Monday, August 20, 2018

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ሃያ ዘጠኝ

 ከክፍል ሃያ ስምንት የቀጠለ
የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤ ክፍል አምስት
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
       ባለፉው ክፍል 28 ጸሁፋችን ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ያስተላለፉትን ውግዘት አስነብበናችሁ፤በቀጣይ ስለ ውግዘቱ ዝርዝር ሁኔታዎች ይዘን እንቀርባለን ብለን በገባነው ቃል መሠረት ቀጣዩን ክፍል እነሆ፡፡
       እንግዲህ አባታችን አለቃ አያሌው ግዝቱን ካስተላለፉም በኋላ ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዚህ መከረኛ ዓለም እስከተለዩበት እስከ ነሐሴ 14 ቀን 1999 ዓ.ም ድረስ፤በመኖሪያ ቤታቸው የቁም እስር ላይ ሆነው በየጊዜው የሚፈጠሩትን ስህተቶች በመቃወም፤ ከተለያዩ አቅጣጫ እቤታቸው ድረስ የሚሄዱትን ምእመናን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በማስተማር፣ ከተለያዩ የግል ጋዜጠኞችና እንደ አሜሪካና ጀርመን በመሳሰሉ ሬዲዮ ጣቢያዎች የሚቀርብላቸውን ጥያቄ በመመለስና እንደሁም ከአራት በላይ መጻሕፍት በማዘጋጀት ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ሩጫቸውን ጨርሰዋል፡፡
የተከበራችሁ የተዋሕዶ ልጆች፤
ከዚህ በመቀጠል አለቃ አያሌው ባስተላለፉት የግዝት ቃል ውሰጥ፤ ግዝት ለማስተላለፍ የተገደዱበትን ምክንያትና የችግሮቹን  እውነትነት የሚያረጋግጡልንን ጥቂት ማስረጃዎች እንመለከታለን፡፡

ማስረጃ አንድ፤ የኑፋቄ መጽሐፍ አሳትመዋል ለተባለው፡-
          በ1988 ዓ.ም በፓትርያርኩ በአቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ፤ በሌሎች ጳጳሳትና የቤ/ክ መምህራን አዘጋጅነት  "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት አምልኮትና የውጭ ግንኙነት" የሚለው መጽሐፍ በሁለት ቋንቋ ማለት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ታትሞ  ለምእመናን ተሸጧል፡፡መጽሐፉ ከቃላት አጠቃቀሙ ጀምሮ ኦርቶዶክሳዊ ለዛ የሌለው ከመሆኑ ሌላ የሚከተሉትን የክህደት ትምህርቶች የያዘ ነው፤
ሀ/ “ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም” በሚለው ርዕስ ስር ገጽ 37 “እመቤታችን በዘመኗ ከነበሩት ደናግል ተለይታ እግዚአብሔር ከፈጠራት ጀምሮ በሃሳብ ፣ በመናገር፣ በመስራት ፣ ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈባት ድንግል ናት
ለ/ “የአማላጅነት ቃል ኪዳን” በሚል ርእስ ስር ገጽ 39 “ቤተ ክርስቲያን ስለ እመቤታችን አማላጅነት እና ቃል ኪዳን የምታስተምረው ፍጹም በሆነ ሐዋርያዊ ትውፊት ነው፡፤”
    ሐ/ “mystery of the trinity” በሚል ርዕስ chapter 3 page 15 “when we say they are three in essence, in divinity, in existence and in will do not mean to say three Gods but one God.”
