Wednesday, August 15, 2018

“ ስለጽዮን ዝም አልልም ” ክፍል ሃያ ሰባት

ከክፍል ሃያ ስድስት የቀጠለ
የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤ ክፍል ሦስት
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
ሀ/ "የቀኖና ጥሰት" የቀጠለ
       ባለፉት ሁለት ክፍሎች በስፋት እንደተመለከትነው፤በተደጋጋሚ "የቀኖና ጥሰት" እየተባለ የሚነገረው "ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም" በሚለው ዙሪያ ይሁን እንጂ፤ (እሱም ተወራለት እንጂ መፍትሔ አላገኘም) የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን መሠረተ እምነቷንና ሥርዓቷን ትውፊቷን ሳይቀር የሚሸረሽሩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች፤ዓይነታቸውና ብዛታቸው  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ከላይ የተመለከትነው የአባቶቻችን መግለጫ፤ "…..ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን…" በማለት እውነታውን ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡እንደሚታወቀው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ እንደሆኑ፤ይህንን የፓትርያርክነት ሹመት ያገኙት በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ፤ ከዚያም ንጉሣዊውን ሥርዓተ መንግሥት በጉልበቱ አስወግዶ ሀገሪቱን በተቆጣጠረው ደርግ በተባለው ሃይማኖት የለሽ መንግሥት በግፍ ታፍነው እንደተገደሉ ታሪክ መዝግቦ አስቀምጦታል፡፡ቤተ ክርስቲያንም ምንም ዓይነት የፍትሕ ጥያቄ አለማቅረቧ ብቻ ሳይሆን ፤ቢያንስ አስከሬናቸው በተገቢው ሥፍራ በክብር እንዲያርፍ ሳታደርግ እንዲሁ "እንደ ንጉሡ አጎንብሱ" እንደሚባለው ሆኖ የደርግ መንግሥት እስከሚወድቅ ድረስ የከበረ አስከሬናቸው የነበረበት ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡

       እንግዲህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን  ለ40 ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷን ሥርዓቷን የሚያፋልሱ ብዙ ጥፋቶች እንደተፈጸሙባት ከታመነ፤ለማስተካከያውም ቅዱሳን አባቶች በሙሉ ኃይል በመነሳት፤በመጀመሪያ ችግሮቹን ነቅሶ ማውጣት፤ከዚያም ከራሳቸው ጀምሮ ታች እስካለው ምእመን ድረስ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መንገዱን ማመቻቸት አለባቸው ማለት ነው፡፡የዚህ ጸሁፍ አዘጋጅ ዋና ዓላማ "በሽታውን የደበቀ መድኃኒቱ አይገኝለትም" እንደሚባለው፤የነበሩትንና አሁንም ያሉትን ችግሮች በመጠኑ ለማሳየትና ሁላችንም እንደ ቤ/ክ ልጅነታችን አቅማችን የፈቀደውን እንድናደርግ ማሳሰብ ስለሆነ፤ በደርግ ዘመን የነበረውን ሰፊ ችግር ለማውሳት ርዕሳችን ስለሚያግደን፤ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ያለውን ችግር ብዙውን አንድ እያልን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
በውጪው( በስደተኛው) ሲኖዶስ በኩል፤
