Monday, July 2, 2012

“ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” ማቴ. ፳፬ ቁ. ፬ ክፍል ፪


ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ማቴ. ፳፬ ቁ. ፬ ካለፈው  የቀጠለ:
         “የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ትምህርት ትውፊትና ታሪክ ጠብቆ የተዘጋጀ ” የተባለለት መጽሐፍ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ / እምነት፤ሥርዓተ እምልኮትና የውጭ ግንኙነት) ይ ከሰፈሩት ስህተቶች በጥቂቱ ከዚህ በታች እንመለከታለን::

 1/ በገጽ 37 በምዕራፍ 7 ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም በሚለው ርዕስ ሥር እንዲህ ይላል “ እመቤታችን በዘመኗ ከነበሩት ደናግል ተለይታ እግዚአብሄር ከፈጠራት ጀምሮ  በአሳብ ፤ በመናገር ፤ በመስራት ፤ ንጽሐ ጠባይዕ ያላድፈባት ድንግል ናት::“  በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ትልቁን ኑፋቄ የያዘው “ በዘመኗ ከነበሩት ደናግል ተለይታ” የሚለው ሐረግ ነው:: ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ለስም አጠራሯ ክብር ምስጋና ይግባትና ምንም እንኳን የሰዎች ትችት ሆነ ስድብ የእመቤታችንን ክብር የሚቀንስ ባይሆንም የነ አባ ጳውሎስ አባባል እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቦና ታስባ የነበረች ፤ ዓለም ከተፈጠረ በኋላ ደግሞ ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ንጽህት ቅድስት የዘላለም ድንግል መሆኗን በሚያመለክቱ  ምሳሌዎችና ትንቢቶች በብዙ ነቢያት ሲነገርላት  ቆይቶ ጊዜው ሲደርስ መልእኩ ቅዱስ ገብርኤል አምላካችን እግዚአብሔር ወልድ ሰውን ለማዳን ከእርሷ እንደሚወለድ ባበሰራት ጊዜ  ”እንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ “ ብሎ የሰጠውን ምስክርነት የሚያስተባብል ነው ::

 2/ በዚሁ መጽሐፍ በገጽ 39 “የእማላጅነት ቃል ኪዳን” በሚለው ርዕስ ሥር
       ”ቤተክቲያናችን ስለ እመቤታችን አማላጅነትና ቃልኪዳን የምታስተምረው ፍጹም በሆነ ሐዋርያዊ ትውፊት ነው::” በማለታቸውም በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውንና ለዘላለም የጸናውን ቃል ኪዳኗን በማቃለል እማላጅነቷ በትውፊት ብቻ የተገኘ እንደሆነ ገልጸዋል::

 3/ የዚህ ኑፋቄ ጥንስስ የተጀመረው (ከዚያ በፊት የነበረውን ለጊዜው ባናውቀውም) ፓትርያርኩ አባ ጳውሎስ ገና በአሜሪካ በፕሪንስተን ቴዎሎጂ ኮሌጅ በትምህርት ላይ እያሉ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጽሁፋቸውን ሲያዘጋጁ እንደነበር በዘንድሮው (2004 ዓ ም) የርክበ ካህናት የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የተከሰተውን ምስጢር“ ደጀ ሰላም” የተሰኘው ድረ ገጽ እንዲህ ሲል ዘግቦታል። 
     “አባ ጳውሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞተች ስለተባለ “የበደል ውርስ አለባት” ብለው ከሚያምኑ ጸሐፊዎች ጋራም ተባብረዋል፡፡ እነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌም የሚሉት እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህም ከአበው ድርሳናት ምስክርነት ቢያጡ የጠቀሱት ከቅብጦቹ ምንጭ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-
 Like all daughters and sons of Adam, the holy Virgin Mary died as a result of Adam’s sin. “Mary sprung from Adam, died on consequence of original sin; Adam died in consequence of sin, and the flesh of the Lord, Sprung from Mary, died to destroy sin.” (p.302) (Malaty, T.Y. St. Mary in the Orthodox Concept, 1978) ይህን ሐሳብ በተመለከተ አባ ሰረቀን ጨምሮ እነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌና ሌሎችም “ስሜን (ሥራዎቼን) በመጥቀስ ማታለያ አድርገውኛል” ያሉት ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ ግለሰቦቹ እሳቸውን በእነርሱ የኑፋቄ ሐሳብ ውስጥ እንዳይጨምሯቸው፣ ለራሳቸው እንዲመለሱና እንዲታገሡ በመከሩበት “ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ” በሚል ርእስ ባዘጋጁት የመጨረሻ መጽሐፋቸው፡“እነ ቄስ አስተርኣየ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞተች ስለተባለ የበደል ውርስ እንዳለባት አድርገው ሊቈጥሯት ሞክረዋል፡፡ ክሕደቱ፣ በደሉ ካልቀረ ሰው የኾነ አምላክ ልጇም የመስቀልን ሞት ተቀብሏልና ከአይሁድ ጋራ ቆመው የጲላጦስን ምስክርነት ቢያስተባብሉ ይሻላል፡፡ ከአበዱ ወዲያ በመንገዱ መሄድ መስነፍ ነው ይባል የለ?” በማለት ተችተዋል፡፡“
       እንግዲህ የዛሬውን ጽሁፍ ለማጠቃለል ፦ ነገር ሁሉ በሶስት ምስክር ይጸናል እንደተባለው እግዚአብሔርን የማይፈሩት ሰውን የማያፍሩትን ፓትርያርኩ አባ ጳውሎስ ለስም አጠራሯ ክብር ምስጋና ይግባትና እመቤታችን ቅድስናዋ በዘመኗ ከነበሩት ደናግል ብቻ ተለይታ እንደሆነ ፤ አማላጅነቷም በትውፊት ብቻ የተገኘ እንደሆነ ፤ እንዲሁም ከአዳም የተላለፈ የውርስ ሀጢአት እንዳለባት አድርገው በቤተ ክርስቲያናችን ስም ሲጽፉ ከታላቁ ሊቅ ከአለቃ አያሌው ታምሩ በስተቀር ከጳጳሳትም ሆነ ከሊቃውንት እንዲሁም ቤ/ክንን እናገለግላለን ከሚሉ ማህበራት ይህንን ስህተት በጊዜው የተቃወመ አልነበረም:: ይህም የቸልተኝነት ስሜት ችግሩ እየተባባሰ እንዲሄድ እድርጎታል:: ዛሬ እዚህ ቦታ ቤ/ክ ተቃጠለ፤ ዋልድባ ተመዘበረ ፤ መናፍቃን (ተሐድሶዎች) እንዲህ እደረጉ የምንለው የቤ/ክ ችግር ሁሉ ምንጩ  ቤ/ክንን እንመራለን ከሚሉት አካላት መሆኑን ሕዝቡም አሕዛቡም እያየው ነው:: ከዚህ አስከፊ ችግር ውስጥ ለመውጣት ከጾምና ከጸሎት ጋር ለመፍትሄ መነሳት የኛ የተዋህዶ ልጆች ድርሻ ነው:: ለዛሬው ይቆየን::
ቀጣዩን የመጽሐፉን ስህተቶች በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን::

No comments:

Post a Comment