ማስታወሻ፤ማን ይናገር የነበረ እንደሚባለው፤ብጹዕ አቡነ ገብርኤል የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና ከመጽሐፉ አዘጋጆች አንዱ ሲሆኑ፤መጽሐፉን በተመለከተ ያቀረቡት ተቃውሞ መስከረም 22 ቀን 1990 ዓ.ም በወጣው መብሩክ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ይነበባል፤
   ለፓትርያርኩ የተጻፈ ማሳሰቢያና ተማጽኖ /ገፅ 4/
"በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ያስነቀፈ ከሁለት ዓመት በፊት በሁለት ቋንቋ የታተመው የሃይማኖትና የቀኖና መጽሐፍ በእግሊዘኛው ክፍል ገጽ 15 ‹‹ እግዚአብሔር በመለኮትና በባህርይ ሶስት ነው›› ተብሎ ተጽፎ በመውጣቱ ብዙ ውግዘትን  ያስከተለ በመሆኑ በአስቸኳይ ይታረም:: ታርሞ ከሆነ ደግሞ በቂ ማብራሪያ በሬዲዮ ፤ በቴቪዥንና  በጋዜጣ ነገር ቀደም ብሎ የታተመው መጽሐፍ ተሰብስቦ እንዲቃጠል ይደረግ"፡፡
 ማስረጃ ሁለት፤ ፓትርያርኩ የሲኖዶስን ሥልጣን የሚሽርና እራሳቸውን በመንፈስ ቅዱስ ቦታ እንዲሰየሙ  የሚያደርግ አዲስ  ሕግ አወጡ ለተባለው፤
ሚያዚያ 30 ቀን 1988 ዓ.ም ከተዘጋጀው ህገ ቤተ ክርስቲያን፤ ምዕራፍ 8 አንቀጽ 23 የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ በሚለው ርዕስ ሥር፤ "የሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና ፀሐፊ ሆኖ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ይሆናል፡፡"ይላል፡፡
እንዲሁም ምዕራፍ 16 አንቀፅ 33 "ካሁን በፊት በቅ/ሲኖዶስ ወጥተው የነበሩ ህጎች በዚህ ሕግ ተሻሽለዋል"
ማስታወሻ፤ የአጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት
የአጣሪ ኮሚሽኑ ሥራው ምንድነው ለምትሉ፤ትንሽ መግቢያ
ከአለቃ አያሌው ውግዘትና ከአቡነ ገብርኤል ተቃውሞ ጀምሮ፤ በአጠቃላይ  የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ችግር አደባባይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ችግር እንዲያጣራ ህዳር 5 ቀን 1990 . በፓትርያርኩ በአቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ የተቋቋመ ነው፡፡ፓትርያርኩ ኮሚሽኑን ያቋቋሙት በየጋዜጣው የሚሰማውን ትችት አለባብሶ ለማለፍ ይጠቅመኛል ብለው ቢሆንም፤ አጣሪ ኮሚሽኑ ግን አቅሙ የፈቀደውን ያህል አጣርቶ ውጤቱን ከነመፍትሔው በሁለት ክፍል አዘጋጅቶ አቅርቦ ነበር፡፡ሆኖም ፓትርያርኩ ኮሚሽኑ ከፍላጎታቸው ውጪ ስለሄደባቸው የኮሚሽኑ የድካም ውጤት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡ኮሚሽኑ ጥናት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ አለቃ አያሌው የተቃወሙት አዲሱ ህገ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ከሌሎች ቀድሞ ከነበሩት ህጎች ጋር እንዲህ ብሎ ያነጻጽረዋል፡፡
የአጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት ክፍል አንድ (ሐምሌ 10/1990 ዓ.ም)
4.1.1.1.3 ከዚህ አንጻር "ተጠሪነቱ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ይሆናል›› የሚለው ኃይለ ቃል በአሁኑ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የተጨመረ መሆኑና የቅ/ሲኖዶስ ተግባራት በተሟላ መልኩ የሚያስተናግድበትና የሚገልፅበት ጠንካራ ጽ/ቤት ያልተደራጀበት በመሆኑ እንደቅሬታው አቀራረብ መፈፀሙን የሚያመለክት ስለሆነ ቅሬታው በአግባቡ የቀረበ መሆኑ ታምኖበታል፡፡"
ከዚህም ሌላ ኮሚሽኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ አደራጃጀትና አመራርንም እንዲህ ብሎ ተችቶታል፤
የአጣሪ ኮሚስን ሪፓርት ክፍል ሁለት (ጥቅምት 23 1991 ዓ.ም)