       ለስደተኛው ሲኖዶስ መመሥረት ዋናው መንስኤ፤ 4ኛው የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አሜሪካ አገር መሰደድ ነው፡፡አንዳንድ ሰዎች አቡነ መርቆሬዎስ በጎቻቸውን በትነው መሄድ አልነበረባቸውም እዚሁ መከራ መቀበል ነበረባቸው ሲሉ ይደመጣል፡፡ሆኖም ማንም ሰው መከራ የሚቀበለው እንደአቅሙና የእግዚአብሔርም ፈቃድ ሲጨመርበት  ስለሆነ፤ደግሞም ተወልደው ካደጉበት ተሹመው ከከበሩት (ያውም በቤተ ክርስቲያን) ሀገር ወደማያውቁት ሀገር መሰደድ እራሱ ሰማዕትነት ስለሆነ ለምን ይህን አላደረጉም ተብሎ ሊወቀሱ አይገባም፡፡የውጭውን ሲኖዶስ ሲመሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በግላቸው፤ በአፍም ሆነ በመጽሐፍ ይህን አደረጉ ተብሎ በጉልህ የሚነገር ችግር አልተሰማም፡፡(ምንልባት እኛ ያልደረስንበት ነገር ካልኖረ በስተቀር) ሆኖም እሳቸውን ተገን በማድረግ የቤ/ክ እምነትና ሥርዓትን የሚያፋልሱ አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ለመጥቀስ ያህል፤
1/ የተለያዩ መናፍቃን (ተሐድሶ)መሸሸጊያ መሆኑ፤
       ቤ/ክ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከውስጥም ከውጭም በሚነሱ ሃይማኖት ለዋጮች ስትፈተን ኖራለች፡፡ቀደም ያለውን ችግር ለታሪክ ጸሐፊዎች ትተን አሁን እኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆንበት ጊዜ ወዲህ ያለውን ስንመለከት፤በመናፍቃኑ የተመረጠው ዘመን አመጣሹ ተዋሕዶ ቤ/ክንን ገዝግዞ የመጣያው ስልት፤ ከቤ/ክ ውጭ ሆኖ ምእመኑን ወደ ተለያየ አዳራሽ ከመጥራት ይልቅ ቤ/ክ ውስጥ ሆነው የራሳቸውን የኑፋቄ ትምህርት በድብቅ በማስተማር ጥንታዊውን የቤ/ክ ትምህርት ቀሰ በቀስ መቀየር ነው፡፡ይህም የጥፋት ተልእኮ የሚያራምደው ኃይል እራሱን ኦርቶዶክስ ተሐድሶ ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው፡፡ ብዙዎቹ የዚህ ዓላማ አራማጆች እዚህ አገር ውስጥ ባለችው ቤ/ክ ውስጥ ውስጡን ሲበርዙና ሲከልሱ ኖረው ሲታወቅባቸው፤ከመወገዛቸው በፊት ሾልከው ሄደው የሚጠለሉት በውጭው ሲኖዶስ ሥር ነው፡፡ከዚያም አልፎ ሙሉ ለሙሉ ወደ ፕሮቴስታንቱ ድርጅት ገብተው እስከ ፓስተርነት ደረጃ የደረሱት ሳይቀሩ፡፡እነዚህ ሃሳውያን የውጪው ሲኖዶስ ለም መሬት ስለሆነላቸው የያዙትን የጥፋት ዓላማ እንደያዙ፤የቅስናና የመሳሰሉት የክህነት ማዕርጋትን፤ ከዚህም በላይ እጅግ በጣም የጎላ የሃይማኖት ህጸጽ ያለባቸውን ስመ መነኮሳት ጵጵስና እስከመሾም ደርሰው፤ይኸው አሁንም በእርቁ ሳቢያ አገር ውስጥ ገብተው አዲሱን ምደባ እየጠበቁ ነው፡፡
2/ ቤ/ክ ለአገልግሎት ከምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች ውጪ መጠቀማቸው
       ቤ/ክ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች ይታወቃሉ፡፡ቀደም ሲል በቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ በኦርጋንና በፒያኖ እንዲዘመር ያደረጉት አባት (ጳጳስ) አሁን እዚያው ስደተኛው ሲኖዶስ ውስጥ ናቸው፡፡አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስ ይህ መሣሪያ የዘፈን በመሆኑ በ1986 ዓ.ም ከቤ/ክ አውጥቶ ጥሎ ከዚያም በኋላ በየትም ቤ/ክ አገልግሎት እንዳይሰጥበት ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎዋል፡፡እዚያ ግን በማናለብኝነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
አገር ውስጥ ባለው ሲኖዶስ በኩል
       ቤተ ክርስቲያን ማለት በጥምቀትና በቅ/ቁርባን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች የሆኑ ሁሉ በአንድነት የሚኖሩባት በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ስትሆን ፓትርያርኩን፣ ጳጳሳንት፣(ሲኖዶስን) ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ ምእመናንን አጠቃላ የያዘች ነች፡፡የምትመራበትም ራሱን የቻለ ህግና ሥርዓት አላት፡፡ቤ/ክ በበላይነት የመምራት ሙሉ ሃላፊነቱ የቅ/ሲኖዶስ መሆኑ ባይካድም፤አገልግሎቱ ሊሰምር የሚችለው ሁሉም በተፈቀደለት ሥርዓት መሠረት የየድርሻውን መወጣት ሲችል ነው፡፡ካህናት ከሌሉ ቤ/ክ እንደማትከፈት ሁሉ ምእመናንም ከሌሉ ቅዳሴ እንደማይቀደስ ማለት ነው፡፡
