ከክፍል ሃያ ስድስት የቀጠለ
የዶግማና
የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤ ክፍል ሦስት
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚች ዕለትና ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን
አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
ሀ/ "የቀኖና ጥሰት" የቀጠለ
ባለፉት ሁለት ክፍሎች በስፋት
እንደተመለከትነው፤በተደጋጋሚ "የቀኖና ጥሰት" እየተባለ የሚነገረው "ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም" በሚለው ዙሪያ ይሁን እንጂ፤ (እሱም ተወራለት እንጂ መፍትሔ አላገኘም) የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን መሠረተ
እምነቷንና ሥርዓቷን ትውፊቷን ሳይቀር የሚሸረሽሩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች፤ዓይነታቸውና ብዛታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ከላይ የተመለከትነው የአባቶቻችን መግለጫ፤
"…..ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን…" በማለት እውነታውን ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡እንደሚታወቀው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ እንደሆኑ፤ይህንን የፓትርያርክነት ሹመት ያገኙት በአጼ ኃይለ ሥላሴ
ዘመነ መንግሥት እንደሆነ፤ ከዚያም ንጉሣዊውን ሥርዓተ መንግሥት በጉልበቱ አስወግዶ ሀገሪቱን በተቆጣጠረው ደርግ በተባለው ሃይማኖት
የለሽ መንግሥት በግፍ ታፍነው እንደተገደሉ ታሪክ መዝግቦ አስቀምጦታል፡፡ቤተ ክርስቲያንም ምንም ዓይነት የፍትሕ ጥያቄ አለማቅረቧ ብቻ ሳይሆን ፤ቢያንስ አስከሬናቸው በተገቢው ሥፍራ በክብር እንዲያርፍ ሳታደርግ እንዲሁ "እንደ ንጉሡ አጎንብሱ" እንደሚባለው ሆኖ የደርግ መንግሥት
እስከሚወድቅ ድረስ የከበረ አስከሬናቸው የነበረበት ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