1.2.2 ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አደራጃጀትና አመራር የመወሰንን ስልጣን በተመለከተ፤
ገጽ 19 ‹‹… በዚሁ መሠረት ኃላፊዎች ያሳዩት የአመራር ብቃትና ውጤት በአንድ በኩል ከተጣለባቸው ኃላፊነት አኳያ በሌላ በኩል ደግሞ የመንበረ ፓትርያርክ መዋቅራዊ የስራ ዘርፎች ከሚገኙበት ድክመትና ውድቀት አንጻር በመሆኑ ከፍተኛ የአመራር ድክመት የተመዘገበበት ወቅት ነው ቢባል ተጋነነ አይሆንም፡፡››
ገጽ 21…"በመሆኑም ያለ እቅድና ፕላን መመራት ብርሃን በሌለበት ጨለማ እንደመጓዝ የሚቆጠር ሲሆን በተፈለገበት ጊዜና በተፈለገው ቦታ የማይደረስበት ለጉዳትና ለችግር የምትጋለጥበት ፤ ተልዕኮዋን በአግባቡ የማትፈፅምበት… በአጠቃላይ ከብርሀንና ከጨለማ ጉዞ በማመሳሰል ሊገለፅ የሚችል ነው ለማለት ይቻላል"፡
ገጽ 22፡- "በዚህ መሠረት አጠቃላይ ችግሩ ሲመዘን 90% የቤተክርስቲያን አስተዳደር ማህበረተሰብ በደል ደረሰብኝ የሚል ቅሬታ ያለው ወገን መሆኑን በዚህ ዙሪያ የችግሩ ተዋናዮችና የበደሉ አራማጆች 10% የማይበልጡ መሆናቸው በኮሚሽኑ ግምገማ የታመነበት ውጤት ነው፡፡"
ገጽ 23 4.2.3.2፡- "በተመሳሳይ ሁኔታ በድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ወ.ዘ.ተ የሚፈጸመው ዝውውርና ምደባ አፈጻጸሙ ይህ ነው የሚባል መመዘኛና ስርዓት የሌለው በጉቦ፤ በዝምድና፡ በአድልዎ፤በወገናዊነት፤በጥቅማጥቅም የተመሰረተ መሆኑን ኮሚሽኑ ከቀረበለት አቤቱታ መረጃና ከደረሰበት ጥናታዊ ድምዳሜ አኳያ ለመረዳት ተችሏል፡፡"
ማስታወሻ ፤ ከላይ የተቀመጠውን የኮሚሽኑን ሪፖርት ስንመለከት ከዋነኛው የሃይማኖታዊው ችግር በተጨማሪ፤ የቀደመውን ትተን የአጣሪ ኮሚሽኑ ይህንን ሪፓርት ካቀረበበት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የዘለቀው የሌብነት፣ጉቦኝነት፣ዘረኝነት፣በአጠቃላይ ብልሹ አሰራር ስንመለከት ቤተ ክርስቲያንን ከተሰለፈችበት መንፈሳዊ ጎዳና እንዳወጣት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ 
ሐ) ማስረጃ ሦስት፤ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ ከሮማው ፓፓ (ካቶሊክ) ጋር ሕብረት መሥርተዋል ለተባለው፤
      አለቃ አያሌው ፓትርያርኩን ካወገዙበት ምክንያት አንዱ፤ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ በተሾሙ በዓመታቸው ማለትም ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው ወደ ሮም እየሄዱ ከካቶሊኩ መሪ (ፓፓው) ጋር የጸሎት፣ የቅዳሴ፣ የመብልና የመሳሰሉት ተሳትፎ በማድረግ፤ቤተ ክርስቲያኒቱን የካቶሊክ ጥገኛ አድርገዋታል፤የሚለው ሲሆን ከዚያ ጋር አያይዘው ሐምሌ 5 1991 ዓ.ም በእለተ ሰኞ 16 ጳጳሳትን በቀይ ልብስ ሾመዋል፤በቀይ ልብስና ከእሁድ ሌላ ባሉት ቀኖች እንደፈለጉ መሾም የካቶሊክ ደንብ ስለሆነ ይህም ከካቶሊኮቹ ጋር ላደረጉት ድርድር አንዱ ማረጋገጫ ነው ፤ የሚል ነው፡፡
ማስረጃውም የሚከተለው ነው፤
ሀ) ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ 50ኛ ዓመት ቁጥር 165 የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የውጭ ግንኙነት በሚለው ርእስ ስር ገጽ 3 ተራ ቁጥር 29 “ግንቦት 20 ቀን 1985 ዓ.ም ለ18 ቀናት 5ኛው ፓትርያሪክ ብጹዕ አቡነ ጳውሎስ በጄኔቭ በቬየና በቫቲካን ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በሰፊው ተወያይተዋል፡፡ በተለይ ቫቲካን በጉብኙበት ወቅት በቫቲካን ቤተ መጽሐፍት የሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጥንታዊያን የብራና መጻህፍት ስለሚመለከት ጉዳይ ከፓፓ ዩሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር ተወያይተዋል፡፡”

