተምር ከተገኘ፤ እንዲሁም የከፋ የምግባር ህጸጽ ከተገኘበት ነው፡፡ አፈጸጸሙም አስቀድሞ በሊቃውንት ተደጋግሞ ይመከራል አልመለስ ብሎ በጥፋቱ ከቀጠለ፤በስህተት ትምህርቱና በመጥፎ ምግባሩ ሌሎችን እንዳይበክል ከቤ/ክ አንድነት ይለያል (ይወገዛል)፡፡ይህንንም ትምህርት ያስተማረው ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡(ማቴ.18፥15-18 ይመልከቱ)
       ይህንን የጌታችንን ትምህርት መነሻ ማድረግ ቅዱሳን ሐዋርያትና በእነሱ እግር የተተኩት በተለያዩ ዘመናት የተነሱ ሊቃውንት  የቤ/ክ እምነትና ሥርዓት ተጠብቆ እንዲኖር የሚያደርግ ቀኖና ሠርተዋል፡፡ከነዚህ ሥርዓቶች አንዱ ከላይ የተመከለትነው ተመክረው አልመለስ ያሉ መናፍቃንንና ምግባረ ብልሹዎችን ከቤ/ክ አንድነት መለየት(መገዘት) ነው፡፡ማንኛውንም ምሥጢራተ ቤ/ክ የሚፈጸሙትና የምእመናንን ኃጢአት ማሰርና መፍታት የሚችሉት ካህናት ብቻ እንደሆኑ ሁሉ፤አንድን ክርስቲያን መገዘት የሚችሉት ካህናት ብቻ ናቸው፡፡ተወጋዡ ምእመን ከሆነ ከማሕበረ ምእመናን እንዲለይ ሲደረግ ካህን ከሆነ ሥልጣነ ክህነቱም ጭምር ተሽሮ ከቤ/ክ እንዲለይ ይደረጋል፡፡የግዝቱ ዋና ዓላማ የተሳሳተው ሰው ከቤ/ክ አንድነትና ከምሥጢራተ ቤ/ክ ሲለይ ከበረከቱ በመለየቱ ወደ ልቡ ተመልሶ እራሱን እንዲመረምርና እንዲታረም እንጂ እስከ መጨረሻ እንዲጠፋ ባለመሆኑ፤ በዚህ ዓይነት ከቤ/ክ የተለየ ሰው በሰራው ስህተት ከልቡ ተጸጽቶ ከተመለሰ አስፈላጊው ቀኖና ተሰጥቶት ወደ ቤ/ክ አንድነት እንዲመለስ ይደረጋል፡፡እስከ መጨረሻው በጥፋቱ ከቀጠለ ካህኑ በምድር ያሰረው በሰማይም የታሰረ ስለሆነ(ማቴ.16፥19)ያለ ምንም ጥርጥር ወደ ሲኦል ብሎም ወደ ገሃነም ይወርዳል፡፡
        በዚሁ መሠረት በሁለቱም ሲኒዶሶች መካከል የተፈጠረው የመለያየት ችግር ስንመለከት ለውግዘት(ለግዝት) የሚያበቃ ነበር ወይስ አይደለም? ደግሞስ ውግዘት የሚፈታው አሁን ሰሞኑን ባየነው ሁኔታ ነወይ? ብሎ መጠየቁ አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜ ያለፈበት ጉዳይ ስለሆነ በዝምታ ማለፉ ይመረጣል፡፡ያም ሆነ ይህ በሁለቱም በኩል የተላለፈው ውግዘት ሳይነሳ ወደ አንድነት ለመምጣት እንደማይቻል ስለታመነበት በቅድሚያ ውግዘቱ እንዲፈታ መደረጉ ለትውልዱ አንድ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ይታያል፡፡ባለፈው ክፍል 26 ጽሁፋችን እንደገለጥነው የሲኖዶሱን ስምምነት ለመፈጸም ከተሄደበት ጊዜና ሁኔታ አንጻር ሲታይ፤በቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው፤ እንደምንም አደፋፍሮ በሁለት የተከፈለውን ሲኖዶስ ወደ አንድ ማምጣቱ ላይ ስለሆነ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች እንዳልተገባ ይታወቃል፡፡"ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም" እንደሚባለው ፈረሱ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ) አሜሪካ ድረስ ሄደው ስደተኛውን ሲኖዶስ አንከብክበው አምጥተው ተገቢው ቦታ አድርሰዋል፡፡እንግዲህ እንዳለፈው ጊዜ በመንግሥት ወይም በሌላ አካል ማመካኘት (የቀድሞም ምክንያት በቂ ባይሆንም) ስለማይቻል በፍቅርና በአንድነት ሆኖ በመመካከር፤ ለዘመናት የተፈጠሩትን የሃይማኖትና የሥርዓት መዛባቶች ማስተካከል የቅዱሳን አባቶች ድርሻ ነው፡፡