       ወደ ተነሳንበት ርዕስ እንመለስና፤ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ከውጪው ሲኖዶስ አንጸር ሲታይ፤ ሀገረ ስብከቱ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር የአገልግሎቱ ደካማም ሆነ ጠንካራ ጎኖቹ የዚያኑ ያህል የሰፉ ናቸው፡፡በመሆኑም የዚህ ጸሁፍ አዘጋጅ ዓላማ፤ችግሮቹን ዓይነትና ብዛት ተመልክተን እርስ በርስ እየተተቻቸንና አንዳችን በሌላችን እያሳበብን እንድንኖር ሳይሆን፤ ለተፈጠሩት ችግሮች ይብዛም ይነስም የሁላችንም አስተዋጽኦ እንዳለበት አውቀን፤( ለምሳሌ መናፍቃኑ የሚያዘጋጇቸውን መዝሙሮች በገዛ ገንዘባችን እየገዛን ችግሩን ያስፋፋነው እኛ ምእመናን መሆናችን መዘንጋት የለብንም፡፡) ለመፍትሔውም የየራሳችንን ድርሻ ለመወጣት እንድንዘጋጅ ለማሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ቀደም ሲል የነበሩትንና አሁንም ያሉትን ችግሮች በመጠኑ እንመለከታለን፡፡
1/ በ1988 ዓ.ም በፓትርያርኩ በአቡነ ጳውሎስ ትእዛዝና በሌሎች ጳጳሳትና መምህራን አዘጋጅነት  ምሥጢረ ሥላሴን፣ምሥጢረ ሥጋዌን፣ነገረ ማርያምንና የመሳሰሉትን ትምህርቶች የሚያፋልስ መጽሐፍ ታትሞ ለህዝብ እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡
2/ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ (1600 ዓመታት ያህል) በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት በውግዘት ከተለየቻቸው የካቶሊክና የሁለት ባሕርይ አምላኪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤በሥርዓተ ጸሎታቸውና በማዕዳቸው በመሳተፍ ቤ/ክ የማትፈቅደውን ተግባር ፈጸመዋል፡፡ከሳቸው ጀምሮ እስከ አሁን ባሉት አባቶችም በእኛና በካቶሊክ መካከል ያለው ልዩነት ትንሽ ነው እየተባለ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡
3/ በ1988 ዓ.ም፤ /ክ ለብዙ ዘመናት ስትመራበት የነበረውን ህገ ቤ/ክ ሽረው፤ የሲኖዶሱ ጸሐፊ ብሎም አጠቃላይ ሲኖዶሱ ተጠሪቱ ለመንፈስ ቅዱስ መሆኑ ቀርቶ ለፓትርያርኩ እንዲሆን የሚያደርግ ህግ አውጥተዋል፡፡
 4/ ጥር አንድ ቀን 1989 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ ዓመታዊ በዓል ላይ ፓትርያርሁ አቡነ ጳውሎስና ሌሎችም ጳጳሳት በተገኙበት ዓውደ ምሕረት በታቦት ፊት አንድ ባህታዊ በፓትርያርኩ አጃቢ ሲገደል በዚያ በዓል ላይ የተገኙት በርካታ ምእመናን ተደብድበዋል፡፡በዚሁ ትርምስ ታቦቱን የተሸከሙት ካህን በመደንገጣቸው መቆም ስላልቻሉ፤ ሌላ ካህን ታቦቱን ተቀብሎ በሴቶች በር ይዞ በመግባት፤ምእመኑ ያለ ጸሎትና ያለ ቡራኬ እንባውን እየተራጨ ተመልሷል፡፡ለተገደለውም ሰው ቢያንስ በኢትዮጵያዊነቱ ፍትህ የጠየቀ የለም፡፡ስለሆነም ደሙ እንደ አቤል ደም እየጮኸ ይኖራል፡፡
5/ ምንም ዓይነት የቤ/ክ እውቀት ሳይኖራቸው፤ አንዳንዶቹ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሆን ብለው እምነታችንንና ሥዓታችንን ለማፋለስ፤ የሚያዘጋጇቸው ለቁጥር የሚታክቱ መጻሕፍትና መዝሙሮች እየታተሙ በቤ/ክ ስም ሲሰራጩ ለማስቆም ቀርቶ ለመከላከል ባለመሞከሩ፤የቤ/ክ እምነትና ሥርዓትን ከሌሎቹ እምነቶች  ለመለየት እስከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