ለ) ዜና ቤ/ክ ጋዜጣ ቁጥር  50ኛው ዓመት ቁጥር 165 “ከህዳር 20 እስከ ታህሳስ 5 1986 በቁስጥንጥያ አቴንስ ሁለቱ ታላላቅ መሪዎች በምስራቅ ኦርቶዶክስና በኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በኮሚቴው ደረጃ ስለተጀመረው የመቀራረብ ውይይት ጉዳይና ስለ ዓለም ሰላም በሰፊው ተወያይተዋል፡፡

ሐ) ዜና ቤ/ክ ጋዜጣ 50ኛ አመት ቁ 165 ተራ ቁጥር 31 “ከጳጉሜ 5/1986 እስከ መስከረም 4/1987 ዓ.ም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ በአሲሲ ኢጣሊያ “የእግዚአብሔር ወዳጆች የሰላም ምስክሮች” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ታላላቅ የሐይማኖትና የመንግስት መሪዎች በተገኑበት አለም አቀፍ የሰላም ጉባዔ ላይ ተገኝተው ሰፊ ንግግር አድርገዋል፡፡"
       እንግዲህ ከላይ ለማሳያ ያህል እንደጠቀሰነው፤ አለቃ አያሌው ስህተት ነው ብለው የተቃወሙትን ነገር በሙሉ፤ የዘመኑ ሹመኞች ሃሳብ ብቻ የሚንጸባረቅበት ጋዜጣው ደግሞ የፓትርያርኩ የአቡነ ጳውሎስ መልካም የሥራ ውጤት እንደሆነ አድርጎ ስለዘገበው ሌላ ማስረጃ ፍለጋ መሄድ ሳያስፈልግ የጋዜጣውን 50ኛ ዓመት ቁጥር 164 ፣ 50ኛ ዓመት ቁጥር 165፣ 50ኛ ዓመት ቁ.167፣ 50ኛ ዓመት ቁ 170፣50ኛ አመት ቁ.172፣ 50ኛ ዓመት ቁ.184 እና ሌሎቹንም በመመልከት እውነቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
       ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ሃይማኖትና ሥርዓት ተጣሰ፤ ቤ/ክ ከተልእኮዋ ውጪ እየሄደች ነው!..ወዘተ እያሉ በብቸኝነት ስለሚጮሁበት የቤ/ክ ጉዳይ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስና አጠቃላይ የሲኖዶሱ አባላት፤ ምን መልስ ሰጡ ? ብሎ ለሚጠይቅ ሰው መልሱን፤  ፓትርያርኩ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን፣ ጸሐፊዎችን፣ የሰ/ት/ቤት ተወካዮችንና ልዩ ልዩ የቤ/ክ ሰራተኞችን ሰብስበው፤ ብርሃኑን ጨለማ፤ጨለማውን ብርሃን በማለት ያቀረቡትን መግለጫና ተሰብሳቢዎቹም ድጋፋቸውን በጭብጨባ መግለጻቸውን ዜና ቤ/ክ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ዘግቦታል፡፡
      ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ 50ኛ ዓመት ቁ.184 “ክህነት ሳይኖር ውግዘት” በሚል ርዕስ ስር ገጽ 11 “አለቃ አያሌው ምንጊዜም እውነትን ተናግሮ አያውቅም  የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ከሮማው ፓፓ ጋር አብረው ቀደሱ ፣ የሮም ቤተ ክርስቲያን አባልነት አጸደቁ፤ወዘተ የሚለው ሁሉ በአልጋው ላይ ተንቶ የሚቃዥው ቅዥት ነው፡፡ሌላውንም እንደ ራሱ በመቁጠር ለማታለል የሚያወራውና የሚያስወራው ከመሆኑ በቀር ቅንጣት ያህል እውነት የለውም፡፡”
እውነተኛውን ፍርድ ለተመልካች ትተነዋል፡፡

ማስታወሻ የተከበራችሁ አንባብያን! ይህ ከዚህ በላይ ያቀረብነው ማስረጃ አለቃ አያሌው ግዝቱን ባስተላለፉት ወቅት የነበረውንና እስከ 1991 ዓ፣ም ድረስ ያለውን ብቻ ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ችግሩ ምን ያህል እየደገ እንደመጣ በተለይም የቤ/ክ መሪዎቹ ከካቶሊክ እምነት ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማስመልከት በቀጣዩ ክፍል የምንመለስበት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