       ወደ ተነሳንበት ርዕስ እንመለስና፤ ለውግዘት(ለግዝት) ይህንን ያህል ክብደት የሚሰጠው መሆኑን ስንመለከት፤የቀድሞው ሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ የነበሩት ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ በ5ኛውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ፓትርያርክ በአቡነ ጳውሎስና የእሳቸውን ዓላማ አስፈጻሚ በሆኑት በሌሎቹም ጳጳሳት ላይ ያሳለፉትን የግዝት ቃል አባቶቻችን እንዴት ያዩታል ብለን መጠየቅ ግድ ይለናል፡፡ የክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩን ማንነትና ከልጅነት እስከ እለተ ሞት፤ ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ያበረከቱትን አገልግሎት፤ ከሃያ ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ካልሆኑ በስተቀር የቤ/ክ ልጅ ሆኖ የማያውቃቸው አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው፤ ቤ/ክ ካፈራቻቸው ታላላቅ ሊቃውንት መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ነገር ግን ከሌሎቹ ሊቃውንት ለየት የሚሉባቸውና በእርሳቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ እንድናደነቅ የሚያደርጉን ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡
       ይህንን ታሪካቸውን በዓይናችን ካየነውና በጆሯችን ከሰማነው በተጨማሪ፤ ወ/ሮ ሥምረት አያሌው የተባሉት የአለቃ አያሌው የመጀመሪያ ልጅ "አባቴና እምነቱ" በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም ካሳተሙት መጽሐፍም ያገኘነው ነው፡፡ ወ/ሮ ሥምረት አያሌው አባታቸው ለቤ/ክ ላበረከቱ መጠነ ሰፊ አገልግሎት የቅረብ ረዳት ከሆኑት ልጆቻቸው የመጀመሪየያዋ እንደመሆናቸው የሕይወት ታሪካቸውን ከስር ከስሩ እየመዘገቡ፤ በጽሁፍ፣ በድምጽ፣ በምስል የተቀረጹትን ስራዎቻቸውን ሰብስበው በመያዛቸው ከላይ የተጠቀሰውን መጽሐፍ ለማዘጋጀት አልተቸገሩም፡፡የመጽሐፉንም አዘገጃጃት ስንመለከት፤ ወ/ሮ ሥምረት አባታቸው ገና ሲወለዱ ጀምሮ  አብረው የነበሩ እስኪመስል ድረስ የተጠቀሙበት የአጻጻፍ ዘይቤ የሥነ ጽሁፍ ስጦታውን ከአባታቸው ትንሽ ወርሰዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ስለሆነም ይህ መጽሐፍ "የአለቃ አያሌው ታምሩ የሕይወት ታሪክ" ይባል እንጂ ወላጅ አባታቸው እድሜያቸውን በሙሉ የደከሙበትን የቤ/ክ ጉዳይና ስለ ውግዘቱም ሆነ ስለሌሎችም አጠያያቂ ጉዳዮች ጠቃሚ መረጃ የያዘ በመሆኑ ደራሲዋ ወ/ሮ ሥምረት በዚህ አገልግሎታቸው ለሌሎችም የጀግኖችና የሊቃውንት ልጆች በተለይም በሴትነታቸው ባሳዩት አርአያነታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
       ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና፤ ከላይ እንደገለጽነው ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ከሌሎች የቤ/ክ ሊቃውንት ከሚለዩባቸው ብዙ ሁኔታዎች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል፤
ሳይፈሩ ሳያፍሩ እውነትን በአደባባይ መናገር፤ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ፤  ልዑል እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ "ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉዋት" ባለው ትእዛዝ መሠረት በህጋዊ ጋብቻ ተወስነው  አስራ አራት ልጆች አባት ቢሆኑም፤ ባለቤታቸውም ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚጠብቁት የእሳቸውን ደመወዝ ብቻ ቢሆንም፤ እውነቱን ብናገር፤ ከሥራ ብባረር ወይንም ብታሰር፤ ከዚህም በላይ መከራ ቢደርስብኝ ልጆቼና ባለቤቴ ምን ይበላሉ ብለው ለሥጋቸው አድልተው እውነቱን ከመናገር ወደ ኋላ  ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ንጉሥም ይሁን ጳጳስ ስህተት አይተው በይሉኝታ ወይንም በፍርሃት የሚያልፉት ነገር የለም፡፡ከመናገርም አልፎ ከሃይማኖት መስመር የወጡትን ፓትርያርኩንና መሰሎቻቸውን ሁሉ በተሰጣቸው ሥልጣን እስከማውገዝ ደርሰዋል፡፡
ዓይነ ስውር ልበ ብርሃን፤ ክቡር አባታችን በፈንጣጣ በሽታ ምክንያት ሥጋዊውን የዓይናቸውን ብርሃን ያጡት ገና የሦስት ዓመት ተኩል ህጻን እያሉ ሲሆን፤ በጠፋው ዓይናቸው ፋንታ ልባቸውን ብሩህ ስላደረገላቸው ተዘርዝሮ የማያልቀውን ከሊቅነት ደረጃ ያደረሳቸውን መንፈሳዊ እውቀት ያካበቱት በጆሯቸው በመስማት ብቻ ነው፡፡
ደራሲነትና ተርጓሚነት፤ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው በሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢነት ላይ እያሉ ከተረጎሙዋቸውና ካዘጋጇቸው፤እንደ መጸሐፈ ግጻዌ፣ የግዕዝና የአማርኛ አዲስ ኪዳን፣ ሃይማኖተ አበው፣ የተለያዩ ገድላትና ድርሳናት፤ ከመሳሰሉት መጻሕፍት ሌላ በግላቸው የአስር መጻሕፍት ደራሲ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ታዲያ መጽሐፎቹ ሲዘጋጁ እንደ ሌላው ደራሲ መጀመሪያ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ከዚያ ታርሞ ወዘተ፤ ሳይሆን አሳቸው ይናገራሉ ጸሐፊው ይጽፋል፤ ከዚያ ሥርዓተ ነጥቡን ብቻ አስተካክሎ ወደ ማተሚያ ቤት መላክ ነው፡፡
በተለይ ገና በወጣትነት እድሜያቸው ያዘጋጁትና ለካቶሊኩ እምነት መልስ የሰጡበት " መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና "  የተባለውን መጽሐፍ ሲያዘጋጁ፤ብዙውን ምላሽ ከቅዱስ ጳውሎስና ከቅዱስ ቄርሎስ እየተነገራቸው እንደጻፉት እራሳቸው መስክረዋል፡፡ስለዚህ መጻሕፍቶቻቸው ለምእመናን እውነተኛው ትምህርት የሚያሰጨብጡ ሲሆኑ፤ቤተ ክርስቲያንን እተቻለሁ እቃወማለሁ ለሚሉ እንደ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት ላሉ አጉራ ዘልሎችና እንዲሁም ከውስጥም ያሉትን ተኩላዎች ምላሽ አሳጥተው ዝም ጸጥ የሚያሰኙ ናቸው፡፡
