Thursday, July 25, 2013

ስለ ጽዮን ዝም አልልም!!! ኢሳ.62፥1 ክፍል ሶስት

ካለፈው የቀጠለ
       የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣

ን ዝም አልልም ” በሚለው ርዕስ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍሎች በቅድስት ቤ/ክ ውስጥና በዙሪያዋ የሚከናወነው ንግድ የተወገዘ እንደሆነ የጌታችንን ወንጌል ጠቅሰን ባቀረብነው ጽሁፍ ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ተስፋ በማድረግ በሶስተኛው ክፍል ደግሞ የዘመናችን የቤ/ክ መሪዎችም ቅድስት ቤ/ክ ከተልእኮዋ ውጪ  በዚሁ የንግድ ስራ እንድትሰማራ ያደረጉበትን ሁኔታ እንመለከታለን::

ሐ/ በቅድስት ቤ/ክ የተቋቋሙ የንግድ ማዕከላት

        ሁላችንም እንደምናውቀውና እንደምናየው በአሁኑ ጊዜ እንኳን ረጅም እድሜና ሰፋፊ ቦታ ያላቸው ይቅሩና በቅርብ ጊዜያት የተተከሉት አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ ገና በመቃረቢያ/ መቃኞ/ እያሉ ማለትም ዋናው ቤ/ክ ሳይጀመር በቅድሚያ የሚሰራው የንግድ ቤት ነው::አንጋፋዎቹና ሰፋ ያለ ቦታና የገንዘብ አቅሙ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ትላልቅ ፎቆችን እየገነቡ የንግድ ስራውን በሰፊው ሲያከናውኑት ይታያል:: ሁኔታውን በማስተዋል ከተመለከትነው አባቶቻችን ባወረሱን  መሰረት ከዋናው ህንፃ ቤ/ክ በተጨማሪ የሚሰሩት ለቤ/ክ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቢሮዎች ማለትም የሰበካ ጉባኤ ፣ የስብከተ ወንጌል፣የካህናት አስተዳደር፣ የሰ/ት/ቤት አዳራሽና  እንዲሁም የጽዋ ማህበራትና የሰንበቴ ቤትን የመሳሰሉትን  እንጂ የንግድ ቤቶችን ሰርተው አላስረከቡንም።
      ታዲያ የዛሬዎቹ የቤ/ክ መሪዎች ወደዚህ ስራ ለምን ተሰማሩ ብለን ብንጠይቅ ዋናው ምክንያት በቀድሞዎቹ መንግሥታት ለቤ/ክ መተዳደሪያ ይሰጣት የነበረው ድጎማና ትተዳደርበት የነበረው ርስትና ጉልት በአሁኑ መንግሥት ስለተቋረጠ መሆኑ ግልጽ ነው::ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ችግር ሲፈጠር የወንጌሉ ቃል ሳይፋለስ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትተዳደርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻል ነበር :: ይህም ማንኛውም ምዕመን መንፈሳዊ ግዴታው መሆኑን አስተምሮና አሳምኖ ተገቢውን አሥራት ፣ በኩራትና ቀዳምያቱን እንዲያወጣ ማድረግና በዚህ መልክ ከምዕመናን የተገኘውን ገቢ አንዱን እጅ ለአገልጋይ ካህናት፣ ለዲያቆናትና የተለያዩ ሠራተኞች ደምወዝ ፤ ሁለተኛውን እጅ ቤ/ክንን ተስፋ አድርገው ለሚኖሩ ነዳያን ፤ ሶስተኛውን እጅ ደግሞ ለቤ/ክ የተለያዩ ወጭዎች በመመደብ እንድትተዳደር ማድረግ ነበር :: ሥርዓተ ቤ/ክ የሚያዝዘንም ካህናት ለምዕመናን እንዲጸልዩ ፣የሚያስፈጋቸውንም ምሥጢራተ ቤ/ክ እንዲፈጽሙላቸው፤ ምዕመናን ደግሞ ለካህናቱ ቀለባቸውን እንዲሰፍሩላቸው ነው::
      እንደሚታወቀው ቤ/ክ  ወንድ ልጅ በተወለደ በአርባ ቀኑ ሴት ልጅ ደግሞ በተወለደች በሰማንያ ቀኗ በስመ ሥላሴ አጥምቃ  የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየመገበች ከእግዚአብሔር የጸጋ ልጅነትን እንድናገኝ ከማድረግ ጀምሮ መላ ሕይወታችንን በቅድስና እንድንኖር እንደየጸጋ ስጦታችን ጋብቻችንንም ሆነ ምንኩስናችንን የምትባርክልን ከሥጋችን ደካማነት የተነሳ በኃጢአት ብንሰነካከል እንኳን በንስሃ ውሃ እያጠበች ለዘላለም ሕይወት የምታዘጋጀን ቅድስት እናታችን ናት ቤተ ክርስቲያናችን :: በዚህ ሁኔታ ሕይወታችንን እየተንከባከበች ያኖረችን ቤ/ክ ከዚህ ዓለም በሥጋ ሞት ከዚህ ዓለም በምንለይበት ጊዜ ደግሞ ነፍሳችንን እግዚአብሔር በገነት በአብርሃምና በልጆቹ እቅፍ እንዲያኖራት በጸሎት ስትሸኝ ሥጋችንን ደግሞ እስከ ትንሣኤ ዘጉባዔ ድረስ በጉያዋ (በቤ/ክ ዙሪያ) ተቀብሮ እንዲቆይ ታደርጋለች::
        የነባሪቱ ቤ/ክ ሁኔታ ይህንን የመሰለ ይሁን እንጂ አሁን የሚታየው ግን ልክ ቤ/ክ ያለ ንግድ ቤት መኖር የሌለባት እስኪመስል ድረስ በቤ/ክ የሚታየው የንግድ ሥራ ከላይ በክፍል አንድ ላይ እንደተገለጸው በዋናነት “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” የሚለውን የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ የሚቃወም ሥራ ከመሆኑ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም አሉት:: ለምሳሌ ያህል ጎላ ጎላ ያሉትን ብንመለከት፦