      እንግዲህ አለቃ አያሌው ችግሩን ገና በጅምሩ ስለተረዱ ብዙ አቤቱታና ተማጽኖ ቢያቀርቡም፤ ከዚያም አልፎ በቀላሉ የማይነሳውን የውግዘት ሰይፍ ቢያነሱም፤አጥፊዎቹ በጥፋታቸው ከመቀጠል በስተቀር የመመለስ አዝማሚያ አላሳዩም፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን አለቃ አያሌው መልእክታቸውን የሚያስተላልፉት ሕዝቡ ሁሉ በሚያነበው የግል ጋዜጣ በመሆኑ ዓለሙ በሙሉ ስለ ችግሩን ሰምቶታል ማለት ይቻላል፡፡ይሁን እንጂ ይህንን ቃለ ውግዘት ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ ሲቀበሉት አልታየም፡፡የዚህንም ምክንያት ለማወቅ ለናሙና አስር ሰዎችን ብንጠይቅ አስር የተለያየ አሰተያየት እንደሚሰጡን የታወቀ ነው፡፡ሆኖም ጥቃቅኖቹን ትተን በብዙዎች ዘንድ  የሚነገሩትን ዋና ዋናዎቹን ሰንካላ ምክንያቶች በሦስት ከፍለን እናያቸዋለን፡፡
አንደኛ/ ጉዳዩን በዓላማ የሚያራምዱት ክፍሎች ውግዘቱን ላለመቀበል የሚያቀርቧቸው  ምክንያቶች፤
1/ አለቃ አያሌው ክህነት የላቸውም፤ እውነትንም ተናግረው አያውቁም፤
       አባታችን አለቃ አያሌው በሥርዓተ ጋብቻ ተወስነው፤ ከመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የቅስና ማዕረገ ክህነት እንደተቀበሉ፤ለብዙ ዓመታት በደብረ አሚን አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤ/ክ በአለቅነት እንዳገለገሉ ይታወቃል፡፡ከዚያም ደረጃ በደረጃ እያደጉ ሄደው ለቤ/ክ እምነትና ሥርዓት የመጨረሻው ተጠያቂ ወደ ሆነው የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢነት ደረጃ የደረሱት ክህነት ስላላቸው ነው፡፡ምክንያቱም ከላይ የጠቀስናቸው አገልግሎቶች የሚሰጡት ሥልጣነ ክህነት ባላቸው ሰዎች ብቻ ስለሆነ ነው፡፡እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ከላይ በተመለከትነው ጋዜጣ፤ "ክህነት ሳይኖራቸው ሊያወግዙ አይገባም" በማለታቸው ከሳቸውም አልፎ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ሲሰጥ የነበረውን የቤ/ክ አገልግሎት በዜሮ አባዝተውታል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በዚያን ጊዜ የሲኖዶሱ ጸሐፊ የነበሩት ጳጳስ ስለ ጉዳዩ ከአንድ የውጭ አገር ሬድዮ ጣቢያም ተጠይቀው ሲመልሱ አለቃ አያሌው ክህነት የላቸውም ከማለትም አልፎ "ክርስቲያን አይደሉም" ብለው ሲመልሱ ተደምጠዋል፡፡
 ማስታወሻ
       ቀደም ብለን እንደገለጽነው፤አለቃ አያሌው የፓትርያርኩንና የተባባሪዎቻቸውን የጥፋት ተልእኮ አጠንክረው በመቃወማቸው፤እሳቸውን ከሃላፊነታቸው ለማስነሳትና የጀመሩትን ጥፋት እንደልባቸው ለመፈጸም እንዲመቻቸው ፓትርያርኩ "የቅሬታ አስወጋጅና የሰላም ኮሚቴ" አቋቁመው ነበር፡፡ይህ ኮሚቴ በሚያዝያ 17 ቀን 1988 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ላይ ለቅ/ሲኖዶስ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ፤ተ.ቁ 1 ላይ "አለቃ አያሌው ታምሩን ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛውን ክብርና ሞገስ ሰጥታ በከፍተኛ ሃላፊነት…" እያለ የነበሩበትን ከፍተኛ ሃላፊነት ከጠቀሰ በኋላ፤በተ.ቁ 4 ላይ ደግሞ "ለሌሎች ካህናት የክፉ አርአያ ሆነው በመገኘታቸው ከማዕረገ ክህነታቸውና ከኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ክ ምእመናን እንዲለዩ…..እንዲደረግ…..ይላል፡፡ስለዚህ ሌላውን ሰፊ ጉዳይ ትተን የዚህን ኮሚቴ ውሳኔ ብቻ እንኳን ብንመለከት፤አለቃ አያሌው ክህነታቸው ይሻር ብለው ማቅረባቸው ክህነቱ ስላላቸው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡እንግዲህ አለቃ አያሌው ይህንን ሁሉ ከፍተኛ ሃላፊነት የሚጠይቅ ሥራ ሲያከናውኑ ኖረው አሁን ጥፋታቸውን ስላወገዙ ብቻ፤ አንዴ "ክህነት ሳኖር ውግዘት" ማለትም "ክህነት የላቸውም" በሌላ በኩል ደግሞ "ክህነታቸው ይሻር" እያሉ የሚናገሩት እርስ በርሱ የሚጣረስ አጸያፊ ንግግር ፤ፓትርያርኩና መሰሎቻቸው በከፍተኛ የጥፋት ዘመቻ ላይ እንደተሰማሩ ከሚያረጋግጥልን በስተቀር ቅንጣት ያህል እውነትነት የለውም፡፡  
2/የእምነትና የክህደት ቃላቸውን ሳይሰጡ ነወይ የሚወገዙት?