የሀገር ፍቅር ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁሉ ተለይታ በህገ ልቡና፣በህገ ኦሪት፣በህገ ወንጌል እየተመራች እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረችና ወደፊትም እሰከ ምጽአት ድረስ "ወልድ ዋሕድ" በሚለው እምነት ጸንታ የምትኖር እንደሆነች፤በቅዱሳት መጻሕፍት በብዙ ቦታ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡እንዲሁም ኢትዮጵያ፤ እግዚአብሔር ብዙ ምስጢር ያስቀመጠባት ቅድስት ሀገር መሆንዋን ከሁሉ ቀድመው የተረዱት አባታችን "ኢትዮጵያ ሆይ እኔ ክብርሽን ለማንም አልሰጥም" እያሉ ሲሟገቱላት፤ በዚህ በ40 ዓመት ውስጥ የተፈጠረ  ማን ዘራሹ ትውልድ ደግሞ ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት እድሜ ያላት ሀገር እንደሆነች ይናገር ነበር፡፡ምንም እንኳን አንድን ነገር ፍጻሜውን ሳያዩ አስቀድሞ ማመስገን ተገቢ ባይሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሀገራችን አልፎ በዓለም ዙሪያም፤; ከማንኛውም ሀገር በፊት የነበረች ጥንታዊት፣ የሥልጣኔና የእውቀት ምንጭ፣ የነጻና የኩሩ ሕዝቦች እናት ስለመሆኗ፤ እንዲሁም ከኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ስለመሆናቸውና አንዳቸውን ከአንዳቸው መለየት እንደማይቻል በአደባባይ ከፍ ብሎ ሲነገር ስንሰማ አባታችን የሚናፍቁት "የምሕረቱ ቀን ሊደርስ ይሆን እንዴ!"ብለን አንድንጓጓም አድርጎናል፡፡
እግዚአብሔርን መፍራትና ሰውን ማክበር፤ አለቃ አያሌው እውነቱን በባለሥልጣን ፊትም ሆነ በየአደባባዩ በድፍረት ሲናገሩ የሚሰማቸው ሁሉ እሳቸውን ኃይለኛና ቁጡ እንደሆኑ አድርጎ ይገምታል፡፡ቀረብ ብሎ ላያቸው ሰው ግን ሰው የተባለ ሁሉ እንዲድንና እንዲጠቀም የሚፈልጉ፣ የሚያዝኑ፣ የሚያጽናኑ ባላቸው ነገር ለመርዳት ወደ ኋላ የማይሉ ናቸው፡፡
ለተጠየቁት ሁሉ ፈጣን መልስ መስጠት፤ በግልም ይሁን በጋራ ጉዳይ፣ በሃይማኖትም ይሁን በአገር ጉዳይ ፣ከዚያም ወጣ ያለ ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሆን ለተጠየቁት ነገር ሁሉ አጥጋቢ መልስ ሰጥተው ይሸኛሉ እንጂ፤ ቆይ መጽሐፍ አገላብጬ፤ ከሌሎች ጋር ተማክሬ፤ ብሎ ቀጠሮ መስጠት የለም፡፡በተለይም ብዙ ሊቃውንት እርስ በርስ ተከራክረው ለመተማመን ሲቸገሩ ተያይዘው ወደ አለቃ ቤት ነው፡፡ለሁሉም ተገቢውን መልስ ሰጥተው ከተጠየቁት በላይ አስረድተው መርቀው ይሸኛሉ፡፡
ሩጫቸውን ሲጨርሱ የተናገሩት የአደራ ቃል፤ በሕብረተሰቡ የተለመደው አንድ ሰው ለሞት የሚያደርስ ሕመም ሲጸናበት በተለይም የልጆች አባትና እናት ከሆኑ  የሚጨነቁትና የሚናዘዙት  ለልጆቻቸውና በምድር ላይ ጥለውት ስለሚሔዱት ነገር ብቻ ነው፡፡እሳቸው ግን ዐረፍተ ሥጋቸው በተቃረቡባቸው ሰዓታት ውስጥ ሳይቀር ድክም ባለ ድምጽ " እብካችሁ ስለ ቤተ ክርስቲያን ተናገሩ፣ ጸልዩ፣ ዝም አትበሉ" እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡….ወዘተ፡፡