6/ ከላይ በገለጽነው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆችና በሌብነት ሥራ በተሰማሩ ሃላፊዎች ምክንያት ሃይማኖታችን፣ሥርዓታችን ተበላሸ፣የቤ/ክ ሃብትና ንብረት የግለሰቦች መጠቀሚያ ሆነ ብለው የጠየቁና የተከራከሩ ካህናት፣ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተገድለዋል፣ታስረዋል፣ከሥራ ተፈናቅለዋል…..ወዘተ፡፡ምሳሌ ቢባል በአዲስ አበባ ብቻ፤ በደብረ ናዝሬት ቅ/ዮሴፍ፣ በልደታ ለማርያም ፣በሰዓሊተ ምሕረት ፣በብሔረ ጽጌ ማርያም ፣በቅ/ኡራኤል፣በገርጂ ጊዮርጊስ፣በቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ወዘተ
7/ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዓላማ አራማጆች የጥፋት ተልእኮ በተመለከተ፤እኩይ ሥራቸውን ለሃይማኖታቸው ቀናእያን የሆኑ የቤ/ክ ልጆች እተከታተሉ፤ የሊቃውንት ጉባዔ ድረስ ማስረጃ ሲያቀርቡ፤ ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ በመስጠት ፋንታ በሌላ ደብር እየተመደቡ ችግሩ የበለጠ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ከዚህም በላይ ጥያቄ አቅራቢዎቹን የተዋሕዶ ልጆች አክራሪ፣ጽንፈኛ፣ሽብርተኛ፣አሳዳጅ….የሚል ስም እየተሰጣቸው በገዛ ቤ/ክናቸው እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ በማድረግ፤በአንጻሩ ደግሞ መናፍቃኑ ከአጥቢያ ቤ/ክ ጀምሮ እስከ መንበረ ጵጵስናው ድረስ ባለ ሙሉ መብት እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
8/ የፈለጉትን ያህል አጥፍተው መስሎ ማጭበርበሩ ሲሰለቻቸው በገዛ ፈቃዳቸው የወጡትም ሆነ  በግድ ተወግዘው የተለዩት የውስጥ መናፍቃን (ተሐድሶዎች) የቤ/ክ የማዕረግ ስም (ዲያቆን፣መምህር፣አባ፣ቀሲስ..)እየተባሉ፤ የአገልግሎት አልባሳት (ካባ፣ ቆብ፣ቀሚስ፣ ነጠላ፣መስቀል..)እንደለበሱ የማጭበርበር ሥራ ሲሰሩ የጠየቃቸው የለም፡፡
9/ እውነተኞቹ ሊቃውንትና አገልጋዮች እየተገፉ፤ ጉቦ መስጠት የሚችሉ፣ በዘርና በጎሳ የተሳሰሩ አፈ ጮሌ የሆኑ እውቀትና ሃይማኖት አልባዎች ወሳኙን የሥልጣን ደረጃ እንዲይዙ መደረጉና ፍትህ በመታጣቱ ለአቤቱታ ወደ መንግሥት አካልና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እስከ መሄድ መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
10/ የቤ/ክ መምህራንን ቀጥራ፣ልብስ ቀለብ ችላ፣ትምህርቴን ተምረው የዘመኑን ትውልድ በፈሊጥ ያስተምሩልኛል ብላ ትልቅ ተስፋ የጣለችባቸው በእጣት በሚቆጠሩ መንፈሳዊ ኮሌጆች ከሚማሩ ተማሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ፤ ከክትትልና ከቁጥጥር ማነስ የተነሳ በድብቅ በሚሰጡ የመናፍቃን ሥልጠናዎች እየተበረዙ፤ወደ ኮሌጅ ሲገቡ መንፈሳውያን የነበሩት ተምረው ሲወጡ መናፍቃን ሲሆኑ ለዚህ ያበቃቸው ችግር ተጠንቶ መፍትሔ ባለመሰጠቱ ችግሩ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው፡፡ከዚህም አልፎ መናፍቃኑ እግራቸውን አስረዝመው በተለያዩ የአብነት ጉባዔ ቤት በመግባት፤ በሃያ አራት ሰዓት አንድ ጊዜ፤ያውም "ቋርፍ" የተባለ መራራ የዛፍ ሥር እየበሉ በሚኖሩበት በዋልድባ ገዳም ሳይቀር ገብተው የቅሰጣ ስራ እየሰሩ መሆኑ ከራሳቸው ሰነድ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡   