       እርግጥ ነው በቀደመው የቤ/ክ ታሪክ አልፎ አልፎ የሚነሱትን መናፍቃን አባቶቻችን በግል መክረው አስተምረው አልመለስ ካሉ በጉባዔ የእምነትና የክህደት ቃላቸውን ተጠይቀው በስህተታቸው ከጸኑ ያወግዟቸዋል፡፡ይህ እንግዲህ በእውነተኞቹ አባቶች መካከል አንዳንድ መናፍቃን ብቅ ሲሉ ነው፡፡በእኛ በአመጸኞቹ ትውልዶች ዘመን ደግሞ ደግሞ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ አጥፊዎቹ ብዙ ጥፋቱን ተቃዋሚው አንድ ብቻ ሆኖ በመገኘቱ በቀደመው ሥርዓት መሄድ አልተቻለም፡፡ይህም ባለመኖሩ አለቃ አያሌው ድንገት ተነስተው ውግዘቱን አላስተላለፉም፡፡ ሥርዓቱን ጠብቀው በመጀመሪያ ለራሳቸው ለፓትርያርኩ፣በመቀጠል ለሲኖዶስ ጽ/ቤት ከዚያም ለሁሉም ጳጳሳት በየአድራሻቸው፤በመጨረሻም ከሁሉም ሀገረ ስብከት የተሰበሰቡ ሥራ አስኪያጆች፣አስተዳዳሪዎች፣የሰበካ ጉባዔ ተመራጮች፣ የሰ/ት/ቤት ተወካዮችና ልዩ ልዩ የቤተ ክህነት ሠራተኛች በተገኙበት፤ በ1987 ዓ.ም የጥቅምቱ አጠቃላይ የሰበካ ጉባዔ ስብሰባ ላይ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ከየትኛውም አቅጣጫ መልስ ባለማግኘታቸውና ፓትርያርኩም ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ በጥፋታቸው እየገፉበት ስለሄዱ፤አለቃም የመጨረሻ ምርጫቸው የሆነውን ግዝት ለማስተላለፍ ተገደዋል፡፡
3/ የተጣሉት በስልጣንና በጥቅም ነው ፤
       ሥልጣንን በተመለከተ ፓትርያርኩ ሲኖዶሱን በርዕሰ መንበርነት የሚመሩበት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ያሉ ሲሆኑ፤ አለቃ አያሌውም በተሰለፉበት መስመር ለቤ/ክ እምነትና ሥርዓት ወሳኝና ተጠያቂ የሆነው የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢነት ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው፡ሁለቱም ህጉና ሥርዓቱ በሚፈቅድላቸው አገልግሎት የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ በመሆናቸው አንዳቸውን በአንዳቸው ላይ የሚያነሳሳ፤የጥቅምም ሆነ የሥልጣን ጉዳይ የለም፡፡ሊኖርም አይችልም፡፡
4/ ቄስ ያወገዘውን ጳጳስ (ፓትርያርክ) ይፈታዋል፤
       ይህ ሃሳብ በመጀመሪያ ክህነት አንዲት መሆኗን ካለመገንዘብ የመነጨ ነው፡፡በቤ/ክ አገልግሎት ከቅስና ቀጥሎ የሚሰጡት  ማለትም፤ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስ፣ሊቀ ጳጳስ (ፓትርያርክ) የሚባሉት ሹመቶች የሚያመለክቱት የተሾሙበትን የማስተዳደር ሃላፊነት ደረጃ የሚገልጹ ናቸው፡፡ጳጳስ ከሆነ ሃላፊነቱ ለተመደበበት ሀገረ ስብከት ሲሆን ሊቀ ጳጳስ(ፓትርያርክ) ሲሆን ደግሞ መላዋን ቤ/ክ የማስተዳደሩን ሃላፊነት መረከቡን የሚያመለክት ነው፡፡ከዚህ ባለፈ ኃጢአትን በማሰርና በመፍታት፣በማጥመቅና በማቁረብ በመሳሰሉት የክህነት አገልግሎቶች በኩል በቄሱና በጳጳሱ መካከል መበላለጥ የለም፡፡ከዚህ አንጻር ሃይማኖትና ሥርዓት አበላሽተው የተወገዙት ጳጳሳትና ፓትርያርኩ ውግዘቱን ሊፈቱ ይችላሉ ማለት፤ አንደ እስረኛ እራሱ እስር ቤት እያለ ሌላውን እስረኛ ይፈታል እንደ ማለት ያለና ፤ አጠቃላይ ከሃይማኖታዊ እይታ የወጣ አመለካከት ነው፡፡
5/ አለቃ አያሌውና ፓትርያርኩም ከዚህ ዓለም ስለ ተለዩ ውግዘቱ ተሽሯል፤