1/ የቤ/ክ በፎቅ መከለል

     እንደ ሃይማኖታችን ሥርዓት በእግሩም ሆነ በመኪና በመጓዝ ላይ ያለ ክርስቲያን ወደ ቤ/ክ ገብቶ ለመሳለም ካልቻለ በሩቁ ሆኖ “ ስላም ለኪ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ”ብሎ እጅ ነስቶ ( ተሳልሞ ) ያልፋል :: ትላልቅ የንግድ ህንጻዎች የተሰሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ግን በነዚህ ፎቆች በመከለላቸው ለመሳለም ይቅርና ቤ/ክ መሆን አለመሆኑን ለመለየት እንኳን የሚያስቸግርበት ደረጃ ላይ ደርሷል::

2/ ለልማቱ ሲባል በክብር ያረፉ የክርስቲያኖች አጽሞች እየተፈነቀሉ መጣላቸው

      በቤ/ክ ለንግድ ሥራ የሚፈልጉትን  ህንጻ ለመሥራት የሚጠቀሙት በዚያው በነባሩ የመሬት ይዞታዋ ላይ በመሆኑ ባዶ ቦታ የሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠሩ መቃብሮችን እያፈረሱ አጽሞቻቸው ለግንባታ ሥራ ከሚቆፈረው አፈር ጋር እየተዛቀ በአልባሌ ቦታ እንዲወድቅ ተደርጓል :: ምናልባት አጽሞቻቸውን በመሰብሰብ በአንድ ጉድጓድ የማከማቸት ሥራ ተሰርቷል ቢባል እንኳን አጽሞቹ የሚነሱበት ዓላማው ንግድ በመሆኑ መነፈሳዊ ድጋፍ አይስጠውም :: አንዳንዶች አጽም ማፍለስ ማለትም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር  በቤ/ክ የተፈቀደ እንደሆነ በመግለጽ ለጥፋቱ ከለላ ለመስጠት የሚሞክሩ አሉ:: እዚህ ላይ አንድ ግንዛቤ እንጨብጥ::
      ለምሳሌ ኦሪት ዘፍጥረትን ስንመለከት የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ወንድሞቹ ለግብጽ ነጋዴዎች እንደሸጡትና ከብዙ ፈተና በኋላ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ላይ እንዳከበረው፤አባቱ ያዕቆብና ወንድሞቹ በረሃብ ምክንያት ከከነዓን ምድር ወደ ግብጽ ተሰደው በዚያው ብዙ ዘመን እንደኖሩና እንደበዙ ታሪኩ ያስረዳናል::ጻድቁ ዮሴፍ ከመሞቱ በፊት  እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠውን ተስፋ ስለሚያውቅ ወገኖቹ ከዘመናት በኋላ ከግብጽ የባርነት ኑሮ ወጥተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን በሚሄዱበት ጊዜ በባዕድ አገር እንዳይቀር  አጽሙን ከነርሱ ጋር እንዲወስዱ በተናዘዘው መሰረት እስራኤላውያን (ያዕቆባውያን) ከግብጽ በሚወጡበት ጊዜ አጽሙን ከመቃብር አውጥተው በተቀደሰችይቱ ምድር አሳርፈውታል:: (ዘፍ∙50 ቁ 22 -26 ) ታዲያ አጽም ለማፍለስ የምንገደድበት ምክንያት ይህና ይህንን የመሳሰሉ ምክንያቶች ሆነው እያለ በኛ ዘመን ደግሞ በተቃራው የተቀደሰውን የክርስቲያኖች አጽም  ከተቀደሰው ሥፍራ  እያወጡ ወደ ቆሻሻ ሥፍራ እንዲጣል ማድረጋቸው ሳያንስ “ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነች ይሏታል ” እንደሚባለው ዘይቤያዊ አነጋገር ለጥፋት ሥራቸው ቃለ እግዚአብሔርን ያለ አገባብ በመጥቀሳቸው ቃሉ እራሱ ይፈርድባችዋል::
     ከዚህ ጋር አያይዘን የምናየው ሌላው ጥፋት የዘመናችን የቤ/ክ መሪዎች የከፈቱትን የጥፋት ጎዳና ተከትሎ ከሃዲው መንግሥትም በልማት ሰበብ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና እንደ ታላቁ ገዳማችን እንደ ዋልድባ በመሳሰሉት ገዳሞቻችን ላይ ሳይቀር የብዙ ቅዱሳን መቃብሮችን እያፈረሱና አጽሞቻቸውም ወደ ዱር እየተጣለ መሆኑን እያየን ነው::ቤተ ክህነቱም ሆነ ቤተ መንግሥቱም የጥፋቱ ባለቤቶች ስለሆኑ  ችግሮቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መናንያንና ምዕመናንም አቤቱታቸውን የሚሰማቸው በማጣታችው ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው ወደ ልዑል እግዚአብሔር ከመጮህ በስተቀር ሌላ ምርጫ አላገኙም ::

3/ በየንግድ ቤቶቹ ውስጥ የሚፈጸሙ አጸያፊ ሥራዎች

     የንግድ ቤቶቹን የሚከራዩት ግለሰቦችም ይሁኑ ድርጅቶች የቤቱን ጣራና ግድግዳ እስካልጎዱ ድረስ በቤቱ ውስጥ የፈለጉትን ለማድረግ መብታቸው ስለሆነ የሚከለክላቸው የለም:: ዕቃ ለመግዛት ወይም አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡትም እንዲሁ:: ስለሆነም በተቀደሰው ሥፍራ ላይ በተሰሩ የንግድ ቤቶች ሲጋራ ይጤስባቸዋል፣ ጫት ይቃምባቸዋል ፣ ወደ ዝሙትና ወደተለያዩ የኃጢአት ዓይነቶች የሚመሩ ዘፈኖች ይዘፈኑባቸዋል ሌሎችም ይህንንም የመሳሰሉ አጸያፊ ሥራዎች ይሰሩባቸዋል:: ከገበያው ሁካታና ግርግር የተነሳ ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት የማይችሉ ምዕመናን በግቢው ውስጥ ሆነው ለማስቀደስም ይሁን ትምህርት ለመስማት እንዲሁም የግል ጸሎታቸውን ለማድረስ ይቸገራሉ ::