       እንግዲህ ሰው ያየውንና የተረዳውን ያህል መመስከር ስለሚገባና ከዚህ ቀጥለን የምናቀርበውን የግዘት ቃል ያስተላለፉት ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ማናቸው ለሚለው ጥያቄ እንደ መግቢያ እንዲሆን ነው እንጂ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጹ ሰው ሆነው አይደለም፡፡"መንፈሳዊ ሰው ሁሉን ይመረምራል እራሱ ግን በማንም አይመረመርም" እንደተባለው፡፡
       የተከበራችሁ አንባብያን! የተነሳንበት ርዕሳችን "ስለ ቃለ ውግዘት፤" የሚለው ስለሆነ፤ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው  ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበትን አስራ አንደኛ ዓመት መታሰቢያቸውን፤ (ነሐሴ 14 2010 ዓ.ም) ምክንያት በማድረግ፤ሰኔ 27 ቀን 1988 ዓ.ም ያስተላለፉትን የግዝት(የውግዘት) ቃል ቀጥሎ አቅርበነዋል፡፡

“ይህንንም እንደሚከተለው እገልጣለሁ፡፡”(አለቃ አያሌው ታምሩ)
    1)  በቤተክርስቲያን የደረሱ ልዩ ልዩ ችግሮ ሁሉ በሲኖዶስ ተመክሮባቸው እንዲወገና እርምጃቸውም እንዲገታ በ1987 ዓ.ም   ጥቅምትና ህዳር ወር ለሲኖዶሱ ማመልከቻ ስጽፍ መልእክቴ በጌታዬ በአምላኬ ትእዛዝ የተደረገ መሆኑን ገለጨ በአፈጻጸሙ ቸልተኝነት እንዳይታይበት ሲኖዶሱን በሾመ በመንፈስ ቅዱስ ዳኝነት ተማጽኜ አቤቱታዬ የእኔ ብቻ ሳይሆን በአጸደ ስጋና በአጸደ ነፍስ ያሉ የኦርቶዶክሳውያን አበውና ምእመናን አቤቱታ መሆኑን ገልጩ ነበር ያቀረብኩት፡፡ ነገር ግን የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ አባ ገሪማና ፓትሪያሪኩ ሀሳባቸው እስከ አሁን በቤተ ክርስቲያን የኖረውን የመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሽረው የራሳቸውን ጣዖታዊ መሪነት ለመተካት ኖሮ በጥቅምት 1988 ዓ.ም አጠቃላይ ጉባዔ ላይ ያቀረብኩትን አቤቱታ ጭምር ሳይቀበሉ ከመቅረታቸውም በላይ የመንፈስ ቅዱስን ዳኝነት የሲኖዶሱን ሥልጣን ለግል አድመኞቻቸው ኮሚቴ አሳልፈው በመስጠትና በነሱ ውሳኔ ተደግፈው የኑፋቄ መጽሐፍ ማውጣታቸውና መበተናቸው አንሶ ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባዔ አፍርሰዋል፡፡
     2) ይህ በዚህ እንዳለ ሲኖዶሱ ተሰብስቦ ጉዳዩን እንዲያይ በግል ማመልከቻ በነፃ ፕሬሱ በኩልም ተቃውሞዬን በማሰማት ላይ እያለሁ ሚያዚያ 18 ቀን 1988 ዓ.ም ቅሬታ አስወጋጅ በሚሉት የግል ኮሚቴያቸው ድጋፍ እኔን ካባረሩ በኋላ ከሚያዚያ 22 እስከ ግንቦት 6 ባደረጉት በአፈና የሲኖዶስ ስሰባ ሕግ አስወጥተው በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ ራሳቸው ፓትሪያሪኩ ሲኖዶሱ ወንጌልን ለሚሰብክበት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለሚያስተምርበት ጉዞ አመራር ሰጪ /ጣኦት/ ወደ መሆን አድገዋል በቤተ ክርስቲያን ስም ተሰይመው እግዚአብሔርንና ቤተክርስቲያንን ሊያገለግሉ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ሳይቀር ለቤተክርስቲያን ተጠሪ መሆናቸው ቀርቶ ለፓትሪያሪኩ ተጠሪዎች እንዲሆኑ ሲያደርጉ ሚያዚያ 30 ቀን ተፈርሞ ጸድቋል፡፡የተባለውና በጽ/ቤቱ አማካኝነት ለሚመለከተው ሁሉ እንዲተላለፍ በቃለ ጉባዔ ትእዛዝ የተሰጠበት ሕገ ቤተክርስቲያን እስከ አሁን ቤ/ክ ስትሰራባቸው የኖሩት ሕጎችና ደንቦች ሁሉ በዚህ ሕግ ተሻሽለው ከስፍራቸው ሲወገዱ ብጹእ አቡነ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአመራር ሰጪነት ቦታ ሲይዙ በቤተ ክርስቲን ላይ የአምልኮ ጣኦት አዋጅ አውጀውባታል ፓትሪያሪኩ በሾማአቸው በእግዚአብሔርና በቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጸሙት ተግባር ታላቅ በደል ፈጽዋል፡፤ ከራሳቸው ጋር ቃላቸውን ለማጽቅ ምኞታቸውን ለሟሟላት በሕጉ ላይ ፈርመዋል ተብሎ ስማቸው የተመዘገበላቸው 34ቱ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት እንደተባለው አድርገውት ከሆነ ለፈጸሙት በደል ተባባሪዎች ናቸው፡፡
ይህም እጅግ የሚያሳዝን ነው የሚገርመው ደግሞ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 14 “ፓትሪያሪኩ” የተዋህዶ እምነትን ሕግጋት ቤተክርስቲያንን የማይጠብቅ ማእረጉን የሚያጉድፍ ሆኖ በመገኘቱ በተጨባጭ ማስረጃ ሲረጋገጥ በምልዓተ ጉባዔ ያለአንዳች የሃሳብ ልዩነት በቅዱስ ሲኖዶስ ከተጠና በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት ከማዕረጉ ይወርዳል” የሚል ቃል አስፍሮ ሲኖዶሱን በአፈና ልዩ ስልጣን ተጠቅሞና እንደሌለ አድርገው ካሳዩ በኋላ የኑፋቄ መጻህፍት በማሳተም የተዋህዶ ሃይማኖትን አፍልሰዋል ሕገ ቤተክርስቲንን ሳይጠብቁ ቤተክርስቲያን ከምታወግዛቸው ጋር የጸሎት ቅዳሴና የማዕድ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ከምታወግዘው ፓፓ ቡራኬ ተቀብለዋል እያልን እየተቃወምን ለተቃውሟችንንም ተጨባጭ ማስረጃ እያቀረብን እራሳቸውም ይህንን ሳይቃወሙ ይህ እንዳይቀጥል በስልጣናቸው ተጠቅመው ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባዔ ሲያፈርሱ ጉዳዩን አይቶ ውሳኔ በመስጠት ፈንታ እንደገና በሕግ በመንፈስ ቅዱስ ሥፍራ ተተክተው ለሲኖዶሱ ስልጣንና ተግባር አመራር ሰጪ ይሆናሉ፡፡ የሲኖዶሱ አባሎች ሁሉ ለፓትሪያሪኩ ተጠሪ ይሆናሉ ሲል የወጣው አዋጅ አፈፃፀም ነው፡፡
ይህ ሕገ ቤተክርስቲያን ተብሎ የታወጀው ህግ…“እስመ ሜጥዋ ለአመፃ ላእሌከ…”/አመጽን ወዳንተ መለሳት /ተብሎ እንደተፃፈ ቤተክርስቲያንን መካነ ጣዖት ምእመናንን መምለኪያ ጣዖት የሚያሰኝ ስለሆነ በሙሉ ድምጽ እንድትቃወሙት በእግዚአብሔርና በቤተ ክረስቲያን ስም እጠይቃለሁ፡
     3)  ከአሁን ጀምሮ ማለት ይህ ቃል በነፃው ፕሬስ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃልና እጅ በሲኖዶሱ ጸሐፊ በአቡነ ገሪማ ቃልና እጅ ይህን የተፃፈውን ሕግ የቤተክርስቲን ሕግ ብለው አጽድቀው በተባባሪነት አሳልፈዋል የተበለ ጳጳሳትና ሁሉ እውነት ሆኖ ከተገኘ የነሱ ተባባሪዎች ናቸውና በነሱ ቃልና እጅ ቡራኬ እንዳትቀበሉ እንዳትዘዙ ስማቸውን በጸሎት ቅዳሴ የሚጠሩ አለቆች ቀሳስት ካህናት ካሉም አምልኮ ጣኦት አራማጅ ናቸውና ተጠንቀቁባቸው ምክር ስጡአቸው እምቢ ካሉም ተለዩዋቸው፡፡