        ይህም እንደሌሎቹ ሰንካላ ሃሳቦች እራስን እየሸነገሉ ለማለፍ ካልሆነ በስተቀር እውነትነት የለውም፡፡ምክንያቱም ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ የተወገዙበትን ጥፋት ቀሪዎቹ ጳጳሳትና በእርሳቸው የተተኩት ፓትርያርክ የነበረውን ስህተት በማረም ፋንታ፤ የበለጠ አስፍተውና አጉልተው እየሰሩት በመሆኑ፤ የመጀመሪያው ውግዘት ዛሬም ይሰራል፡፡ለዚህም ቅ/ጳውሎስም በገላ.ም.1 ቁ.9 "አሰቀድሜ እንደተናገርኩ አሁንም ደግሞ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን እላለሁ፡፡"በማለት የተናገረው ቃለ እግዚአግሔር በእሱ እግር ለተተኩት እስከ ምጽአት ለሚነሱት ካህናት ሁሉ እንጂ ለራሱ ብቻ አይደለም፡፡እንዲሁም ካህናት ከሞቱም በኋላ ቢሆን ቃላቸው እንደሚሰራ፤ በወንጌል ከተመዘገበልን ከጌታችን ትምህርት ለምሳሌ ብንጠቅስ፤ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጌታችንን "ሁሉን ትተን ለተከተልንህ ለእኛ ዋጋችን ምንድነው?" ብለው ቢጠይቁት፤ጌታችን በዳግም ምጽአት ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ በ12 ዙፋን ተቀምጠው እንደሚፈርዱ ነግሯቸዋል፡፡( ማቴ.19፤27) ጌታችን በዚህ ክፍለ ትምህርት፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ልክ እንደ ክርስቶስ "ንዑ ኀቤየ፤ ሑሩ እምኔየ" ብለው ይፈርዳሉ ማለቱ ሳይሆን እነሱ በምድር እያሉ ባስተማሩት ትምህርት ባደረጉት ተአምራት አምኖ የተገኘ እንደሚፈረድለት ያላመነው እንደሚፈረድበት ለማጠየቅ (ለማስገንዘብ) ነው፡፡እንዲሁም ጌታችን ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን "ከጻድቁ አቤል ጀምሮ እስከ ካህኑ ዘካርያስ ድረስ የፈሰሰው የጸድቃን ደም በናንተ ላይ ይደርሳል"ብሎ ገስጿቸዋል፡፡(ማቴ.23 ቁ. 35) ስለዚህ ደም አልባው ሰማዕት የአለቃ አያሌውም  (ወልደ ጊዮርጊስ) በአካለ ነፍስ ሆነው የተበላሸው እምነትና ሥርዓት እስኪስተካከል ድረስ ጩኸታቸውን አያቋርጡም፡፡እግዚአብሔርም በጊዜው ጊዜ መፍረዱ አይቀርም፡፡
ሁለተኛ/ ችግሩን የተረዱ ነገር ግን ውግዘቱን ለመቀበል ያልቻሉ ካህናት፣ ዲያቆናትና ሌሎች አገልጋዮች፤
       በውግዘቱ ዙሪያ የካህናትና የዲያቆናት ድርሻ፤የተወገዙትን ፓትርያርክ በቅዳሴም ሆነ በማንኛውም ጸሎት ስማቸውን አትጥሩ የሚል ነው፡፡( የነ አርዮስ፣ የነ ንስጥሮስ ስም እንደማይጠራ ሁሉ) ይህንን ቃለ ውግዘት ተግባራዊ ላለማድረጋቸው የሚያቀርበት ምክንያት የፓትርያርኩን ስም ካልጠራንማ ከሥራ እንባረርና ከነቤተሰባችን እንቸገራለን የሚል ነው፡፡ይህ ደግሞ እንኳን በቅርብ ሆነው ለሚያገለግሉት ካህናት ቀርቶ ለራሳቸው ለፓትርያርኩና ለጳጳሳትም ደመወዝ የሚከፈለው በየአጥቢያው ካሉ ምእመናን ኪስ በሚሰበሰበው የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ መሆኑን ካለማስተዋል የመነጨ ነው፡፡ካህናቱም ከቤ/ክ መሪዎች የሚደርስባቸውን ችግር በመፍራት የምንደኝነት ሥራ ሲሰሩ ፤ምአመኑ ደግሞ የየዕለቱ አገልግሎት አለመቋረጡን ብቻ በመመልከት እየተጽናና ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡በአጣቃላይ ካህኑም ሆነ ምእመኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የባለቤትነት መብቱንና ግዴታውን ተገንዝቦ፤ ለቤ/ክ እምነትና ሥርዓት መከበር የየራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ባለመቻሉ ቤተ ክርስቲያኗ እንደ ግል ድርጅት በበላይ ሃላፊዎች ፈቃድ ብቻ የምትዘወር ሆና ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡

ሦስተኛ/ የችግሩንን ምንነት በውል ያልተረዱ ምእመናን የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች፤
1/ ማንም ካህን ቢቀድስ የሚቀድሱት ቅዱሳንና መላእክት ስለሆኑ፤
       ቅድስት ቤ/ክ በአጸደ ሥጋም በአጸደ ነፍስም ያሉ ክርስቲያኖች ሕብረት በመሆኗ ቅዱሳን በማንኛውም አገልግሎት በረድዔት የሚራዱ ሲሆን፤ቅዱሳን መላእክት ደግሞ የሚቀርበውን ጸሎትና መሥዋዕት በማሳረግ የሚራዱ ናቸው፡፡የሥርዓተ ቁርባን አገልግሎት ግን የሚከናወነው በካህናት ብቻ ነው፡፡በቤ/ክ ትምህርት ከመላእክት ክብር  የካህናት ክብር ይበልጣል የሚባለውም መላእክት በእጃቸው የማይነኩትን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን  ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ካህናት በእጃቸው ስለሚፈትቱ ነው፡፡ይህም አገልግሎት ሊሰምር የሚችለው ካህኑ ክህነቱን ጠብቆ በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆኖ ሲያገለግል እንጂ በትዕቢትና በድፍረት ከዚያም አልፎ በኑፋቄ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ለታይታ ወይም የሥራ ግዴታን ለመወጣት ብቻ የሚያቀርበው ከሆነ መላእክትም አያሳርጉትም እግዚአብሔርም አይቀበለውም፡፡ (የቃየልን መሥዋዕት ቁራ እንደበተነበት ልብ እንበል)
2/ መስቀሉ ጌታ የተሰቀለበት ስለሆነ ማንኛውም ካህን ቢያሳልመን ችግር የለውም፤
       ማንም ቢያሳልመን ችግር የለውም ካልን፤ለምን መስቀሉን ከእንጨት የሰራው አናጢ፤ወይንም ከብረት የሠራው አንጥረኛ፤ወይንም የሚሸጠው ነጋዴ ለምን አያሳልመንም󠄀 ብለን ብንጠይቅ፤ እነሱ ሥልጣነ ክህነት ስለሌላቸው ነው መልሱ፡፡እንዲህ ከሆነ ከመስቀሉ የሚገኘውን በረከት ልናገኝ የምንችለው ሥልጣነ ክህነት ያለው ካህን፤ማለትም ከውግዘቱ ነጻ የሆነ ካህን ሲያሳልመን ብቻ ነው፡፡
3/ እግዚአብሔር የሾማቸውን መቃወም አይገባም፤
      ይህ አባባል በመሠረተ ሃሳብነቱ ትክክል ቢሆንም ፓትርያርኩም ሆኑ ሌሎቹ የእሳቸውን ፈለግ የሚከተሉት ጳጳሳት፤ቤ/ክ በእውነት ለማገልገል የገቡትን የመሐላ ቃል አፍርሰው፤ ሹመታቸውን እንደ ይሁዳ በፈቃዳቸው ስለተውት፤ለቤ/ክ እምነትና ሥርዓት መከበር ሲባል ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ግዝት ማስተላለፋቸው እኛም በአቅማችን መጥፎ ስራቸውን መቃወማችን እግዚአብሔርን ፈቃድ እንደ ተቃወምን ሊያስቆጥርብን አይችልም፡፡

ማስታወሻ፤ የተከበራችሁ አንባብያን የተዋሕዶ ልጆች፤በዚህ አሁን በያዝነው ርዕስ ለሁሉም ማስረጃ እናቅርብ፤ መልስ እንስጥ ብንል ጉዳዩ ከመርዘሙ የተነሳ አንባቢን ስለሚያሰለች፤ በዚችው ጡመራ መድረካችን ከክፍል አንድ ጀምሮ "ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ" በሚለውና" እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ" በሚሉት ርዕሶች በተከታታይ ያቀረብነውን ቆየት ያለ ዘገባ ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ በመመልከት እውነተኛውን ነገር ማረጋገጥ እንደምትችሉ እንገልጽላችኋለን፡፡ይህንን ለማድረግ ለምትቸገሩ ደግሞ አለፍ አለፍ እያልን በድጋሚ እንለጥፈዋለን፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡
በቀጣዩ ክፍል፤ይህ የውግዘት ቃል ባለመከበሩ ያስከተለውን ችግርና ወደፊትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል በሚለው ሃሳብ ዙሪያ እንመለሳለን፡፡


No comments:

Post a Comment