4/ የንግድ ቤቶቹን የሚከራዩት ከሃይማኖታችን ውጪ የሆኑ ሰዎችም ጭምር መሆናቸው

     ከላይ በተመለከትነው ዓይነት የንግድ ቤቶቹን ለመከራየት የሚመጡት ግለሰቦች የተተመነውን ኪራይ እስከከፈሉ ድረስ ቤቱን ይከራያሉ የፈለጉትንም ይሰራሉ:: በእምነትም በኩል የተለያየ እምነት ተከታዮች ሊሆኑ ይችላሉ:: ይህ ስፍራ ከስጋም ከነፍስም ደዌ የምንፈወስበት የተቀደሰ ስፍራ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ለስጋዊ ሥራ ተላልፎ የተሰጠ ስለሆነ ሁሉም እንደ እምነቱ የፈለገውን ሲያደርግበት ይውላል ያድራልም::በአንዱ በተቀደሰው አደባባይ ከውስጥ ቅዳሴ ይቀደስበታል ከውጭ የመናፍቃንና የመሳሰሉት <<መዝሙር>> ይዘመርበታል:: ከውስጥ ምዕመናን ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ ከውጭ አረማውያን ለጣኦት ይሰግዱበታል:: ሌላም ሌላም::

5/ የእያንዳንዱ ቤ/ክ የገቢ መጠን መዛባት

     ከላይ በዘረዘርነው ሁኔታ በሰፊው ለመነገድ እድሉ የገጠማቸው አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ገቢ ስለሚያገኙ የአገልጋዮቹም ደመወዝ በዚያው መጠን ከፍ ይላል:: ከከተማ ወጣ ያሉት ደግሞ ካህናቱ ለቅዳሴ ጊዜ እንኳን የሚለብሱት ልብሰ ተክህኖ ፤ ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን እጣንና ጧፍ የመሳሰሉትን ስለማያገኙ እስከመዘጋት የደረሱት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: የየአጥቢያው ምዕመን አሥራት በኩራቱን እያወጣ ቤ/ክ እንዲያስተዳድር ቢደረግ ግን የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ ይወገዱ ነበር::
     የተከበራችሁ ክርስቲያኖች ከዚህ በላይ ከብዙው በጥቂቱ የተመለከትነው ችግር ቅድስት ቤ/ክንን ከከበቡዋት ሌሎች ችግሮች ማለትም እምነታችንንና ሥርዓታችንን እያፋለሱ ካሉ የውስጥና የውጭ መናፍቃን እየደረሰባት ያለው ከፍተኛ ተጽዕኖ ፤ ሀብትና ንብረቷ አልፎ ተርፎም ንዋያተ ቅድሳቶቿ ሳይቀሩ እየተዘረፉ የግለሰቦች መጠቀሚያ መሆናችው፤ መሪዎቿ ከጠባቡና ከመንፈሳዊው ጎዳና ወጥተው የራሳቸውን ዓለማዊ ኑሮ ሲያደላድሉ በጎቹ (ምዕመናን) ያለ እረኛ በተኩላዎች መካከል ተበትነው እየተቅበዘበዙ መሆናችው፤ ይህንንና ይህንን ከመሳሰሉት ችግሮች ጋር ተደምሮ ያለንበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል እንድናስተውልና  “ ከእኔ ምን ይጠበቃል? ” ብለን ለመፍትሄ እንድንዘጋጅ ነው የዚህ መልእክት ዋና አላማ::
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዚሁ ርዕስ በሌላ ጊዜ እንቀጥላለን::
ለዛሬው ይቆየን :: 

No comments:

Post a Comment