11/  የቤ/ክ ህንጻ በአጸራረ ሃይማኖተኞች በግሬደር ሲፈርስ፣ በእሳት ሲቃጠል፣ ቅርሶቿንና ንዋያተ ቅድሳቷን ሲዘረፉ፣የጥምቀትና የደመራ ማክበሪያ ቦታዎችዋ ሲወረሱ ተከራካሪዎቹ ምእመናን ብቻ ናቸው፡፡አገራችን ለዱር እንስሳት እንኳን ፓርክ ተዘጋጅቶ መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩባት ስትሆን፤ ዓለም በቃን ብለው ጫካ የገቡ፤እንደ ሌላው ዜጋ የመብራት፣የውሃ የስልክና የመሳሰሉትን ፍጆታዎች የማይፈልጉ፤ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ቅጠል እየቀመሱ፤ እንደ ዋልድባ በመሳሰሉት ታላላቅ ገዳማት የሚኖሩ መናንያን በጫካ እንኳን የመኖር መብት ተነፍጓቸው ገዳማቸውን ለቀው እንዲሰደዱና እንዲበተኑ ከዚያም አልፎ እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡
12/ በአጠቃላይ እነዚህና የመሳሰሉት የውስጥና የውጪ ችግሮች በጋዜጣና በኢንተርኔት ለዓለም በመሰራጨታቸው ቤ/ክ ለመናፍቃንና ለአሕዛብ መሳለቂያ ስትሆን የሚመለከቱ ምእመናን የማይጠገን የልብ ስብራት አድርሶባቸዋል፡፡      
ለ/ ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን አለመወጣቱ
       ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር በተሰጠው አደራ የወንጌልን ቃል ለዓለም ሁሉ ማዳረስ፤ያላመኑትን በማሳመንና ያመኑትንም እስከ መጨረሻው ጸንተው እንዲኖሩ ማበረታታት፤ በተለያየ ኃጢአት የተሰነካከሉትን በንስሃ በማደስ ሁሉንም የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻልና፤ በአጠቃላይ ከቀደሙት አባቶቻችን የተረከብናት የተዋሕዶ ሃይማኖት ሳትበረዝና ሳትከለስ ለቀጣዩ ትውልድ እንድትተላለፍ ማድረግ ነው፡፡እንግዲህ ከላይ ለተመለከትናቸው የተለያዩ ችግሮች የተጋለጥነው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ሲሆን፤ለዚህም ከዋነኞቹ ምክንያቶች አንዱ የቤ/ክ መሪዎች በየጊዜው የሚለዋወጠው ዓለማዊ አስተዳደር (መንግሥት) ጥገኛ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ  ማትያስ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. 34ኛውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔን የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ  የተናገሩትን ስንመለከት ከላይ ያለውን ሃሳብ ያረጋግጥልናል፡፡
       "…..ባህርን አቋርጦ፣ድንበርን ተሻግሮ፣እስከ ጽንፈ ምድር ተጉዞ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤ/ክ ልጅ ማደርጉ ይቅርና በሀገሩ ውስጥ ያሉትን ወገኖች ቤ/ክ ውስጥ አጠራቅሞ ምዕመናንን ማበዛቱ የቱና ያህል የተሄደበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ከሁሉ በላይ የሚያስቆጨው ደግሞ ትናንት ቤ/ክ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ሰጥታ በሃላፊነት የተቀበለቻቸውን ልጆቿ ዛሬ እናት ቤ/ክ እየከዱ ወደ ሌላ ጎራ የመቀላቀሉ ጉዳይ እጅግ በጣም እየናረ መምጣቱ ነው፡፡የምዕመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ የመሄዱ መነሻ ምስጢር ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ቤ/ክ በአንክሮ ልታጤነው ይገባል፡፡…….ይኸውም ምዕመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዷችንን ከመቅረታችን በፊት ለተለያየ ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል እንነሳ፡፡….."