እንዲሁም ሀምሌ 5 ወይም 6 ቀን ይከበራል ተብሎ ሽርጉድ የሚባልለት በዓለ ሲመት የአሮን የወርቅ ጥጃ መታሰቢያ ሆኖ በቤተክረስቲያን ሊከበር የማገባው ስለሆነ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የሲኖዶሱ አባላት በአስቸኳይ ተሰብስበው ሕጉን ካልሻሩና በጣኦትነት የተሰየሙትን አቡነ ጳውሎስን ከስልጣናቸው ካላነሱ ይህንን እንዳታከብሩ ለቤተክርስቲያን ደሙን ባፈሰሰ አምላክ ስም ቤተክርስቲያን በሚመራ በሚጠብቅ በመፈስ ቅዱስ ስም ጥያቄዬን አስተላልፋለሁ፡፡
ምናልባት የሕጉን ጹሁፍ አንብቦ መረዳት የተሳነው ግን በልዩ ልዩ ደጋፊዎቻቸው ተጭበርብሮ በቸልታ የሚመለከተው ከዚያም አልፎ በስልጣናቸው እየተመኩ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ጆሮአችንን አንሰጥም ብለው ይህን በደል ያደረሱትን ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስን በ3 የሹመት ስም የሚንቀባረሩትን አባ ገሪማን ለነሱ ድጋፍ የሚሰጡትንም ሁሉ ጌታዬ አምላኬ በምድር ያሰራችሁትን በሰማይ የታሰረ ይሆናል ሲል በሰጠው ቃል በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስልጣን በጥሮስ ፣ በጳውሎስ፣ በማርቆስ፣በቄሎስ፣ በባስልዮስ፣ በቴዎፍሎስ፣ በተክለ ሐይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ቃ፤ ሃጥእ ደካማም በምሆን በእኔም በቀሲስ  ወልደ ጊዮርጊስ ቃል አወግዛለሁ፡፡
       ይህን ሕግ የተቀበሉ ከሥራ ላይ ያዋሉ ሁሉ እንደ አርዮስ እንደ መቅዶንዩስ እንደ ንስጥሮስ እንደ ፍላብያኖስ እንደ ኬልቄዶን ጉባዔና ተከታዮቹ እሱራን ውጉዛን ይሁኑ በማይፈታው በእግዚአብሔር ሥልጣን አስሬአለሁ፡፡
                       ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን አሜን፡፡
ማስጠንቀቂያ
አምላኬ ሂድ ተናገር ያለኝን ትዕዛዝ ለናንተ አድርሻለሁ ሩጫን ጨርሻለሁ ከእንግዲህ ተጠያቂነቱ የእናንተ የምእመናንና ታሪክ ተጠያቂ ያደረገው የመንግስት ነው ለዚህም ምስክሬ እራሱ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላዕክት ሰማይና ምድር ናቸው፡፡››
                                                                             አለቃ አያሌው ታምሩ
                                                                             ዘዲማ ጊዮርጊስ

ለዛሬው፤ የክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ሥርዓተ ቀብር በተፈጸመበት ዕለት ወ/ሮ ሥምረት አያሌው ያቀረቡትን ግጥም አስነብበናችሁ እንሰናበታችሁ፡፡
አያሌው ታምሩ ዐምደ ሃይማኖቴ፤
አጥንት ሥጋ ደም ማተቤ ኩራቴ፤
በሥጋም በነፍስም ወለደኝ ሁለቴ፡፡
ነሐሴ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም
በቀጣዩ ክፍል አለቃ አያሌው ይህንን ውግዘት ለማስተላለፍ ያበቃቸውን ዝርዝር ምክንያትና ማጠቃለያውን ይዘን እንቀርባለን፡፡
እስከዚያው በደህና ቆዩን፡፡



No comments:

Post a Comment