       እንዲሁም በቅርቡ የአ.አ.ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት መምህር ይቅርባይ፤ይህንን የቤ/ክ መጠነ ሰፊ ችግር ቁጭት በተሞላው አነጋገር እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤
"….አሁን የምናየው ኹኔታ ከዚህ ፈጽሞ የተለየም ብቻ ሳይኾን፣ ፍጹም ተቃራኒና ከመንፈሳዊ አባቶችና ወንድሞች ቀርቶ ከሰብአ ዓለም እንኳ የማይጠበቅ ተግባር በመኾኑ፣ እያንዳንዳችን እንደየአቅማችን ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፤ ቤተ ክርስቲያናችንንም ዋጋ እናስከፍላታለን፡፡"……"በኑፋቄአቸው አወናብደው ከወሰዱብን ይልቅ፣ በመጥፎ ሥነ ምግባራችን ዕንቅፋት ኾነን ያባረርናቸውን ዓለም ይቁጠራቸው፡፡ ስለዚህ በጋራ ኾነን ብልሹ አሠራርን አርመን ወደ መልካም አስተዳደር እናምጣ፡፡"
(ማስታወሻ፤ መምህር ይቅርባይ የአ.አ.ሀ.ስብከት ሥራ አስኪያጅነቱን ሃላፊነት በተረከቡት ዕለት ለሥራችን መቃናት በሃሳብም በጸሎትም አግዙን ማለታቸው አይዘነጋም፡፡እኛም ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ የጋራችን እስከሆነ ድረስ በተሰጠን የቤት ሥራ መሠረት ቤ/ክ ከገባችበት አዘቅት እንድትወጣ ከጸሎትና ከጾም ጋር በሁሉም ነገር መትጋት ይጠበቅብናል፡፡)
ሐ/ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቤ/ክ ልጆች…..ይቅርታ እንዲጠይቅ
       ይቅርታ መጠየቅ ወይም ይቅርታ ማድረግ የሚባለው ነገር የሚመጣው በሁለት ሰዎች ወይም ቡድኖች መካከል፤አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡ለመታረቅ የሚችሉት ደግሞ ምናልባት የተበደለው አካል ይቅርብኝ ብሎ ካልተወው በስተቀር የበደለው አካል ለተበዳዩ የቀማውን መልሶ የበደለውን ክሶ ሲሆን እርቁ ከልብ የመነጨ ይቅርታ የሚያሰጥ ይሆናል፡፡እንዲሁም ሰው ኃጢአት ሰርቶ ከፈጣሪው ሲጣላ ከፈጣሪው ለመታረቅ በመጀመሪያ ስለ ሰራው ኃጢአት መጸጸት፤በመቀጠልም እንደ ቤ/ክ ሥርዓት ለንስሃ አባቱ መናዘዝ ይጠበቅበታል፡፡በኑዛዜው መሠረት ካህኑ የሰጠውን ቀኖና ሲጨርስ በካህኑ አማካይነት(ይቅርታ) ሥርየተ ኃጢአት ያገኛል፡፡
       እንደዚሁ ሁሉ ከላይ በመግለጫው እንደተመለከትነው በአባቶቻችን አለመግባባትና ከዚያ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት እኛ ልጆቻቸው፤ ከፍተኛ የልብ ስብራት እንደደረሰብን አባቶቻችን ከተረዱልን፤ "ከቁስል ሁሉ የልብ ቁስል ይከፋል" እንደሚባለው፤ ይህ የልብ ስብራት ሊጠገን የሚችለው በነዚህ አስከፊ ጊዜያት የተፈጠሩትን ስህተቶች ማረም ሲቻልና ቤ/ክ ወደ ቀደመ ክብርዋ ስትመለስ እንጂ ጉዳዩ እንደ ቀላል ነገር ታይቶ፤አጥፍተናል ይቅር በሉን በማለት ብቻ የሚቋጭ መሆን የለበትም፡፡

የተከበራችሁ አንባብያን!  የጀመርነውን ርዕስ አላጠቃለልንም፡፡
በቀጣዩ ክፍል ይዘን እንቀርባለን
ለዛሬው ይቆየን፡፡




No comments:

Post a Comment